የእለት ዜና

“አሸባሪ የሆነን አካል መታገሱ ዋጋ አስከፍሎናል”

Views: 38

ተስፋሁን አለምነህ ይባላሉ። የአማራ ዴሞክራሲያዊ ኃይል ንቅናቄ ሊቀመንበር ሆነው በዘንድሮው ምርጫ ተሳትፈዋል። በፖለቲካው ዓለም ውስጥ መሳተፍ የጀመሩት ከ1997ቱ ምርጫ ወዲህ ነው። የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት የሕዝብ ግንኙነት ሆነው እስከ 2006 ቆይተዋል። ሠላማዊ ትግሉ እንደማያዋጣም ተረድተው በዓመቱ መጨረሻ ወደ ኤርትራ በረሃ ወርደው የትጥቅ ትግሉን እስከ2011 ዘልቀውበታል። በመንግሰት ጥሪ ከተደረገ ወዲህ ወደ ሃገር ውስጥ በመግባት ሰላማዊ የፖለቲካ ትግሉን ተቀላቅለዋል። ያዋጣል ባሉት መንገድ ሕወሓት መራሹን መንግስት ሲታገሉ የነበሩት እኚህ ፖለቲከኛ ስለወቅታዊው የሰሜኑ ፖለቲካ ከአዲስ ማለዳው ቢኒያም ዓሊ ጋር ቆይታ አድርገዋል።

አጠቃላይ የሰሜኑን ዘመቻ ሂደት እንዴት ያዩታል?
እሱን ኹሉም ኢትዮጵያዊ እንደሚረዳው፣ ላለፉት አመታት የህወሓት ቡድን በኢትዮጵያ ውስጥ አድራጊ ፈጣሪ ሁኖ፣ ጸረ-አማራ እና ጸረ-ኢትዮጵያ አቋም ሲያራምድ ነው የነበረው። በኋላ ከማዕከላዊ መንግሥት ከተገፋ በኋላ አሁን መልሶ ለመስፋፋት በማሰብ የሚያደርጋቸውን ነገሮች ነው እያየን ያለነው። ይህ ደግሞ የውስጥም የውጭም ጠላቶች በአንድም ይሁን በሌላ መንገድ እየገቡበት የኢትዮጵያ አንድነት ላይ የተቃጣ ጥቃት ነው። በተለይም የውጭ ኃይሎች ድጋፍ እያደረጉ ባሉበት ሁኔታ ጦርነቱ እየቀጠለ ነው ያለው።

ከጦርነቱ መነሻ ጀምሮ መከላከያ እስከወጣበት ጊዜ ያለውን ሂደት እንዴት ይገመግሙታል?
ጦርነቱ የተራዘመ ጦርነት ነው፤ በእኛ እምነት ህወሓትን ለማጥፋት እና ህወሓት አቅም እንዳይኖረው የሚደረግን ጦርነት ስንደግፍ ቆይተናል። መደገፍ ብቻ ሳይሆን በዚያ ሂደት ውስጥ ማድረግ የሚገባንን ነገር በቻልነው አቅም አድርገናል። ነገር ግን፣ አሁን ያለውን በግልጽ ለማስቀመጥ ያህል፣ ጦርነቱን የኹለት ክልሎች እንደሆነ አይነት አድርጎ የማስመሰል አይነት አዝማሚያ አለ። ይሄ በፍጹም ተቀባይነት የለውም፤ ህወሓት ለሁሉም አካል ጠላት ነው። በእኛ እምነት የኢትዮጵያ ሕዝብ ኹሉ ጠላት ነው። በተለየ ሁኔታ የአማራን ሕዝብ ፈርጆ ቢነሳም፣ ማዕከላዊ መንግሥቱን ተቆጣጥሮ በነበረበት አመታት በርካታ ግፍ አድርሷል። ስለዚህ ጦርነቱ ከጅምሩ የነበረው በዛ ስሜት ነው የነበረው። ዞሮ ዞሮ ግን ጦርነትን ለሆነ አካል ገፍተህ የምተወው አይደለም። ለኹላችንም የህልውና ጦርነት ነው። በግልጽ በአማራ ሕዝብ ላይ ሂሳብ እናወራርዳለን ብሎ ህወሓት ተነስቷል። በእኛ በኩል፣ ይህ ማለት ለህልውናችን ስንል የምንገባበት ጦርነት ነው። ስለዚህ ለእገሌ ለእገሌ ተብሎ የሚሰጥ አይነት ጦርነት አይደለም። ምንም ይሁን ምን ይሄን የህልውና ጦርነት መቀልበስ ነው ዋናው ዓላማችን። ከሁሉም በዋናነት መታወቅ ያለበት ቡድኑ የአማራ ሕዝብ ላይ ሂሳብ እናወራርዳለን ብሎ መነሳቱን በግልጽ ማስቀመጥ ያስፈልጋል። ይሄንንም ዕቅዱን መቀልብስ እንዳለብን በኛ በኩል እምነት ወስደን እንቅስቃሴ ጀምረናል።

መከላከያ የወጣበትን ሂደት እንዴት ታዩታላችሁ?
በእኛ እምነት መከላከያ በእንደዚያ አይነት ሁኔታ ጥሎ መውጣቱን አንደግፍም። ብዙ ዋጋ ያስከፍላል የሚል ጥቅል ግምገማ ነው ያለን። መከላከያ በውጭ ጫናም ሆነ በምንም ምክንያት በቦታው እያለ ማዕከላዊ መንግሥት የሚያስቀምጠው ነገር አለ። ዞሮ ዞሮ ግን እኛ መከላከያ የወጣበትን መንገድ አንደግፈውም።

የሰፈሩበትን ቦታ እና አካባቢ እንዴት ታዩታላችሁ? በምንስ የተመረጠ ይመስላችኋል?
እሱ ውሳኔ ስትራቴጂካዊ ሊሆን ይችላል። ምናልባት እነሱ ያዩበት የተለየ ወታደራዊ አንግል ሊኖር ይችላል። እኔ እያልኩት ያለሁት ፖለቲካዊ አንድምታውን ነው። በአንድም ሆነ በሌላ መንገድ ወታደራዊ የበላይነት ተወስዶብን ከሆነ ማጥቃትና ማስለቀቅ ያለ ነገር ነው። ነገር ግን፣ ሙሉ በሙሉ አቅም እያለ፣ ችሎታው እያለና መቆጣጠር እየተቻለ ዳግም እንዲያንሰራሩ መደረጉ ተገቢ ነው ብለን አናምንም። ይህ ደግሞ የውጭ ፖለቲካዊ ጣልቃ ገብነት እንዳለ ያሳያል።

የኢትዮጵያ መንግሥትንም አጣብቂኝ ውስጥ በማስገባት መሪ እንደ መሪ የሚፈተንበት አጣብቂኝ ሰዓት ላይ እንገኛለን። ይሄኛው ዋጋ ከሚከፈል ይሄ መስዋዕትነት ይሻላል በሚል እንደማሲያዢያ መጠቀም ተገቢ ነው ብለን አናምንም። በአሁኑ የህወሓት ጦርነት ቀጥተኛ ተጎጂው የአማራ ሕዝብ ነው። ተጎራባችም ስለሆነ በዋናነትም ደግሞ እንደ ዶክትሪኑም የአማራን ሕዝብ ማዕከል አድርጎ ስለሚነሳ ተጎጂው የታወቀ ነው። ስለዚህ የመከላከያ ሠራዊት መቀሌንም የለቀቀው የመከላከያ ሠራዊት አመራሮች በሚሉት አግባብ ነው ብለን አናምንም። ምንም ይሁን ምን የሆነን ሕዝብ ለአደጋ እያጋለጥክ መውጣት ተገቢ ሊሆን አይችልም።

የህወሓት ኃይል ወደዚህ ሲመጣ የሚያሰለልፋቸው ኃይሎች ዓለም አቀፍ የጦር ወንጀለኝነት ሕጎችን እጅግ የሚጻረሩ ናቸው። በአደንዛዥ ዕጽ አእምሯቸውን እያሳተ፣ እያስገደደና እያታለለ ነው ጦርነት ውስጥ የሚማግዳቸው። ጥቃት በሚፈፅሙበት አካባቢ የሚኖርን ተራ ሕዝብ እየገደሉ ነው የሚንቀሳቀሱት። የማይካድራው ብቻ አይደለም ከዛ ሲመጡ በየደረሱበት እየገደሉ ነው የሚመጡት። ይሄ ባለበት ሁኔታ ሰንካላ ምክንያት አቅርበህ ከማስወጣት ይልቅ፣ በአገር መከላከያ ሠራዊት መከፈል ያለበት ዋጋ ሁሉ መከፈል አለበት። አሸባሪ የሆነን አካል መታገሱ ዋጋ አስከፍሎናል የሚል እምነት አለን።

የህወሓት ኃይሎች በጦርነት ሳይሆን በፕሮፓጋንዳ አሸንፈዋል ይባላል። በዚህ ጉዳይ ላይ እርስዎ ምን ይላሉ?
በጦር ሜዳማ እንደማያሸንፉ የታወቀ ነው። ፖለቲካዊ አሻጥር ነው እንጂ በጦርነትማ እንደማያሸንፉ የታወቀ ነው። ከነበሩበት ሥልጣን ሲለቁ የአማራ ልዩ ኃይልና የመከላከያ ሠራዊት ያደረገው ተጋድሎ አለ። የእነሱ ፖለቲካዊ አሻጥርና የተጋነነ ፕሮፓጋንዳ ጩኸት በግልጽ ይታወቃል። አሜሪካ ስቴት ዲፓርትመንት ሲንከባለሉ ይታያሉ። “ተገደልን” እያሉ ሲያለቅሱ ከቆዩ በኋላ የሆነ ቀን ላይ ደሞ እኛ ነን አድራጊ ፈጣሪዎችና የጦር መሃንዲሶች እያሉ እነሱ ብቻ ተዋጊዎች እንደሆኑ አድርገው ፕሮፓጋንዳ ይለቃሉ። ይህንን ሚዛናዊ ሆነን ብናየው ፕሮፓጋንዳ ነው። ነገር ግን ፕሮፓጋንዳ የጦርነት አካል ነው፤በፕሮፓጋንዳ የተሰለበ ኃይል ውጤት ያመጣል ተብሎ አይታሰብም። በአገራችን እኮ ትልቅ አባባል አለ፤ “ጦር ከፈታው ወሬ የፈታው” ይባላል። ይሄንን አካሄድ በደንብ ያውቁታል። ከጅምሩ ቅጥፈት ነው የለመዱት። አይደለም አሁን ዓለም አቀፍ ሚዲያዎችን ይዘውና የሚመስል ነገር እየታየ፣ እንዲሁ ዝም ብለው በማታለል የታወቁ ናቸው።

ስለዚህ ፕሮፓጋንዳውን መቀልበስ ይቻላል። ይህም የሚቻለው ሃቀኛውን መንገድ በማሳየት ነው። አሁን ባሉበት መንገድ ፓርላማው ሽብርተኛ ብሎ ፈርጇቸዋል። እነዚህ ሽብርተኛ ኃይሎች ጋር ደግሞ ምንም አይነት ድርድር የለም። ለአንዴ እና ለመጨረሻ ጊዜ እስካልጠፉ ድረስ የአማራ ሕዝብ ምንም ሠላም አያገኝም። የኢትዮጵያ ገጽም ተጠብቆ አይቆይም።

እሾህን በእሾህ በሚለው መርህ የእነሱን ፕሮፓጋንዳ በተመሳሳይ ፕሮፓጋንዳ ማሸነፍ ይቻላል የሚሉ አሉ። ስለዚህስ የሚሉት አለ?
አንደኛ ነገር ከእነዚህ ኃይሎች ጎን የቆሙ ኢትዮጵያ አሁን ካላት ፖለቲካዊ አቀማመጥና ከአባይ ግድብ ጋር ተያይዞ የኢትዮጵያን አንድነት የማይፈልጉ ናቸው። ይህ በግልጽ ይታወቃል። እነዚህ ኃይሎች የፕሮፓጋንዳ ሚናውንም እየተጫወቱ ነው ያሉት። ይህን በሚመጥን መንገድ ደግሞ እየተካሄደ አይደለም። ከዛ ባለፈ በውስጥ ጉዳያችን ገብተው እጃቸውን አስረዝመው ለመፈትፈት ይፈልጋሉ። ይህንን ለማስተካከል በሚደረገው ጥረት ውስጥ ደግሞ እነሱም ይገቡበታል። ይብዛም ይነስም የማዕከላዊ መንግሥቱን ይዘው ሲቆጣጠሩ የነበሩ ኃይሎች ናቸው። እነዚህ ኃይሎች መንግሥት በነበሩበት ወቅት የሆነ ዲፕሎማሲ ሠርተዋል። የውጭ ኃይሎች ያላቸው ፍላጎት ሲደማመር የተወሰነ ጫና ያመጣል።

ከውስጥ አለ ያሉትን አሻጥር ቢያብራሩት?
እንግዲህ የፖለቲካ አሻጥር በአንድም ይሁን በሌላ መንገድ ይህ ነው የምልህ አይደለም። በግልጽም እንደሚታየው አንዴ ግባ አንዴ ውጣ፣ እንደዚህ ነው እንደዛ ነው የሚል ኢትዮጵያንም ሠላም የማያደርግ፣ የአማራንም ሕዝብ የተገዢነት ስሜት እንዲሰማው የሚያደርግ ነው። የፖለቲካ አሻጥር ሁሌም ይኖራል። አንደኛ በዚህ ሂደት ውስጥ የራሳቸውን የፖለቲካ የበላይነት ለማግኘት የሚፈልጉ የፖለቲካ ኃየሎች ይኖራሉ። ስለዚህ ከዚህ አንጻር የአማራ ሕዝብ ተጎራባች ይሁን እንጂ ጦርነቱ የአማራ ብቻ አይደለም። ነገር ግን የአማራ ብቻ በማስመሰል አሁን በውጭ አገራት አማራን ወራሪ የማስመሰል ነገር ይታያል።

ይህን ደግሞ እንደ ፖለቲካ ካርድ የሚመዙት አንዳንድ ኃይሎች አሉ። ይህንንም በመጠቀም የውጭን ጫና ለመቀነስ የሚደረግ ጥረት አለ። ይህንን አሻጥር ፖለቲካዊም እንበለው ወታደራዊም ፕሮፓጋንዳም ብንለው አሁን ያለንበት ሁኔታ የህልውና ጦርነት ውስጥ ነው።
ይህንን የህልውና ችግር ደግሞ የእገሌ የእገሌ ብለን የምንተወው አይደለም። የአማራ ብልጽግናም ሆነ ሌሎችም የፖለቲካ ፓርቲዎች እኛን ጨምሮ ልንፈርድ የምንችለው ሁሉም ላይ ነው። ዞሮ ዞሮ ግን የአማራን ሕዝብ መሰረት አድርገው እያጠቁ ያሉ ስለሆነ በእኛ ግምት የህልውና ትግል ውስጥ ነን ያለነው ብለን እንገምታለን። ይህን የህልውና ጦርነት ደግሞ ልዩነታችንን ወደ ጎን በመተው የምንችለውን ለማድረግ በዝግጅት ላይ ነው ያለነው። ይህንን ነው አሁን ልል የምችለው።

የአማራ ክልል መንግስት ሚሊሺያና ታጣቂዎች የራሳቸውን ስንቅ እና ትጥቅ ይዘው እንዲጠጉ መጠየቁን እንዴት ያዩታል? ከመንግሥት ድጋፍ ሊደረግላቸው አይገባም ይላሉ?
እሱ ምንም ጥያቄ የለውም። መንግሥት እንደመንግሥት ማቅረብ የሚገባውን ሎጀስቲክስ ማቅረብ አለበት። የግዴታው ነው። ይህ ጦርነት የአማራ ሕዝብ ጦርነት ብቻ አይደለም። አሸባሪው ህወሓትን ደግሞ አንድ ወገን ይዋጋ የሚል ሕግ የለም። ስለዚሀ የማዕከላዊ መንግሥት ግዴታም ጭምር ነው።

አማራ ክልል እስከዛሬ በነበረው ጦርነት የተለያዩ ወጪዎችን በራሱ ሲችል ቆይቷል። አሁንስ በዚህ መንገድ መቀጠሉ ተገቢ ነው ይላሉ?
እንግዲህ እሱን አብረን የምናየው ነው የሚሆነው። እኛም ማድረግ የሚገባንን እናደርጋለን ። ለጊዜው ይህንን ነው ልልህ የምችለው።

እናንተስ እንደ አንድ ፖለቲካ ፓርቲ ምን ለማደረግ አስባቹሃል?
እኛ ሕዝብ እናነቃለን፤ ሕዝብ እናደራጃለን። የህልውና ትግሉን እንዲመክት ማድረግ የሚገባንን ነገር እናደርጋለን። ከፊት መስመር ተሰልፈን ማንኛውንም መስዋዕትነት ለመክፈል ዝግጁ መሆናችንን ገልጸናል ። ይህንንም በተግባር እናረጋግጣለን።

የሌላው ክልልስ ተሳትፎ ምን መሆን አለበት?
የአማራ ክልል የሱማሌን አልፎ አይደለም ጥሪ የሚያቀርበው። የአማራ ክልል ለኦሮሚያ አይደለም ጥሪ የሚያቀርበው። እነዚህ በማዕከላዊ መንግሥት ስር ውስጥ ነው ያሉት። ማዕከላዊ መንግሥት ይሄን ጦርነት ጀምሮታል፤ መጨረስ መቻል አለበት። አሁንም ደግሜ ደጋግሜ የማነሳው አሸባሪን መዋጋት የአንድ ክልል ብቻ አይደለም። አሁን በውጭም በውስጥም ያለውን ተቋቁሞ ህወሓትን መደምሰስ የሚችል ከሆነ እኛ የምንችለውን ጠጠር እንወረውራለን። የምንችለውን እናደርጋለን። ይሄ ደግሞ ግልጽ አቋማችን ነው።

በዚህ ጉዳይ ላይ እርስ በርስ ለመከፋፈል የሚሞክሩ አሉ ይባላል። በዚህስ ላይ ምን አስተያየት አለዎት?
የአማራ ሕዝብ ከምንጊዜውም በላይ አንድነቱን ማጠናከር መቻል አለበት። የውስጥ ሽኩቻዎች ሊኖሩ ይችላሉ። ነገር ግን ትልቁን ምስል ማስተዋል አለብን። አሁን ጠላት የማሸነፊያ መንገዶችን ይቀይሳል ። ከዚህ ውስጥ አንድነትን ማላላት ዓላማው ነው። ከመቼውም ጊዜ በላይ ስለትልቁ ምስል ስለ አማራ ሕዝብ ሲባል ልዩነቶችን ማቻቻል ተገቢ ነው የሚል እምነት አለን። ያን ማድረግ መቻል አለብን፤ ካላደረግን እንደ ሕዝብ ህልውናችንን ማስጠበቅ አንችልም የሚል የጸና እምነት አለን። ምንም ይፈጠር ምን የውስጥ ልዩነታችንን ለጊዜውም ቢሆን ማቻቻል እንዳለብን በዚህ አጋጣሚ መልዕክቴን ማስተላለፍ እፈልጋለሁ ።

የአላማጣና ኮረም መያዝን በተመለከተ፣ በምን ምክኒያት ነው በዚህ አጭር ጊዜ ውስጥ ተይዘው የነበሩት?
አዳዲስ መረጃዎች እየወጡ ስለሆነ አሱን መጠበቅ ነው የሚሻለው። ለጊዜው ይህንን ነው ልል የምችለው።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በቅርቡ ያወጡትን መግለጫ እንዴት ተመለከታችሁት ?
በመርህ ደረጃ ጥሩ ነው፤ ግን ዋጋ አስከፍሏል። ወደ ተግባር መገባት አለበት።
እንደ መርህ ያው ነው። ዞሮ ዞሮ እንደ ድርጅት እናዋለን ።

የፌደራል መንግሥቱን በተመለከተ ዓለም አቀፍ ጫናዎችን በመፍራት እነሱን ለማርገብ የተደረገ ሙከራ ነው ይባላል። እንዴት ነው ይሄን የምታዩት?
ዓለም አቀፍ ተጽዕኖ የምንወጣበትን መንገድ ራሳችን መቀየስ አለብን እንጂ አንድን ሕዝብ ማዕከል አደርጎ የሚንቀሳሳስን አሸባሪ መተው አያስፈልግም። የአማራን ሕዝብ ሂሳብ እናወራርዳለን ነው የሚሉት፤ ይሄን በሚሉበት አግባብ ደግሞ የውጭ ጫና አለና ንጹሀን ዜጎችን ሙቱ የሚል ሎጂክ የለም። ምንም ይፈጠር ምን የትኛውም ኃይል ይኑር፣ ቢያንስ በትንሹ የዜጎች በሕይወት የመምኖር ዋስትና የሚሰጥ ነው መንግሥት የሚባለው። ስለዚህ አሸባሪ መሆኑን አውጀህ የዜጎችን ሠላምና ደህንነት ማስጠበቅ መቻል አለብህ። ስለዚህ እነዚህ ሎጂኮች አንካሳ ናቸው። በቂ ምክኒያት አይሆኑም በኛ እምነት።

በአጠቃላይ የአሸባሪው ቡድን እያደረገ ያለውን እርምጃ ይቀጥላል ብለው ይገምታሉ?
በእኛ እምነት በተቀናጀ ትግል ይመለሳል የሚል ዕምነት አለን። ይህንን ነው ልል የምችለው። ምንም ቢፈጠር የአማራ ሕዝብ ህልውናውን ማሰከበር አያቅተውም የሚል የጸና እምነት አለን። የአማራ ሕዝብ በተባበረ ክንዱ ከሌሎች ወንድሞቹ ጋር ሆኖ ይሄንን የህልውና ትግል መስመር ያሲዘዋል። በአሸናፊነትም ይወጣዋል።

እዝ ሰንሰለቱን በተመለከተ ወታደሩ ላይ የሞራል መላሸቅ እንዲፈጠር እየተደረገ ነው የሚባልም ነገር አለ?
እሱ ፖለቲካ ነው። ወታደራዊ ድሎች በፖለቲካ ድል ካልታገዙ ዋጋ የላቸውም። ስለዚህ ወታደራዊ ድሎችን ለማስጠበቅ ፖለቲካዊ ድሎችን ማስመዝገብ ያስፈልጋል። ነቢይ መሆን ባይጠይቅም በእርግጠኝነት መናገር የምችለው በተባበረ ክንዳችን ልናሸንፍ እንደምንችል ነው። ስናሸንፍ ሁሉም ይስተካከላል። ምንም ይፈጠር ምን እሱን ሁሉ ተሻግረን አማራን በዚህ የህልውና ትግል እናስከብራለን የሚል የጸና እምነት አለን። ይህን ደግሞ እናደርገግዋለን። ይህንን ስናደርግ መስዋዕትነት ልንከፍል እንችላለን። መስዋዕትነት ለመክፈል ደግሞ በጣም ዝግጁ ነን። እኛ እንደ አማራ ዲሞክራሲያዊ ንቅናቄ ይህንን ስናደርግ ደግሞ በደስታ ነው። በመጨረሻ እንደምናሸንፍ እርግጠኞች ነን። ይሄ ተራ ፉከራ አይደለም፤ተራ የፖለቲካ ንግግርም አይደለም። የምናደርገውን ነው የምንናገረው። ምክንያቱም ቁመን ወይም ለሌላ አካል ሰጥተን ልናሸንፍ አንችልም። አመሰግናለሁ።


ቅጽ 3 ቁጥር 141 ሐምሌ 10 2013

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com