የእለት ዜና

የኢትዮጵያ ምርት ገበያ 10 አዲስ ምርቶችን ወደ ገብያ ሥርዓት እንደሚያስገባ አስታወቀ

Views: 42

ምርት ገብያው በ2013 በጀት ዓመት 775 ሚሊዮን ብር ገቢ አግኝቷል

የኢትዮጵያ ምርት ገብያ በ2014 በጀት ዓመት 10 አዳዲስ ምርቶችን ወደ ገብያ ሥርዓት እንድገቡ ለማድረግ የቅድመ ዝግጅት ሥራ መሥራቱን አስታወቀ።
በአዲሱ በጀት ዓመትና በቀጣዮቹ ዓመታት ወደ ግብይት ሥርዓቱ ሊገቡ ለሚችሉ 10 ምርቶች ማለትም ሙጫ፣ አብሽ፣ቁንዶ በርበሬ፣ ጥቁር አዝሙድ፣ እርድ፣ ኮረሪማ፣ ጓያ፣ ኦቾሎኒ፣ ሩዝ እና የዱባ ፍሬ ላይ የአዋጭነት ጥናት መካሄዱን የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ወንድማገኘሁ ነገራ ገልጸዋል። እነዚህ ምርቶች በ2014 በጀት ዓመት እና በሚቀጠሉት አመታት ወደ ግብይት ስርዓት እንደሚገቡ ዋና ሥራ አስፈጻሚው አስታውቀዋል።
በተጠናቀቀው በጀት ዓመት የርግብ አተር፣ ዥንጉርጉር ቦሎቄና ፒንቶ ቢን ወደ ግብይት ስርዓቱ መካተታቸው ተመላክቷል።

በ2013 በጀት ዓመት ምርት ገበያው ከኦፕሬሽናልና ኦፕሬሽናል ካልሆኑ ምንጮች ያገኘው ገቢ ባጠቃላይ ብር 775 ሚሊዮን ሲሆን፣ ከዕቅዱ ከታቀደው በላይ 106 በመቶ ማሳካቱን አስታወቋል። ገቢው ካለፈው በጀት ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር 20 በመቶ ብልጫ እንዳለው ተጠቁሟል። እንዲሁም ጠቅላላ ወጪ ብር 517 ሚሊዮን ሲሆን ከ2012 በጀት ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲተያይ የ14 በመቶ ጭማሪ አሳይቷል። ከወጭ ቀሪ በ2013 በጀት ዓመት ብር 258 ሚሊዮን በላይ ከግብር በፊት ትርፍ መገኘቱ ተገልጿል። ይህ አፈጻጸም ይመዘገባል ተብሎ ከታሰበው ትርፍ በላይ 15 በመቶ መሆኑን ዋና ሥራ አስፈጻሚው በመግለጫው ላይ አስታውቀዋል።

ከምርት ሻጮች 2 በመቶ ዊዝ ሆልዲንግ ታክስ 756 ሚሊዮን ብር፤ ከአገር ውስጥ ቡና ተገበያዮች ቫት 847 ሚሊዮን ብር፤ ምርት ገበያው ከሚሰብስበው የአገልግሎት ክፍያና ከመሳሰሉት ቫት 60 ሚሊዮን ብር፤ በድምሩ 1̌.7 ቢሊዮን ብር ግብር በመሰብሰብ ለመንግሥት ገቢ መደረጉንም ዋና ሥራ አስፈጻሚው አክለው ገልጸዋል።

በ20013 በጀት ዓመት ለግብይት ከቀረቡ ምርቶች በስብጥር ደረጃ 35.5 በመቶ በመያዝ ቡና ቀዳሚነቱን ሲይዝ፣ ሰሊጥ 31 በመቶ እና የተለያዩ ጥራጥሬዎች በጋራ 33.4 በመቶ በመያዝ ይከተላሉ።
በሌላ በኩል የማዕድን ሃብት ግብይትን ለማሻሻል የማዕድን ምርቶችን ወደ ዘመናዊ የግብይት ሥርዓት ለማስገባት የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ከማዕድንና ነዳጅ ሚኒስቴር ጋር ስምምነት ተፈራርሟል። በተፈራረመው የመግባቢያ ሰነድ መሰረት በ2014 በጀት ዓመት ኦፓል፣ሳፋሪና ኢመራልድ ማዕድናትን ማገበያየት እንደሚጀመር ተጠቁሟል።

ባለፉት ወራት ከኹለቱም መሥሪያ ቤቶች የተውጣጡ ባለሙያዎች ያሉበት የቴክኒክ ኮሚቴ ተቋቁሞ የዝግጅት ሥራ እያከናወነ እንደሆነና እስካሁን የቅድመ ዝግጅት ሥራ፣ የኮንትራት ዝግጅትና የግብይት ሞዳሊቲ ተዘጋጅቶ በቅርቡ በማዕድን ምርትና ግብይት ላይ ከተሰማሩ ባለድርሻ አካላት ጋር የኢንዱስትሪ ምክክር እንድሚድረግም ተገልጿል።

የኢትዮጵያ ምርት ገበያ በበጀት ዓመቱ የኮትሮባንድና ሕገ-ወጥ ንግድ ፈተናዎቹ እንደነበሩ የገለጸ ሲሆን፣ በሚመለከታቸው አካላት የመከላከል ጥረት ቢደረግም አሁንም ማስቀረት እንዳልተቻለ ታውቋል።
ግብይታቸው በምርት ገበያው ተከናውኖ የውጭ ምንዛሬ ለአገራችን ማስገኘት የሚችሉ ምርቶች አሁንም ወደ ጎረቤት አገራት በኮንትሮባንድ መላካቸው ስላልተገታ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመሆን ሕገ-ወጥ ንግድን ለመከላከል የሚደረገውን ጥረት አጠናክረን እንቀጥላለን ሲሉ የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ወንድማገኘሁ ነገራ አስታውቀዋል።

በ2013 በጀት ዓመት 614 ሺሕ 586 ሜትሪክ ቶን ምርት በ39.6 ቢሊዮን ብር ማገበያየቱንም ምርት ገብያው ሐምሌ 8/2013 በሰጠው ጋዜጣዊ መገለጫ አውስቷል።
ለግብርና ምርት አቀነባባሪ ኢንዱስትሪዎች በቂ ግብዓት እንዲያገኙ ለማስቻል በጥቅምት 2013 በከፈተው ልዩ የግብይት መስኮት አማካይነትም እስካሁን 430,680 ኩንታል አኩሪ አተር በ990 ሚሊዮን ብር አገበያይቷል። ለአቀነባባሪ ኢንዱስትሪዎች የተገበያየው የአኩሪ አተር መጠን ከጠቅላላ የምርቱ ግብይት 50 በመቶ ይሸፍናል።

ከደረጃ በታች የሚመጡ ምርቶች ሲኖሩ አቅራቢዎች የማበጠርና የእጥነት አገልግሎት የሚያገኙበት አሠራርም ተዘርግቷል ተብሏል። እንዲሁም ለጥራጥሬና ቅባት እህል አቅራቢዎችና ገዢዎች ለግብይት ከመምጣታቸው በፊት በመረጃ መረብ የቅድመ ግብይት መረጃ የሚያገኙበት ሁኔታ ሥራ ላይ ውሏል።

በተጨማሪም የቅድመ ግብይት ሥርዓትን ለመጀመር የሚያስችል የመጀመሪያ ደረጃ የአዋጭነት ጥናት በውስጥ አቅም ተሰርቶ የተጠናቀቀ ሲሆን፣ ዝርዝር ጥናት የአፈጻጸም ዕቅድ (Implementation Plan) ለማዘጋጀት ከኢንተርናሽናል ፋይናንስ ኮርፖሬሽን ጋር በመተባበር በዘርፉ ልምድ ያለው የውጭ ኮንሰልታንት እንዲሳተፍበት በማድረግ የመጨረሻ ደረጃ ጥናቱ በመከናወን ላይ ይገኛል ተብሏል።


ቅጽ 3 ቁጥር 141 ሐምሌ 10 2013

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com