የእለት ዜና

አሸናፊው ፈጥኖ የተሸነፈበት የውጊያ ውሎ!

Views: 69

በያዝነው ሳምንት በኢትዮጵያውያን ዘንድ መነጋገሪያ ከነበሩ ክስተቶች ዋና የነበረው “ህወሓት አላማጣንና ኮረምን ተቆጣጠረች” የሚለው ነው። ከመቐለው መለቀቅ የበለጠ ዜናው ለብዙዎች ዱብ እዳ ያልነበረ ቢሆንም፣ መከላከያ ያለምንም ውጊያ እንዲወጣ መደረጉ ብዙዎችን ያስገረመ ነበር። ይህ ብቻ ሳይሆን ድል እየቀናው ሊወር የመጣውን ኃይል እየመለሰ የነበረው የአማራ ልዩ ኃይል ቀኝኋላ ዙር ተብሎ እንዲመለስ ተደረገ የሚለው ብዙዎችን ያበገነ ክስተት ነበር።

ከህወሓት ጥቃት ይበልጥ መነጋገሪያ የነበረው የአዋጊዎች ድርጊት እንደነበር ጉዳዩን ለተከታተለው ግልፅ ነው። በተለይ ከተለያየ አካባቢ የግል ስንቃቸውንና ትጥቃቸውን ይዘው እንዲገኙ ተደርገው የነበሩ የገበሬ ታጣቂዎች ያለምንም ምክንያት በመኪና መጥተው በእግር እንዲመለሱ መደረጋቸው ብዙዎችን ተስፋ ያሰቆረጠ ድርጊት ነበር። በተንቀሳቃሽ ምስል የተቀረጸው ጉዟቸው ይፋ ተደርጎ የተመለከተ ዘማቾቹ በድካም ተሰላችተው ቅርብ እየመሰላቸው የቀናትን ጉዞ በእግር ለመመለስ ሲጥሩ ላስተዋለ አንጀት የሚበላ ክስተት ነበር።
ህወሓት ጥቃት እንደምትከፍት በግልጽ ስትናገር የቆየች ቢሆንም፣ ከመቐለ እንደተወጣው ዝግጅት ተደርጓል ሳይባል ከፍተኛ የጦር መሳሪያዎች ባሉበት ተትተው መወጣቱ፣ “ሊያስጨርሱን ነው” እስከማስባል አድርሶ ነበር። አላማጣንና ኮረምን ያለምንም ውጊያ የተቆጣጠሩት ህወሓቶች ድል አደረግን ብለው ዜናውን በዓለም አቀፍ ደረጃ ለማስተጋባት ጊዜ አልፈጀባቸውም ነበር። መሪዎቹም ከተማዋ መግባታቸውን ለማሳወቅ ፈጥነው የነበረ ቢሆንም አልዘለቀላቸውም ነበር።

እንደመርዶ ንጋት ሳይጠብቅ የተሰማው የከተማዎቹ መያዝ ያንገበገባቸው ሰዎች ንዴታቸውን ሳይጨርሱና ወቀሳቸውም ደርሶ ሳይሰማ በበነጋታው ምሽት ሌላ ተቃራኒ ዜና ተሰራጭቷል። የአማራ ልዩ ኃይል ጥሪ ተደርጎላቸው ከነበሩ የአማራ ሠራዊት ጋር በመሆን ከተማዎቹን መልሶ መቆጣጠር መቻሉ ሲነገር ወዲያው ለማመን ያስቸገራቸው በርካቶች ነበሩ። የእርዳታ ጥሪው ደርሶ ሌሎች ሳይደርሱ ከተማዎቹን ማስለቀቅ ቢቻልም በነበሩበት እንደማይቆሙ ብዙዎች ሲናገሩ ነበር።

መንግሥት ጉዳዩን አስመልክቶ ትዕግስቱ እንዳለቀ መግለጫ ቢሰጥም፣ “ተግባር እንጂ ንግግር የሚያስፈልግበት ጊዜ አይደለም” እያሉ ከአድናቆትም ሆነ ከትችት የተቆጠቡ ነበሩ። በሌላ በኩል ብዙዎች ውጊያው በኹለት ክልሎች መካከል ብቻ የሚደረግ መምሰል የለበትም እያሉ ሲተቹ ነበር። ይህ አስተያየት ቀደም ብሎ ከ8 ወር በፊት ተሰንዝሮ የነበረ ቢሆንም፣ ምላሽ ያገኘው ግን በዚህ ሳምንት ነው። የኦሮሚያ፣ ደቡብና ሲዳማ ክልሎች ለሚልኩት ልዩ ኃይል ሽንት አድርገው ሲደርሱም አቀባበል ተደርጎላቸዋል።

በሌላ በኩል የክልል ልዩ ኃይሎች በተናጥል የጦር አውድማው ውስጥ ገብተው ከሩቅ ሆነው ለሚመለከቱት የውጭ ኃይሎች፣ የክልሎች ግጭት እንዳይመስል የጋራ ጠላት ሆና ድንበራችንን አልፋ ወደመጣችው ሱዳን አቅጣጫቸውን እንዲያዞሩ ይመክራሉ። ያም ሆነ ይህ የእርስ በርስ ውጊያን ለማፋፋም ከሚሰለፉ ይልቅ ለአንድነታችን መሰረት የሚጥሉ የጋራ ጠላቶችን በማስተንፈስ ቅድሚያ ቢሰጥ፣ በነሱ የተማመነንም ዝም ማስባል እንደሚቻል የሚናገሩ አሉ።


ቅጽ 3 ቁጥር 141 ሐምሌ 10 2013

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com