የእለት ዜና

በመጓጓዣዎች ውስጥ የሚከሰቱ ጾታዊ ትንኮሳዎች አሳሳቢነት

Views: 80

በመጓጓዣዎች ላይ የሚፈጸሙ ጾታዊ ትንኮሳዎችን ለመቅረፍ አዲስ አዋጅ ለማጽደቅ በስፋት እየተሠራ መሆኑን የሴቶች፣ህጻናትና ወጣቶች ሚኒስቴር አስታውቋል።
ጾታዊ ትንኮሳ የሚባለው በተለያየ መልኩ በሰዎች ላይ የሚፈጸም አካላዊና ሥነ-ልቦናዊ ጥቃታ ብሎም በንብረት ላይ የሚደርስ ጉዳት ነው። ጾታዊ ትንኮሳ አንዱ ወገን ሳያውቅ ወይም ሳይፈልግ የሚደረግ ማንኛውም ጾታን መሰረት ያደረገ ድርጊትን ይገልጻል።
ለጾታዊ ትንኮሳ ተጋላጭ ከሆኑ የማሕበረሰባችን ክፍሎች ውስጥ በዋናነት ወጣት ሴቶች ተጠቃሽ ናቸው። በሴቶች ላይ የሚፈጸም ጾታዊ ትንኮሳ የሚባለው፣ ጾታን መሰረት አድርጎ በአካልና በንብረት ላይ ወሲባዊና ሥነ-ልቦናዊ ጉዳት ሊያደርስ የሚችል ማንኛውም አይነት ደርጊት ነው።

በሴቶች ላይ የሚደርስ ጾታዊ ትንኮሳ በብዙ መንገድ የሚገለጽ ሲሆን፣ ከነዚህም መካከል ጾታን መሰረት ያደረገ ሐሳብ ወይም ስድብ በሴቶች ላይ መሰንዘር እና ያለ ሴቶች ፈቃድ የሚደረግ አካላዊ ንክኪ ይጠቀሳል።
ጾታዊ ትንኮሳ ከሚፈጸምባቸው ቦታዎች አንዱ የትራንስፖርት አገልግሎት መሆኑ ይታወቃል። የሕዝብ ትራንስፖርት ሕዝብን ከማገልገል ባለፈ ለተለያዩ ወንጀሎችና ጾታዊ ትንኮሳዎች አጋላጭ ቦታ በመሆኑ ደርጊቱን ፈጻሚ አካሎች በስፋት እየተንቀሳቀሱበት የሚታዩበት ቦታ ነው።

የባቡርና አውቶቡስ ትራንስፖርት ሴቶች ለጾታዊ ትንኮሳ የሚዳረጉበት አንዱና ዋነኛው ቦታ መሆኑ ይታወቃል።
በሴቶች ላይ የሚደርስ ጾታዊ ትንኮሳ በየትኛውም ጊዜና ቦታ የሚከሰት ቢሆንም በባቡር እና አውቶብስ ትራንስፖርት ላይ በይበልጥ ይስተዋላል።
የባቡር ትራንስፖርት ተጠቃሚ ሴቶች ባቡር ላይ የሚያጋጥሙ ጾታዊ ትንኮሳዎችን በተመለከተ የከዚህ ቀደም ገጠመኞቻቸውን እና አሁን ላይ ያስተዋሉትን ለአዲስ ማለዳ አካፍለዋል።
ለአብነት ያህል ወይንሸት አንዳርጋቸው የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪና የባቡር ትራንስፖርት ተጠቃሚ ናት። ጸታዊ ትንኮሳን እንዲህ በማለት ገልጻዋለች። ‹‹ሴቶችን ሆን ብሎ ነጻነታቸውን መንፈግ፤ መጥፎ ቃላትን መናገር፤ እንዲሁም ያለፈቃዳቸው የሚደረግ ማንኛውም አይነት አካላዊ ንክኪ ነው።››

የባቡር ትራንስፖርት በምጠቀምበት ወቅት ጾታዊ ትንኮሳ እኔን አጋጥሞኝ ባያውቅም፣ በቅርቡ ግን በነበርኩበት ባቡር ውስጥ የነበረን ከፍተኛ የተሳፋሪ መጨናነቅ በመጠቀም አንድ ወጣት ከፊት ለፊቱ የነበረችውን ወጣት ሴት ሆን ብሎ ሲተሻሻት ተመልክቻለው ብላለች።
ጾታዊ ትንኮሳ የደረሰባትም ልጁን በኃይለቃል ተናግራው እንደገፈተረችው ተመልክቻለሁ። ነገር ግን ድርጊቱን የፈጸመው ሰው ምንም እንዳልተፈጠረ ሲያስመስል እንደነበረ ታስታውሳለች።

ለችግሩ ዋናው መነሻ በከፍተኛ ሁኔታ በሚፈጠር የትራንስፖረት እጥረት የሚከሰት የተሳፋሪዎች ከመጠን በላይ መተፋፈግ እንደሆነ ወጣቷ ትናገራለች። ወይንሸት የባቡር ትራንስፖርት በምንጠቀምበት ጊዜ ተገቢውን ጥንቃቄ ማድረግ አስፈላጊ መሆኑን በመጠቆም፣ አስገዳጅ ሁኔታ ካልገጠመን በስተቀር በተጨናነቀ ባቡር ከመጠቀም መቆጠብ እንደሚገባ ትመክራለች።

ሌላኛዋ ያጋጠማትን ያካፈለችን የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪ የሆነችው ተማሪ ማህሌት ደረጄ ስትሆን፣ ለእሷ ጾታዊ ትንኮሳ ማለት ማንኛውንም ሁኔታ በመጠቀም መጥፎ ሐሳብ ያላቸውን ንግግሮችን በሴቶች ላይ መሰንዘርንም ያካትታል።
እንደ ማህሌት ገለጻ የተለያዩ ጾታዊ ትንኮሳዎች በተለያዩ ቦታዎችና ሁኔታዎች ውስጥ እንዳጋጠማት ትናገራለች። ከዚህም መካከል በባቡር ትራንስፖርት ላይ የሚከሰት ጾታዊ ትንኮሳ በዋናነት ያሳስባታል።
የባቡር ትራንስፖርት ተጠቃሚ ስለሆነች ጾታዊ ትንኮሳው በስፋት ባቡር ውስጥ እንዳጋጠማት ከአዲስ ማለዳ ጋር በነበራት ቆይታ ተናግራለች።

ባቡር ውስጥ በሴቶች ላይ የሚፈጸመው ጾታዊ ትንኮሳ የሚያጋጥመው በብዛት ጠዋትና ማታ ሲሆን፣ የሠራተኞች መውጫና መግቢያ ሰዓት በመሆኑ ከፍተኛ የሆነ መተፋፈግ ስለሚፈጠር ለጾታዊ ትንኮሳ አድራሾች በር መክፈቱን ጠቁማለች።
በብዛት የባቡር ትራንስፖርት ጠዋት ስለምትጠቀም በአንድ ወቅት ከኋላዋ ያለ ምንም ምክንያት ሲተሻሻት ስለነበር ወጣት ልጅ የማትረሳውን ታሪክ ተናግራለች። በትራንስፖርት እጥረቱ ምክንያት በተፈጠረው መጨናነቅ ሳቢያ ወጣቱ ያደርገው የነበረ ድርጊት ከፍተኛ ጫና ስለፈጠረባት መውረድ ከነበረባት ቦታ ሳትደርስ ለመውረድ ተገዳለች።

በወቅቱ ከፍተኛ በሆነ የመረበሽ ስሜት ውስጥ ስለነበረች ምንም አይነት ራስን የመከላከል ተግባር ለመፈጸም እንዳልሞከረች ታስታውሳለች። “በቦታው ብዙ ሰዎች በመኖራቸው ምክንያት ከፈተኛ ድንጋጤ ውስጥ ስለገባሁ፣ ድርጊቱን የፈጸመው ከካል ላይ እርምጃ ከመውሰድ ይልቅ ባቡሩን ለቆ መውጣትን መርጫለሁ” ብላለች።

በወቅቱ የደረሰባት ትንኮሳን ለመከላከል ልጁን ብትናገረው ወይም አካላዊ ዕርምጃ ብትወስድ፣ ልጁ በእርግጠኝነት እንደሚክድ በማመኗ እንደ አማራጭ የወሰደችው ባቡሩን ለቆ መውጣትን ነበር።
የነበረውን ሁኔታ በቦታው ለነበሩ ሰዎች ብናገር ይረዱኛል ብዬ ስላላሰብኩ፣ ራሴ ትክክል ነው ብዬ ያመንኩበትን ፈጽሜ ተጎድቼበታለሁ ብላለች።

ትንኮሳው በስፋት ባቡር ላይ የመታየቱ ዋነኛው ምክንያት በባቡር ትራንስፖርት እየተሰጠ ያለው አገልግሎት አቅም ከሚችለው በላይ በመሆኑ ተሳፋሪዎች ለመቆም በመገደዳቸው ነው። በዚህም ምክንያት ሴቶች ለጾታዊ ትንኮሳ ሰለባ ይሆናሉ።
ባቡር ውስጥ በቂ የሆነ መተላለፊያና መቆሚያ ስለማይኖር መጨናነቅን ይፈጥራል። ይህም በተሳፋሪዎች መካከል መተፋፈግ ስለሚፈጠር ሰዎች ሀኔታውን ለመረዳት ይቸገራሉ።

ማህሌት ከአዲስ ማለዳ ጋር በነበራት ቆይታ የባቡር ትራንስፖርት አገልግሎትን የሚሰጠው ተቋም በሴቶች ላይ የሚደርሰውን ጾታዊ ትንኮሳ ለማስቀረት በሚችለው አቅም ጥረት ቢያደርግ መልካም ነው ብላለች፡
በአዲስ አበባ ከተማ ከፍተኛ የሆነ የትራንሰፖርት እጥረት ከመኖሩ አንጻር ዜጎች ያገኙትን ትራንስፖርት ለመጠቀም ይገደዳሉ። ይህን ችግር የሚመለከተው አካል በጥልቀት ተመልክቶ ተገቢውን መፍትሄ ለማሕበረሰቡ ቢሰጥ፣ በትራንስፖርት አገልግሎት ላይ የሚስተዋሉ ጾታዊ ትንኮሳዎችን ዘላቂነት ባለው መላኩ ለመፍታት እንደሚያስችል ትጠቁማለች።

አሁን ያለንበት ወቅት በዓለማችን ብሎም በአገራችን የኮሮና ቫይረስ በስፋት እየተሰራጨ የሚገኝበት ነው። ይህንን ሁኔታ ከግምት ውስጥ በማስገባት የባቡር ትራንስፖርት አገልግሎት ሰጪው በባቡር ላይ የሚስተዋለውን የተሳፋሪ ቁጥር መቀነስ እንዳለባቸው ታስረዳለች።
በአጠቃላይ እንደባቡር ትራንስፖርት ተጠቃሚ ሴቶች አረዳድ፣ ጾታዊ ትንኮሳ የባቡር አገልግሎት በሚጠቀሙ ብዙ ሴቶች ላይ በየዕለቱ ማለት በሚቻል ሁኔታ የሚከስት የሕይወት ገጠመኝ መሆኑን አስረድተዋል።
አስተያየት ሰጭ ሴቶች የባቡር ትራንስፖርት በሚጠቀሙበት ወቅት ስለሚያጋጥሟቸው ጾታዊ ትንኮሳዎች ለማን አቤት ማለት እንደሚችሉ ባለማወቃቸውም መቸገራቸውን ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል።
ከዚህ ቀደም በዚህ ሁኔታ በሴቶች ላይ ጾታዊ ትንኮሳዎችን ያደረሱ ሰዎች ላይ ቅጣትም ሆነ ማስጠንቀቂያ ተሰጠ ሲል ባለመሰማቱ የሚጋጥማቸውን ትንኮሳ ለሚመለከው አካል የማቅረብም ፍላጎት የላቸውም።

በርግጥ ጾታዊ ትንኮሳዎችን ለማስቀረት በባቡር ትራንስፖርቶች ላይ ጾታዊ ትንኮሳን የሚመለከቱ የማስተማሪያ ወረቀቶች ተለጥፈዋል። ነገር ግን ይህ ብቻውን በቂ ሊሆን አይችልም። ምክንያቱም ከዚህ በተሻለ መልኩ ትንኮሳ በሚያደርሱ ሰዎች ላይ እንደየ ድርጊቱ ክብደት ማስጠንቀቂያ ወይም ቅጣት መስጠት ስለሚያስፈልግ ነው ብለዋል።

በመጨረሻም አስተያየት ሰጪዎቹ ማንኛውም አይነት ጾታዊ ትንኮሳን ለመከላከል እራሳቸውን መጠበቅ አስፈላጊ አንደሆነ ተናግረዋል። ከዚህ አንጻር የተጨናነቀ የባቡር ትራንስፖርት አለመጠቀም አንዱ መፍትሔ መሆኑን ይገልጻሉ።
ከዚህ ጋር በተያያዘ በሴቶች፣ህጻናትና ወጣቶች ሚኒስቴር የሕግ ጉዳዎች ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ደረጄ ጠግይበሉ በበኩላቸው፣ ስለ ጾታዊ ትንኮሳ እንዲሁም ትንኮሳው በደረሰባቸው ሴቶች ዙሪያና ቀጣይ ስለታቀደው የሕግ ማሻሻያ በስፋት ሐሳባቸውን ለአዲስ ማለዳ አካፍለዋል።

የአንድን ሰው አካል ያለፈቃዱ መንካት በወንጀል ያስጠይቃል። ነገር ግን ጾታዊ ትንኮሳ ብለን መናገር አንችልም ብለው ተናግረዋል።
ጾታዊ ትንኮሳ እራሱን ችሎ በወንጀል ሕጋችን ባለመቀመጡ፣ ትንኮሳ ፈጻሚው አካል በሕግ የሚጠየቅበት ሁኔታ አለመኖሩን ገልጸዋል።
በትራንስፖርት አገልግሎት ላይ ጾታዊ ትንኮሳን የሚያደርሱ ሰዎች የሴቶችን አካል ያለ ፈቃድ በመንካት ወይም ጾታን መሰረት ያደረገን ሐሳብ መሰንዘር ብሎ በሕግ መጠየቅ ይቻላል እንጂ፣ በጾታ ትንኮሳ የሚጠየቁበት አዋጅ አለመኖሩን ጠቁመዋል።
ከአገራችን ሕግ መካከል አንዱ ክፍተት ይህ በመሆኑ ለወደፊት በስፋት እየተሠራ መሆኑን ዳይሬክተሩ ከአዲስ ማለዳ ጋር በነበራቸው ቆይታ ተናግረዋል። ‹‹ይህ ጉዳይ የሴቶች፣ህጻናትና ወጣቶች ሚኒስቴርን ባይመለከትም፣ ሴቶች መጓጓዣዎችን በሚጠቀሙበት ወቅት ይህ አይነቱ ድርጊት ሲያጋጥማቸው በአቅራቢያችው ወደሚገኝ የሕግ አካል በመሄድ መጠቆም ይገባቸዋል›› ብለዋል።


ቅጽ 3 ቁጥር 141 ሐምሌ 10 2013

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com