የእለት ዜና

የኮቪድ ክትባት በኢትዮጵያ

Views: 50

የካ ክፍለ ከተማ፤ ባልደራስ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ፤ ወረዳ 7 ጤና ጣቢያ ተገኝተናል። የጤና ጣቢያው በርቀት በተተከሉ ድንኳኖች አንዳች ድንገተኛ ክስተት የተፈጠረበት ይመስላል። አሻግረው ወደ ድንኳኑ የሚመለከቱ በእድሜ ጠና ያሉ እናቶችና አባቶች እንዲሁም ጎልማሶች በጊቢው በተን ብለው በየቆሙበት የየራሳቸውን ወግ ይዘዋል። አንዳች የሚጠብቁት ኹነት እንዳለ ግልጽ ነው። አዲስ ማለዳ ቀረብ ብላ እነዚህን ሰዎች ለማነጋገር ሞክራለች።

ሥማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ አንድ እናት ከሦስት ወር ገደማ በፊት የመጀመሪያውን ዙር ክትባት መውሰዳቸውን በማስታወስ ይጀምራሉ። አሁንም የጤና ሚኒስቴር ኹለተኛ ዙር መውሰድ ለሚገባቸው ሰዎች ክትባት ወደ አገር ውስጥ መምጣቱን ተከትሎ ለመከተብ በስፍራው እንደተገኙ ተናግረዋል።

‹‹ይመጣል ብለውን ነበር። እስከአሁን ግን ምንም አዲስ ነገር የለም፤ እየጠበቅን ነው። ከዛሬ ነገ ይመጣል ብለን ስንጠብቅ ተንገላታን።›› ሲሉ የገለጹት ወይዘሮዋ፣ በጤና ጣቢያው ያሉ አገልግሎት ሰጪ የጤና ክብካቤ ባለሞያዎች እንዲታገሱ እንደነገሯቸው ለአዲስ ማለዳ ጠቅሰዋል። በምንአልባት ግን ከቦታው ሊንቀሳቀሱ እንዳልፈለጉና ክትባቱን በፈጥነት ለማግኘት ከፍተኛ ጉጉት እንዳደረባቸው አኳኋናቸው ያስታውቃል።
ክትባቱ መጀመሪያ ሲተዋወቅ ግን አቀባበሉ እንዲህ በጉጉት አልነበረም፤ በምልሰት እናውሳ፤

ኮቪድና የክትባቱ አቀባበል
ነገራችንን ወደኋላ መለስ ብለን እንጀምር፤ ዓለማችን በተለያየ ጊዜ ከባድ የሆኑ ወረርሽኞችን አስተናግዳለች። በእነዚህም እጅግ በርካታ የሆኑ ሰዎች ሕይወት አልፏል። እነዚህ ወረርሽኞች ቶሎ መድኃኒትም ሆነ ክትባት ያልተገኘላቸው መሆኑም ትዝታውንና ትውስታውን አሰቃቂና ዘግናኝ ያደርገዋል። በተጓዳኝ እነዚሁ ኹኔታዎች ተመራማሪዎች አዳዲስ እውቀቶችንና አካሄዶችን እንዲያዩና መፍትሔ እንዲፈልጉ መንገድ ጠርገዋል።

ኤች አይቪ ኤድስ እንዲሁም ኢቦላ ቫይረስ በቅርብ ዓመታት ዓለማችን ያስተናገደቻቸው ወረርሽኞች ናቸው። እነዚህንም ማጥፋት ባይቻልም ቢያንስ ለመቆጣጠር የተለያዩ ጥረቶች ተደርገዋል፤ ጥረቶቹ ግን ዓመታትን የወሰዱ ናቸው። ክትባቶች ብዙ ምርምር፣ ብዙ ገንዘብና ረጅም ጊዜን ይወስዳሉ። ከዛም በብዛት አምርቶ ተደራሽ ማድረግ ላይ የሚወስደው ጊዜም እንደዛው ይቆያል።

ዓለምን ከተዋወቀ ኹለት ዓመቱን ሊሞላ ወራት የሚጠብቀው ኮቪድ 19 ኮሮና ቫይረስ በአንጻሩ ክትባቱ በቶሎ የተገኘለት ይመስላል። የክትባቱን ፈዋሽነት እንዲሁም ተያያዥ የጎንዮሽ ጉዳቶችን በሚመለከት አሁንም የሚጠበቁ ጥናቶች ያሉ ቢሆንም፣ ቢያንስ ቫይረሱ በሰውነት ውስጥ ሊያስከትል የሚችለውንና ለሞት የሚዳርገውን ከባድ ሕመም ለመቀነስና ለመከላከል እንደሚያስችል ተመራማሪዎች፣ የጤና ክብካቤ ባለሞያዎችና የጤና ጉዳይ ይመለከተናል ያሉ ዓለማቀፍ ተቋማት ደጋግመው አስረድተዋል።

በአንጻሩ ክትባቱ በአጭር ጊዜ ተገኘ መባሉ አንዳንድ የቀደሙ ጥርጣሬዎችን በድጋሚ በአዲስ ዕይታ ሳይቀሰቅስ አልቀረም። በተለይም ቫይረሱ ከቤተ ሙከራ ያመለጠ ነው፣ ይሁነኝ ተብሎ የተፈጠረና የተሰራጨ ነው… ወዘተ የሚሉ አመለካከቶችን ‹እውነት ይሆን እንዴ?› ብሎ ለመጠየቅ የገፋፋም ይመስላል። ‹ክትባቱ ከምኔው ተገኘ? ሌሎች ቫይረሶች እንዲህ በፍጥነት መች ክትባት ተገኝቶላቸው ያውቃል?› አብሮ ተያይዞ የተነሳ ጥያቄ ነው።

ይህንን ተከትሎም ክትባቱ ከክፉ መንፈስ ጋር ይያያዛል፣ በክትባት መልክ የሚሰጡን ሌላ ‹ነገር› ነው፣ የሚቀብሩብን ነገር አለ፣ በቶሎ ለሞት ይዳርጋል፣ ኦቲዝምን ያስከትላል…ወዘተ የሚሉ ሐሳቦች በማኅበራዊ ሚድያ በስፋት ሲዘዋወሩ ተስተውሏል። በዚህም ላይ ‹በክትባቱ ሳቢያ› የደም መርጋት የገጠማቸውና ሕይወታቸው ያለፉ ሰዎች እንዳሉ የተነገሩ ዜናዎች ውጥረቱን አባባሱት። ‹ክትባቱን አንወስድም› የሚሉ ሰዎች ቁጥርም ከፍተኛ ሆነ።

ፌስቡክ ሳይቀር ክትባቱ መርዛማ ነው፣ አደገኛ ነው፣ ኦቲዝም ያስከትላልና መሰል የሚሉ በገጾች የተለጠፉ ጽሑፎችን እንደሚያነሳ አሳውቆ ነበር። የአውሮፓ ኅብረት የመድኃኒት ቁጥጥር ባለሥልጣንም ክትባቱ የደም መርጋትን እንደማያስከትል ደጋግሞ አስረድቷል።
ይህ ጉዳይ በመላው ዓለም አነጋጋሪ የነበረ ነው። ይህን ለማሸነፍና ክትባቱን ሰዎች እንዲወስዱ ለማድረግ ታድያ የጤና ጉዳይ ይመለከተናል ያሉ ሁሉ ቅስቀሳና ግንዛቤ መስጠት ላይ ብዙ ሠርተዋል። አልፎም ታላላቅ ሰዎችና የአገር መሪዎች ጭምር ክትባቱን በመውሰድ አረአያነትንም በማሳየት ዜጎቻቸው እንዲከተቡ ጥሪ አቅርበዋል። ብዙዎቹም ተሳክቶላቸዋል ማለት ይቻላል።

ኢትዮጵያና የኮቪድ ክትባት
ከዓለም ዜና የማትርቀው ኢትዮጵያ፣ ዜጎቿ የኮቪድ ክትባትን በጥርጣሬ ዐይን መመልከታቸው አልቀረም። የጤና ባለሞያዎችን ጨምሮ እጅግ በርካቶች ክትባቱን ለመቀበል በቶሎ አልፈቀዱም። ክትባቱ የባሰ ሕመም የሚያስከትል አልፎም ለሞት የሚዳርግ፣ እድሜንም የሚያሳጥር እንደሆነ በተለይ በማኅበራዊ ገጾች የሚጻፈውና የሚባለው ከፍተኛ ተጽእኖ ማሳደር ችሎ ታይቷል።

የካቲት 28/2013 ነበር ኢትዮጵያ ኮቫክስ ከተሰኘው ዓለማቀፍ የክትባት አቅርቦት ጥምረት 2.2 ሚሊዮን የኮቪድ ክትባት የተረከበችው። መጋቢት 4 ቀን 2013 ደግሞ በአዲስ አበባ ክትባቱ መሰጠት ተጀመረ። ለተለያዩ ክልል ከተሞችም በተመሳሳይ ጊዜ ክፍፍል ተደረገ። በዚህ ጊዜም የክትባቱ ጎጂነት በተደጋጋሚ ሲጠቀስና ሲነሳ ይሰማ ነበር። ደረሱ ከባድ ጉዳቶች የተጠቀሱ ባይኖሩም፣ የክትባቱ የጎንዮሽ ሕመም የሆኑ እንዳሉ፣ እነዚህም ማንኛውም ክትባትና መድኃኒት መውሰድን ተከትሎ ሊስተዋሉ የሚችሉ መሆናቸውን ጤና ሚኒስቴርና የጤና ባለሞያዎች ተረዱልን ሲሉ ቆይተዋል።

በጊዜው መጀመሪያ ክትባቱን የወሰዱት የአዲስ አበባ ጤና ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ዮሐንስ ጫላ ክትባቱን ሲወስዱ፣ በክትባቱ ዙሪያ የሚናፈሱት አሉባታዎች ሁሉ ከእውነት የራቁ ናቸው ሲሉ መናገራቸውም የሚታወስ ነው። ታድያ ይህን ቅስቀሳና የተሳሳተውን ግንዛቤ የማረም ሥራ ተጠናክሮ ክትባቱን የሚወስዱ ሰዎች ቁጥር በየእለቱ ሲጨምር ተስተውሏል።

የጤና ሚኒስቴት ሐምሌ 5 ቀን 2013 ባወጣው መግለጫ፣ መግለጫው እስከተሰጠበት ዕለት ድረስ ኢትዮጵያ 2 ሚሊዮን 64 ሺሕ 777 ዜጎቿን ከትባለች ሲል አስታውቋል። ከእነዚህም 42 ሺሕ በላይ የሚሆኑ የኹለተኛ ዙር ክትባት ወስደዋል። በእለቱም ተጨማሪ 400 ሺሕ የሚጠጋ የአስትራዜኒካ ክትባት ወደ ኢትዮጵያ መግባቱን አስታውቀዋል። ክትባቱ የዘገየውም በዓለማቀፍ ደረጃ በተከሰተ እጥረት ነው ሲሉ ሚኒስትሯ ዶክተር ሊያ ታደሰ አስታውቀዋል።

በዚሁ መግለጫ በተሰጠበት እለት ማግስት ጀምሮ በአዲስ አበባ ክትባቱ መሰጠት እንደሚጀምር የገለጹ ሲሆን፣ ከሐምሌ 9/2013 ጀምሮ ደግሞ በክልሎች የመጀመሪያውን ክትባት ከወሰዱ 3 ወር የሞላቸው ዜጎች መውሰድ ይችላሉም ተብሏል።በደቡብ አፍሪካ የኮቪድ ስርጭት ካለበት ሊከፋ ይችላል ተባለ

የቀድሞ ፕሬዘዳንቷ ጃኮብ ዙማ መታሰራቸውን ተከትሎ በኹከትና ዝርፊያ እየተናወጠች ባለችው ደቡብ አፍሪካ የኮቪድ 19 ሪፖርቶች በከፍተኛ መጠን ሊጨምሩ እንደሚችሉ በአፍሪካ የዓለም ጤና ድርጅት አስታወቀ።
አለመረጋጋቱ እንዲሁም ዝርፊያው በአገሪቱ ኹለት ትልልቅና ብዙ ሕዝብ በሚገኝባቸው፣ ከፍተኛ የንግድ እንቅስቃሴ በነበረባቸው ግዛቶች የተስተዋለ ሲሆን፣ እየደረሰ ካለው ጥፋት በተጓዳኝ የኮቪድ ስርጭቱ በከፍተኛ መጠን እንዲጨምር እንደሚያደርግ ከወዲሁ ተገምቷል። ይህም የዓለም ጤና ድርጅት እየጠበቀ ያለውን ሦስተኛውን የኮቪድ ወረርሽኝ ማዕበል ሊያከፋው ይችላል ተብሏል።
የዓለም ጤና ድርጅት የደቡብ አፍሪካ መንግሥት ለዚህ እንዲዘጋጅ ሲልም ጥሪ አስተላልፏል።
ደቡብ አፍሪካ በአፍሪካ ከፍተኛ ቁጥር ያለው ሕዝቧን በኮቪድ ያጣች ሲሆን፣ በተጠቂ ሰዎች ቁጥርም በቀዳሚነት ትገኛለች። ልውጥ የሆነው የቫይረሱ ዝርያም በአገሪቱ ከፍተኛ ስጋት ያሳደረ ሲሆን፣ ከቀናት በፊት በተጀመረው ዝርፊያና ኩኸት ሳቢያ የክትባት አገልግሎቱም እንደተቋረጠ ተገልጿል። መረጃውን ከብሉምበርግ ገፅ ላይ ያገኘነው ሲሆን፣ ይህ ዘገባ በተጠናቀረበት ሰዓት የደቡብ አፍሪካ መንግሥት ኹከቶችን በማረጋጋትና የተዘረፉ ንብረቶችን በማስመለስ ላይ እንደሆነ አስታውቋል።


ቅጽ 3 ቁጥር 141 ሐምሌ 10 2013

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com