የእለት ዜና

የመፍትሔ ሐሳቦች ትኩሳት የሆኑበት መተከል

Views: 43

በቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል መተከል ዞን ከአንድ ዓመት በላይ በዘለቀው ተደጋጋሚ ጥቃት ከዜጎች መፈናቀልና ንብረት መውደም ጀምሮ እስከ ንጹሐን ሰዎች ሕልፈት ሕይወት በዞኑ ኗሪዎች ላይ ተከስቷል። በዞኑ በተፈጠረው የጸጥታ ችግር ከሞት የተረፉ ዜጎች፣ በተለያየ ጊዜ ተፈናቅለው ለወራት ሕይወታቸውን በመጠለያ ጣቢያ ለመግፋት ተገደዋል። ከ50 ሺሕ በላይ ተፈናቃዮች አሁንም ሕይወታቸውን በመጠለያ ጣቢያ እየመሩ ይገኛሉ።

በዞኑ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰ የመጣውን የንጹሀን ዜጎች ግድያና መፈናቀል ተከትሎ የፌደራል መንግሥት ከመስከርም 11/2013 ጀምሮ አካባቢው በኮማንድ ፖስት እንዲመራ አድርጓል። በዞኑ የተፈጠረውን የጸጥታ ችግር ምክንያት አድርጎ የተቋቋመው የዞኑ ኮማንድ ፖስት ሥራውን ከጀመረበት ጊዜ ጀምሮ እስካሁን ዞኑን እያሥተዳደረ ይገኛል። በኮማንድ ፖስት እየተዳደረ የሚገኘው መተከል የንጹሐን ዜጎች ግድያና መፈናቀልን አሁንም እያስተናገደ ይገኛል።

ዞኑን በማሥተዳደር ላይ የሚገኘው ኮማንድ ፖስት ችግሩን ለመፍታት መፍትሔ ይሆናሉ ያላቸውን ተግባራት ሲያከናውን ቆይቷል። እንደ መፍትሔ ከተወሰዱ ተግባራት መካከል የመጀመሪያው ታጥቀው የሚንቀሳቀሱ ኃይሎችን ወደ ሰላም እንዲመጡ ማድረግ የነበረ ሲሆን፣ በዚህም ታጥቀው ወደ ጫካ የገቡ አካላትን የተሃድሶ ስልጠና መስጠቱን ኮማነድ ፖስቱ በተደጋጋሚ ሲገልጽ ነበር።

በተጨማሪም ለችግሩ መፍትሔ ይሆናል ተብሎ የታሰበው የተሃድሶ ስልጠና ወስደዋል የተባሉ አካላትን ሹመት መስጠት ይገኝበታል። የተሃድሶ ስልጠና ከወሰዱ ሰልጣኞች መካከል ለ25ቱ ግለሰቦች ሹመት መስጠቱን የክልሉ መንግሥት ሰኔ 27/2013 መግለጹ የሚታወስ ነው። የክልሉ መንግሥት በታጣቂዎች በኩል የተነሳውን ጥያቄ መሰረት በማድረግ ቃል በተገባው መሰረት ለ25 አመራሮች ሹመት ሰጥቶ ነበር። ሹመቱም በወረዳ 16፣በዞን ደረጃ 3 እና በክልል ደግሞ 2 ግለሰቦች ያካተተ መሆኑ ተገልጿል።

በመተከል ዞን የተፈጠረውን አለመረጋጋት በዘላቂነት ለመፍታት ይረዳል የተባለለት በኹለተኛ ዙር ስልጠና የወሰዱ የታጠቁ ኃይሎች ተመርቀዋል ተብሏል። በሌ/ጀኔራል አስራት ዴኔሮ የሚመራው የዞኑ ኮማንድ ፖስት በታጣቂ ኃይሎች በኩል የተነሱ መሰረታዊ ጥያቄዎችን ለመፍታት ስምምነት በተደረሰው መሰረት መፍትሔ ለመስጠት ጊዜያዊ ጽህፈት ቤት ተቋቁሞ እየተሰራ እንደሆነም ገልጿል።

ለኹለተኛ ዙር የተሃድሶ ስልጠና የወሰዱ 1 ሺሕ 633 የታጠቁ ኃይሎች መመረቃቸው ሹመት በተሰጠበት ዕለት ተገልጿል። የተሃድሶ ስልጠናው ለሦስት ሳምንት የተሰጠ መሆኑም ተመላክቷል። 106 ለሚሆኑ የሰላም ጥሪን ተቀብለው የተሃድሶ ስልጠና ለወሰዱ ሰዎች 530 ሄክታር መሬት ለመስጠት ዝግጅት እየተደረገም ነው ተብሏል።

ኮማንድ ፖስቱ መፍትሔ ይሆናሉ ያላቸውን ተግባራት ቢያከናውንም፣ በዞኑ የሚፈጸመው ጥቃት እሰካሁን ድረስ አልቆመም። ባሳለፍነው ሳምንት በዞኑ በቡለን ወረዳና በአካባቢው የጸጥታ ችግሮች እንደተከሰቱ የወረዳው አስተዳደር ገልጿል። ይህንኑ መነሻ በማድረግ ኮማንድ ፖስቱ በወረዳው ክልከላዎችን አሰተላልፏል። ከተላለፉት ክልከላዎች የሰዓት ዕላፊ አንዱ ነው።

አዲስ ማለዳ ከዚህ ቀደም በሠራቻቸው ዘገባዎች በዞኑ መፍትሔ ያመጣል ተብሎ የተጠበቀው የታጣቂ ኃይሎች የተሃደሶ ስልጠና አስተማማኝ አለመሆኑን እና የተሃድሶ ስልጠና ወስደው የተመለሱ አካላት ጥቃቶችን እየፈጸሙ መሆኑን ከኗሪዎች አረጋግጣ መዘገቧ የሚታወስ ነው። በዞኑ በተፈጠረው የጸጥታ ችግር ተፈናቅለው የነበሩ ዜጎች በቅርቡ ወደ ቀያቸው መመለሳቸው የሚታወስ ነው። ይሁን እንጅ የተሃድሶ ስልጠና የወሰዱ የታጠቁ ኃይሎች ጥቃቶችን እየፈጸሙና ተመልሰው ወደ ጫካ እየገቡ እንደሆነ በዞኑ በመጠለያ ካምፕ የሚገኙ ዜጎች ተናግረዋል።

በዞኑ አሁንም ድረስ የጸጥታ ችግሩ እንዳልተቀረፈ የሚገልጹት ተመላሾቹ፣ ኮማንድ ፖስቱ ተፈናቃዮች የተጠለሉባቸውን የካምፕ አከባቢዎች በከፍተኛ ጥንቃቄና በንቃት መከታተል እንዳለበት አሳስበዋል። ከፍተኛ ጥንቃቄ እንደሚያስፈልግ ያሳሰቡት ተመላሾቹ፣ የተሃድሶ ስልጠና የወሰዱ አካላት ወደ ቀድሞ ተግባራቸው የመመለስ አዝማሚያ ውስጥ መሆናቸውን አስተውለው እንደሆነ ጠቁመዋል።

የዞኑን የጸጥታ ሁኔታ በንቃት የሚከታተለው በክልሉ የሚንቀሳቀሰው ቦሮ ዴሞክራቲክ ፓርቲ በጉዳዩ ላይ ባሳለፍነው ሳምነት ሐምሌ 4/2013 መግለጫ አውጥቷል። ፓርቲው በመግለጫው “በመተከል ዞን ባለፈው አንድ ዓመት በተፈጠረው ማንነትን መሰረት ያደረገ ጅምላ ጭፍጨፋ በዜጎች ላይ ሞት፣ መፈናቀልና የንብረት ውድመት ተከስቷል። አሁንም ሙሉ በሙሉ ያልቆመው ግድያ በዞኑ ነዋሪዎች ላይ ከፍተኛ የሆነ ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊና ሥነልቦናዊ ጫና አሳድሯል” ብላል።

ፓርቲው በመግለጫው የክልሉ መንግሥት ሰላምና መረጋጋትን ለማስፈን ከታጣቂ ቡድኑ ጋር የሰላም ስምምነት ከፈጸመ በኃላ የተሟላ ሰላም ይሰፍናል ብሎ ሕዝቡ ተስፋ ያደረገ ቢሆንም፣ አሁንም ችግሩ እንዳልተፈታ ገልጿል።
በመተከል ዞን እየተስተዋለ ያለውን ወቅታዊ ሁኔታ በጥልቀት የገመገመው የፓርቲው ሥራ አስፈጻሚ፣ የሰላም ጥሪ ተደርጎ ፈቃደኛ ለሆኑት የተሃድሶ ስልጠና እንዲሰጥ መደረጉ ተገቢነት ያለውና የመንግሥትን ሆደ ሰፊነት የሚያሳይ ቢሆንም፣ አሁንም ግን ግድያና የንብረት ዝርፊያው መቆም አልቻለም ብሏል። በመሆኑም ከተሃድሶ ስልጠና በኋላ የሠልጣኞቹ ቀጣይ እንቅስቃሴና የኑሮ ሁኔታ ክትትል የሚደረግበት ጥብቅ ሥርዓት እንዲዘረጋና የኮማንድ ፖስቱ ሕግን የማስከበር ተግባር ሳይላላ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ፓርቲው አሳስቧል።
ፓርቲው ኗሪዎች ለአዲስ ማለዳ የገለጹትን ሐሳብ የሚያጠናክር ሀተታም በመግለጫው አካቷል። ይሄውም “አንዳንድ በተሃድሶ ስልጠናው ከጥፋት ተግባራቸው ያልተመለሱና ከነትጥቃቸው ወደ ማሕበረሰቡ የተቀላቀሉ የጥፋት ኃይሎች፣ አሁንም በግድያና በዘረፋ ተግባራቸው በመቀጠል ለሕዝባችን ስጋት ሆነው ቀጥለዋል” ማለቱ ነው።

በመሆኑም የተሰጣቸውን ዕድል እንደ ሽንፈት የሚቆጥሩና ከነትጥቃቸው የተለቀቁ የጥፋት ኃይሎች ባአስቸኳይ ትጥቅ እንዲፈቱ ወይም በኮማንድ ፖስቱ ጥብቅ ቁጥጥር እንዲደረግባቸው ፓርቲው አሳስቧል። ለታጣቂ ኃይሎች የሚሰጠው ስልጠና ውጤት ማምጣቱ ጥርጣሬ ውስጥ እየከተተው የመጣ መሆኑን የገለጸው ፓርቲው፣ በሕዝቡ ላይ እየደረሰ ያለው ግድያና ዝርፊያ ያልቆመ በመሆኑ በአስቸካይ እንዲቆም፣ ኮማንድ ፖስቱም ሕግ የማስከበር እርምጃ እንዲወስድ ጠይቋል።

የመተከል ዞን ሕዝብ በጥፋት ኃይሎች የሚደርስበትን ትንኮሳና ጥቃት ከኮማንድ ፖስቱ ጋር በመተባበርና አጋዥ መረጃ በመስጠት ለመመከት በትጋት ከመሥራት ባለፈ፣ በምንም ምክንያት ከሰላማዊው የጉሙዝ ማሕበረሰብ ጋር መጋጨት ተገቢ አለመሆኑን በመረዳት ለአካባቢው ሰላም የበኩሉን አስተዋጽኦ እንዲያበረክት ቦዴፓ ጥሪ አቅርቧል።

የተፈናቀሉ ዜጎች አሁንም ድረስ ወደ ቀያቸው እንዳልተመለሱና የግብርና ሥራ እንዳልጀመሩ ፖርቲው ጠቁሟል። አዲስ ማለዳ ያነጋገረቻቸው ተፈናቃዮች ፓርቲው እንዳለው እርሻ ሥራቸውን ለመከወን የሚያስችል ሁኔታ የለም ብለዋል። በመሆኑም የክረምት የግብርና ሥራ ከማለፉ በፊት ሁሉም ተፈናቃይ ቀደም ሲል ወደነበረበት ቀየው እንዲመለስና ተረጋግቶ የግብርና ሥራውን እንዲጀምር እንዲደረግ ሲል ቦዴፓ ጠይቋል።

ተፈናቃዮች ወደ ከመፈናቀላቸው በፊት ወደ ነበሩበት ወረዳ ቢመለሱም፣ በዞኑ ያለው የጸጥታ ችግር አስተማማኝ ባለመሆኑ፣ በአንድ ላይ ተከማችተው በካምፕ ውስጥ ከመኖር ውጭ ወደ ቀድሞ ቦታቸው ተመልሰው የእርሻ ሥራ መሥራትና መንቀሳቀስ እንደማይችሉ ነው የገለጹት። በዚሁ ምክንያት ተፈናቃዮች በሰፈሩበት አካባቢ ያልታረሱ መሬቶችን በጋራ እንዲያርሱ ዕቅድ ቢኖርም፣ የጋራ እርሻ ከመሆኑ በላይ ለውጥ የማያመጣ መሆኑን ተፈናቃዮች ጠቁመዋል።

በዞኑ በተፈጠረው የጸጥታ ችግር በንጹሐን ዜጎች ላይ በደርሰው ጉዳት ቤተሰቦቻቸውን በሞት ላጡት፣ የንብረት ውድመትና የዘረፋ ጉዳት ለደረሰባቸው ዜጎቻችን ገለልተኛ አጣሪ አካል ተዋቅሮና እያንዳንዱን የጉዳት መጠንና አይነት አጣርቶ በዘላቂነት እንዲቋቋሙ እንዲደረግ ፓርቲው ጠይቋል። በዚህ ጉዳይ ላይ ከዚህ ቀደም ከአዲስ ማለዳ ጋር ቆይታ ያደረጉት የቦዴፓ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ መብራቱ አለሙ(ዶ/ር) በተደጋጋሚ በደረሰው ጥቃት ተጎጅ የሆኑ ዜጎች ካሳ ሊከፈላቸው እንደሚገባ ጠቁመው ነበር።
በክልሉ በመተከል እና ካማሽ ዞን በተፈጠረው የጸጥታ ችግር ምክንያት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሰኔ 14/2013 በተካሄደው ምርጫ ዞኖቹን እንዳላካተታቸው የሚታወስ ነው። በመሆኑም የኹለቱ ዞኖች ምርጫ በቀጣይ ጳጉሜ 1/2013 በሚካሄደው ኹለተኛ ዙር ምርጫ የሚደረግ በመሆኑ ከወዲሁ አካባቢውን ለምርጫ ምቹ ለማድርግ ኮማንድ ፖስቱና የፌደራል መንግሥት አስፈላጊውን እርምጃ እንዲወስዱ ቦዴፓ ጠይቋል።


ቅጽ 3 ቁጥር 141 ሐምሌ 10 2013

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com