የእለት ዜና

የሴቶች የጎዳና ሕይወት

Views: 22

ብዙ የጎዳና ተዳዳሪዎች ከሚኖሩባቸው የኢትዮጵያ ከተሞች መካከል አዲስ አበባ አንዷ ናት። በከተማዋ ጎዳናዎች ላይ የሚኖሩ ሴት ሕፃናትና እናቶች ቁጥርም በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ መምጣቱ ይታወቃል። በሚያጋጥሟቸው አስከፊ ችግሮች ምክንያት ከአጎራባች ክልሎች የሚመጡ ሴቶች ወደ ጎዳና ሕይወት ለመግባት ይገደዳሉ።
በአዲስ አበባ በተለያዩ አካባቢዎች ማለትም በብሔራዊ፣ ለገሃር፣ ስታዲየም፣ ፒያሳ፣ ቦሌና መርካቶ እንዲሁም በተለያዩ የከተማዋ የትራፊክ መብራቶች በሚገኙባቸው ስፍራዎች ላይ የሚታዩት የጎዳና ተዳዳሪዎች በርካታ ናቸው፡፡ ሕፃናትና ወጣት ሴቶች በተለይም እናቶች ልጅ ይዘው በጎዳናው ላይ የሚተላለፉ መኪናዎችንና እግረኞችን በመከተል እርዳታ ሲጠይቁ ይስተዋላል።
በብዛት ይህንን ድርጊት የሚፈጽሙት ወጣት ሴቶች እና የመማር ብሎም የመሥራት አቅም ያላቸው ግለሰቦች ናቸው።
በአዲስ አበባ ዋና ዋና መንገዶች ላይ ኑሮአቸውን መስርተው ለመኖር የተገደዱ የጎዳና ተዳዳሪ ሴቶች ለዚህ ሕይወት ከዳረጓቸው ምክንያቶች መካከል በስፋት የሚጠቀሱት የቤተሰብ መለያየት፣ እናትና አባትን በሞት ማጣት፣ ሥራ ለማግኘት የሚደረግ ፍልሰት፣በቤተብ መካከል የሚፈጠር ጸብ ተጠቃሽ ናቸው።
በሌላ በኩል፣ ሴቶች የተሻለ ዕድል ለማግኘት ወደ ከተማ ይመጣሉ፤ ነገር ግን የሚገጥማቸው ሕይወት በተቃራኒው ይሆናል። የተሻለ ትምህርትና ሥራ ማግኘት ቀርቶ ያለዕድሜያቸውና በመማሪያ ጊዜያቸው የልጅ እናት ለመሆን ይገደዳሉ። አንዳንዶቹ የጎዳና ተዳዳሪ ሴቶች በ ጎዳና ላይ በሚያጋጥማቸው እርግዝና ልጃቸውን ያለ ማንም እርዳታ ይወልዳሉ።
ከዚህ ጋር በተያያዘ እንደ ማሳያ የምትሆነው ጎዳና ላይ ኑሮዋን መስርታ የነበረችው ጠይባ ናት። የዕለት ጉርሷን ለማግኘት ወደ አዲስ አበባ ከተማ የመጣችው ጠይባ ያልጠበቀችው ችግር በመፈጠሩ ብዙ የመከራ ጊዜያትን ነፍሰ-ጡር ሆና አሳልፋ ነበር። በጎዳና ላይ ብቻዋን ያለ ማንም እርዳታ ልጇን በሰላም የተገላገለች ቢሆንም፣ ከዛ በኋላ ግን ሁኔታውን ለመቋቋም አልቻለችም ነበር። እንደእሷ አይነት ኑሮአቸውን ጎዳና ላይ ያደረጉ ሴቶች ለከፍተኛ ረሀብ፣ ጭንቀትና መደፈር ይጋለጣሉ፡፡
በዚህም ምክንያት ኑሯቸው በችግር የተሞላ፣ የጭንቅና የመከራ ይሆናል። ሕይወታቸውን በጎዳና ላይ የመሰረቱ ታዳጊ ሴቶች የሚደርስባቸውን የማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ሥነ ልቦናዊ ጉዳት ለመርሳት እና በተለይም ብርዱን ለመቋቋም በእጃቸው ማስቲሽ ሸጉጠው ጠዋትና ማታ እየሳቡ ማየት እየተለመደ መጥቷል።
በሕይወታቸው የተከሰተውን ሁሉን ለመርሳት በሱስ ውስጥ መኖርን ይመርጣሉ። ሴት ሕፃናትና ወጣቶች ማስቲሽ፣ ቤንዚን፣ የመኪና ጭስ፣ ቀለምና ሌሎችንም ያሸታሉ፤ይስባሉ፡፡ ይህ አይነቱ ድርጊት ለጤና መቃውስ ያጋልጣቸዋል። አሁን ያለንበት ወቅት ክረምት በመሆኑም ከፍተኛ የሆነ ዝናብና ብርድ የጎዳናን ኑሮን እጅግ ያከብደዋል።
በአገራችን የሴቶች የጎዳና ኑሮን ለመቀነስ ኹሉም ባለ ድርሻ አካላት የሚቻላቸውን ማድረግና ሕወታቸው እንዲለወጥ መረባረብ ግድ ይላቸዋል፡፡


ቅጽ 3 ቁጥር 141 ሐምሌ 10 2013

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com