የእለት ዜና

የአገር ውስጥ ቱሪዝምና መሰናክሎቹ

ቱሪዝም ለአንድ አገር ዕድገት የሚኖረው አስተዋጽኦ ከፍተኛ እንደሆነ ይታመናል። ከጎብኚዎች በሚገኝ ገቢ አገራቸውን የሚያስተዳድሩ በርካታ አገሮች የመኖራቸውን ያህል፣ አነስተኛ ገቢንም እያገኙ ዘርፉን ትኩረት ሳይሰጡት በርካታ መስህቦቻቸውን የሚያባክኑ አገራት በርካታ ናቸው።

ኢትዮጵያ የረጅም ዘመን ታሪኳንና ታይተው የማይጠገቡ የተፈጥሮ ስጦታዎቿን ለጎብኚዎች አመቻችታና ትኩረት ሰጥታ ገቢ ማግኘት ከጀመረች ብዙም አልቆየችም። አገሪቷ የምታስተናግዳቸው ዓለም አቀፍ የጎብኚዎች ቁጥር ከዓመት ዓመት በ10.37 በመቶ እየጨመረ እንደሆነ እየተነገረ ቢመጣም፣ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ግን ማሽቆልቆሉ ይነገራል። በፈረንጆቹ 2018 እና 2019 የጎብኚዎች ቁጥር በ9 እና በ4.3 በመቶ በተከታታይ መቀነሱን ስለ ዓለም አቀፍ ጉዳዮች አህዛዊ መረጃ የሚያቀርበው Knoema የተሰኘው ተቋም በድረ-ገጹ ስለኢትዮጵያ የቱሪስት ፍሰት ካወጣው መረጃ መመልከት ይቻላል። የሰላም እጦት ለቁጥሩ መቀነስ ዋና ምክንያት ቢሆንም፣ የኮሮና መከሰት የራሱን ከፍ ያለ አስተዋጽኦ አበርክቷል። የአገሪቱ የጸጥታ ሁኔታም እያደር እየተባባሰ በመምጣቱ የቱሪስት ፍሰቱን የቁልቁለት ጉዞው ማስቆም አልተቻለም።

የውጭ አገራት ጎብኚዎች ቁጥር ሲቀንስ ኬንያን የመሳሰሉ አገራት መፍትሔ ያደረጉት ትኩረታቸውን ወደ አገር ውስጥ ጎብኚዎች ማዞር ነው። ዘርፉ እንዳይንኮታኮት፣ በቀላሉ መልሶ እንዲያንሰራራ እና ሕይወታቸውን በጎብኚዎች ላይ የመሰረቱትንም አካላት ለመደደገፍ ሲባል ነበር የትኩረት አቅጣጫው የተቀየረው። በመደበኛው ጊዜ የውጭ ምንዛሬ ከሚያስገኙት ጋር እየተጋፉ ውድ ገንዘብ መክፈል ለማይፈልጉት መካከለኛ ገቢ ላላቸው ዜጎች መልካም አጋጣሚ ነበር። በአነስተኛ ወጪ ግርግር በሌለበት መንገድ የውጭ ዜጋ የሚያዘወትረውን መዳረሻ ኬንያውያኑ ተቆጣጥረውት የቱሪዝም ዘርፉን መታደጋቸው ተነግሮላቸው ነበር።

ወደ እኛ አገር ስንመጣ ሆቴሎችን ጨምሮ ከዘርፉ ጋር ግንኙነት ያላቸው ድርጅቶችና ግለሰቦች ለችግር መዳረጋቸው ሲነገር ነበር። ይህ ቢሆንም አስጎብኚ ድርጅቶች የለመዱት ገቢ ቀንሶባቸውም ከዚህ በፊት ከሚጠይቁት ዋጋ ቀንሰው ኢትዮጵያውያን ጎብኚዎችን ለመሳብ ሲጥሩ አልተስተዋለም።

በሌላ በኩል፣ ከአገር ውስጥ ጎብኚዎች ጋር በተገናኘ ትኩረት ሰጥተው ዘርፉን ለማሳደግ የሚሰሩም አሉ። ከእነሱ መካከል ጉዞ አድዋ አንዱ ነው። ጉዞ አድዋ፣ የአድዋ ጦርነትን የሚዘክር፣ ላለፉት 8 አመታት ወጣቶችን በማሰባሰብ እየተካሄደ የሚገኝ እና ከአዲስ አበባ አድዋ ድረስ ለ45 ቀናት የሚደረግ የእግር ጉዞ መርሃ-ግብር ነው። በእግር ጉዞው ወቅት ተጓዦቹ በሚያልፉባቸው አካባቢዎች ያሉ ታሪካዊ ቅርሶችን እንደሚያስጎበኙም የጉዞ አድዋ ዋና አስተባባሪ ምስክር ከበደ ነግረውናል።

ይህ መርሃ-ግብር ከስፖርታዊ የጤና ጠቀሜታው ባሻገር፣ ታሪካዊና ተፈጥሯዊ መስህቦች በኢትዮጵያውያን እንዲታወቁ በማድረጉ ዝናን ማትረፉ ይነገርለታል። እያደር እውቅና ያገኘው ጉዞ አድዋ በዓመት አንድ ጊዜ የሚያደርገው እንቅስቃሴ በቂ ሆኖ ስላላገኘው፣ ሌሎች ጉዞዎች ማድረግ ከጀመረ ኹለት አመት አልፎታል። ያለምንም ወጪ አድዋ የሚጓዙበትን ዓላማ ለማጠናከር በማሰብ በሳምንትና በየ15 ቀኑ የተለያዩ ቦታዎችን ለማስጎብኘት የእግር ጉዞ ያለባቸውን መዳረሻዎች ሲመርጥ ቆይቷል። ከ500 እስከ 700 ብር በማስከፈል በርካታ ተጓዦችን በመያዝ የደርሶ መልስም ሆነ የአዳር ጉዞዎችን በማመቻቸት ትርፉን ለጉዞ አድዋው ተጓዦች መደጎሚያ ያስቀምጣል።

የጉዞ ማኅበሩ ከአዲስ አበባ በቅርብ ርቀት ላይ የሚገኙ ለእግር ጉዞም የሚመቹ መዳረሻዎችን ቅድሚያ በማሰስ ይመርጣል። የታወቁትን እንደ ወጨጫ፣ ባሌና አዋሽ ፓርክን የመሳሰሉ ቦታዎችን ለማስጎብኘት በሚያደርገው ጉዞ ወቅት ያን ያህል እክል እንደማይገጥም የሚናገሩት ምስክር፣ ራሳቸው ፈልገው የሚያገኟቸውን አዳዲስ ቦታዎችን ለማስጎብኘት ግን የተለያዩ መሰናክሎች ይገጥሟቸዋል። ወጣቶች መንገድ ዘግተው አናሳልፍም ብለው ተጓዦች ላይ ከሚፈጥሩት ስጋት ባሻገር፣ አካባቢዎቹ ጎብኚ ስለማያውቁ ሲመጣባቸው ግር ይላቸዋል። በተለይ ኢትዮጵያውያን ጎብኚዎች ወደአካባቢያቸው መምጣታቸው ጥርጣሬ ውስጥ ስለሚከታቸው፣ “ከየት የመጡ ናቸው?” እያሉ መሰናክል ይሆናሉ። “አትምጡብን” የሚሉና የማለፊያ ገንዘብ የሚጠይቁም ወጣቶች አሉ ብለውናል።

የታወቁ መዳረሻዎች የቱሪዝም ቢሮዎችን ጨምሮ ጠባቂ አላቸው። ያረጀም ቢሆን መሠረተ ልማት ስለሚኖራቸውም ያን ያህል አያስቸግሩም። አዳዲስ በሚገኙ መስህቦች አካባቢ ግን የማስተዋወቅ ሥራው ዝቅተኛ በመሆኑ፣ መንግሥትም የባሕልና ቱሪዝም ቢሮዎች በአካባቢዎቹ ስለሌለው ለአገር ውስጥ ጎብኚዎች መሰናክል ሆኗል። ደብረ ዘይት/ቢሸፍቱ አካባቢ ያለን ብዙም የማይታወቅ አረንጓዴው ሐይቅ የተባለን መስህብ፣ የረርን፣ በጀርባና ደንቢ ሐይቅን እንዲሁም ፉሪ ተራራን ለማስጎብኘት የነበረው ዕቅድ ዓላማውን ባልተረዱ ግለሰቦች ምክንያት ችግር ተፈጥሮ ነበር። በእንዲህ አይነት አዳዲስ ቦታዎች የሚፈጠሩትን መሰናክሎች ጉዞ አድዋ እያለፈ እስካሁን የተለያዩ ቦታዎችን እንዳስጎበኘ አስተባባሪው ነግረውናል። የሕብረተሰቡ ግንዛቤ አነስተኛ በመሆኑ ከጎብኚዎች ሊያገኝ የሚችለውን ጥቅም እያስረዳን፣ የሚፈጠረውንም የሥራ ዕድል እያሳየን ብዙ ተጉዘናል የሚሉት ምስክር፣ ለወደፊቱ ልምዱን ለማጠናከርና ሩቅ ቦታዎችንም ለማስጎብኘት አቅደናል ብለዋል።

የተለመዱት አስጎብኚ ድርጅቶች ትኩረታቸው የውጭ አገር ዜጎች ላይ በመሆኑ፣ እንዲሁም ትልቅ ወጪን የሚያስከትሉ ማረፊያዎችን ስለሚጠቀሙ የአገር ውስጥ ጎብኚዎችን ለመሳብ ይቸገራሉ። የሕብረተሰቡን ፍላጎት ከግምት ውስጥ በማስገባት፣ ለሚያስፈልገው መሰረታዊ ወጪ የሚሆን አነስተኛ የሆነን ክፍያ በመተመን ኢትዮጵያውያን ጎብኚዎችን ቁጥር ለማሳደግ እንደታሰበም ነግረውናል። እንደ አድዋው ጉዞ ተጓዡ የሚያርፍበት ነጻ ቦታ ለማግኘት ካልተቻለ ድንኳንን የመሳሰሉ አማራጮችን በመጠቀም የአገር ውስጥ ጎብኚዎችን ለማሳደግ እየታቀደም ነው ብለውናል።

የጉዞ አድዋን ዓላማ የተረዱ ብዙ እንደመሆናቸው፣ እስካሁን አባላቱ ያለምንም ክፍያ እያገለገልን እንገኛለን ያሉን ምስክር፣ ለወደፊቱ በርካታ ጉዞዎች ስለሚታቀድና ሥራውም ስለሚሰፋ፣ በትርፍ ጊዜም ሊሠራ የማይችል ስለሆነ በአነስተኛ ክፍያ ሰራተኞች እንዲኖሩት ይደረጋል። ለጊዜው ትርፍ ላይ አተኩሮ ስለማይሠራ ለማደግና ለመስፋፋት እንቅፋት እንደሆነበት የሚያምነው ማኅበሩ፣ የተለያዩ አካላት በማሳተፍ እገዛ ይጠብቃል።

የኢትዮጵያ የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ጋር የሚሠራ ቱሪዝም ኢትዮጵያ የተባለ ድርጅት የጉዞ አድዋን ዓላማ በመረዳት ከሌሎች መሰል ድርጅቶች ጋር በጋራ ለመርዳት እንቅስቃሴ መጀመሩን ሰምተናል። ማንኛውንም ድጋፍ ከማድረጉ በፊት ሕጋዊ አሰራርን ለመከተል እንዲያስችል እውቅናም እንድናገኝ ማኅበር እንድንመሰርት ተጠይቀናል ያሉን የጉዞ አድዋ አስተባባሪ፣ በቅርብ ጊዜ ውስጥ ተጠናቆ ማግኘት የሚገባንን ድጋፍ እንድናገኝ ያስችለናል ብለዋል።

የአገር ውስጥ ጎብኚዎችን ቁጥር ለመጨመርና የቱሪስት መዳረሻዎችን ለማስፋት የሚሠራው ጉዞ አድዋ፣ ከማስጎብኘት በተጨማሪ የተጓዦችን ጤና ለማስጠበቅም የእግር ጉዞን እያካተተ ይገኛል። የእግር ጉዞ ያላቸውን ጉብኝቶች ለይቶ በማዘጋጀት እስከ 15 ኪሎ ሜትር ሊረዝሙ የሚችሉ መንገዶችን በመምረጥ የጤና ጉዳይንም ትኩረት አድርጎ ይሠራል።

አዲስ አበባ ከፍተኛ መጠን ያለው ገንዘብ በየዕለቱ እንደማንቀሳቀሷ ያን ያህል ከነዋሪዎቿ ጋር የተመጣተነ መዝናኛ እንደሌላት ይታወቃል። አብዛኛው ነዋሪ ተጨናንቀው ያሉ የተለመዱ ቤቶችን በማዘውተሩ ለጤናው የማይስማማ ተግባራት ላይ ያዘወትራል። ነገሮች ምቹ ባለመሆናቸውም ኗሪው እንደ አቅሙ ወጣ ብሎ ለጤናውም ሆነ ለመንፈሱ ጠቃሚ የሆነ እንቅስቃሴ ላይ ሲሳተፍ አይስተዋልም። ለአንድ ምሽት መዝናኛ የሚያወጣውን ለበጎ ዓላማ ማዋል ይችላል ያሉት ምስክር፣ ለራሱ መዝናኛ ብቻ ሳይሆን ለበርካቶችም የገቢ ምንጭ ሊሆን ይችላል።

ጉዞ አድዋ መስህቦችን ከማስጎብኘትና ጤና ተኮር እንቅስቃሴዎች ላይ ከማዘውተር ባሻገር በጎ አድራጎት ተግባር ላይም እንደሚሳተፍ ተነግሮናል። እሁድ ሐምሌ 11 በጉለሌ የዕፅዋት ማዕከል ኹሉም የሚሳተፍበት የእግር ጉዞ መርሃ ግብር በ100 ብር አዘጋጅቷል። ለአስፈላጊ ወጪዎች ከሚውለው ከዚህ ክፍያ ውጭ፣ መግቢያው ለእርዳታ የሚውል የመማሪያ ቁሳቁስ ነው። “በትምህርት መርጃ ቁሳቁስ እጥረት አንድም ተማሪ ከትምህርት ገበታ መቅረት የለበትም” የሚል የማኅበራዊ ሚዲያ ዘመቻን ለማገዝ በታቀደው በዚህ ጉዞ መሳተፍ የሚፈልግ ሰው፣ ደርዘን(12) ደብተር፣ 2 እስክርቢቶ፣ 2 እርሳስ፣ 2 ላጲስና 2 መቅረጫ ይዞ መምጣት ይጠበቅበታል። ይህ አይነቱ የእግር ጉዞን ያካተተ ጉብኝት ከመደበኛው በተለየ መልኩ በጎ አድራጎት ተግባርን የሚያበረታታ እንደሆነ ምስክር ነግረውናል።

የኢትዮጵያን የውጭ ቱሪዝም ፍሰት ከአገር ውስጡ ጋር እያነጻጸሩ ጥናታዊ ጽሁፍ ያቀረቡት ብርሃኑ እሱባለው እንደሚሉት፣ የአገር ውስጥ ጎብኚዎች ቁጥር በየአመቱ እየጨመረ ቢመጣም ሁኔታው ከቦታ ቦታ ይለያያል። ላሊበላን በመሳሰሉ መንፈሳዊ መዳረሻዎች በየጊዜው ቁጥሩ በከፍተኛ ፍጥነት እየጨመረ ሲሆን፣ የውጭ ጎብኚዎችንም በብዙ እጥፍ የበለጠበት አመታት አሉ። ይህ ቢሆንም ግን ኢትዮጵያውያን አገራቸውን የመጎብኘት ዝቅተኛ የሚባል ፍላጎት እንዳላቸው በጥናት መረጋገጡ ተጠቅሷል።


ቅጽ 3 ቁጥር 141 ሐምሌ 10 2013

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com