የእለት ዜና

በአሸባሪነት የተፈረጀው ሕወሓት ሕጻናትን በጦርነት ማሳተፉን ዓለም አቀፉ ማሕበረሰብ እንዲያወግዘው ተጠየቀ

Views: 62

በአሸባሪነት የተፈረጀው የሕወሓት ቡድን እየፈጸመ ያለውን ሕጻናትን በአደንዛዥ ዕጽ በማስከር ወደ ውጊያ የመማገድ ወንጀል ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ሊያወግዘው እንደሚገባ የሴቶች፣ ህጻናትና ወጣቶች ሚኒስቴር ጠየቀ።
ዓለም አቀፍ ስምምነቶችን በመጣስ ህጻናትን ወደጦርነት ያሰለፈውን የህወሓት ሃይል በዓለም አቀፍ ወንጀል እንዲጠየቅም ዓለም ዓቀፍ ተቋማት ተባባሪ መሆን እንዳለባቸው ሚኒስቴሩ ገልጿል። ከሰሞኑ የሚወጡ መረጃዎች እንደሚያሳዩት ዓለም አቀፍ ድንጋጌዎችን በተጻረረ መልኩ ብዙ ወንጀሎችን በሕጻናት ላይ እየፈጸመ ስለመሆኑ በገሃድ ተስተውሏል።
የሴቶች፣ ህጻናትና ወጣቶች ሚኒስትር ዲኤታ አለሚቱ ኡሞድ የህወሓት ቡድን በመከላከያ ሠራዊት ላይ ከፈጸመው ኢ-ሰብዓዊ ድርጊት ባለፈ አሁን ደግሞ ሕጻናትን በአደንዛዥ ዕጽ አስክሮ ለጦርነት እያሰለፈ የወንጀል ድርጊት እየፈጸመ መሆኑን ገልጸዋል ሲል ኢዜአ ዘግቧል። “እድሜያቸው ለውጊያ ያልደረሱ የነገ አገር ተረካቢ ሕጻናትን ወደጦርነት ማስገባት ኢትዮጵያ ከፈረመቻቸው አህጉራዊና ዓለም አቀፍ ስምምነቶች የተጻረረ በመሆኑ ሊወገዝ የሚገባው ድርጊት ነው” ብለዋል።
ሕጻናት የነገ አገር ተረካቢዎች እንጂ ካለ እድሜያቸው በጦርነት እንዲሞቱ ማድረግ በዓለም አቀፍ ደረጃ የተደነገገ ወንጀል ቢሆንም፣ ዓለም አቀፉ ማሕበረሰብ ግን ሽብርተኛው የህወሓት ቡድን እየፈጸመ ያለውን ዓለም ቀፍ ወንጀል በዝምታ መመልከቱን አንስተዋል። ይህ ሕጻናትን ወደ ውጊያ የማስገባት ወንጀልን በዝምታ ማለፍ በአገር ሞራል ላይ መረማመድ እንደሆነም ገልጸዋል።
ይህንን ሰብዓዊ ወንጀል ያለማውገዝና የድርጊቱ ተባባሪ የመሆን ዝንባሌ የውጭ ኃይሎች መታየቱ ኢትዮጵያ በራሷ ሀብት እንዳትለማና ሕዝብ ከሕዝብ ጋር እየተጋጨ እንዲኖር ፍላጎት እንዳላቸው እንደሚጠቁምም አንስተዋል። “የሽብር ቡድኑ ዕድሜያቸው ለውትድርና ያልደረሱ ታዳጊዎቸን ወደውጊያ በማስገባት ዓለም አቀፍ ወንጀል እንዲጠየቅ ልንሰራ ይገባል” ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።


ቅጽ 3 ቁጥር 141 ሐምሌ 10 2013

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com