የእለት ዜና

በካዝና የተገደበው የትግራይ ክልል በጀት

Views: 70

በጀት ለአንድ ክልል የነዋሪዎቹን መሰረታዊና አስፈላጊ ፍላጎቶችን ለማሟላት አስፈላ መሆኑ ይታወቃል።ከዚህ በመነሳት ለትግራይ ክልል 12 ቢሊዮን ብር የሚደርስ በጀት ተመድቧል። ይህ ደግሞ መንግስት መፈጸም ካለበት ኃላፊነቶች መካከል አንዱ ነው። ቢሆንም ግን ትግራይ ክልሉን የሚያስተዳድር የተረጋጋ መንግሥት ባለመመስረቱ በጀቱን ወስዶ ለሚፈለገው ጉዳይ ለማድረስና ለማዋል መንግሥትም እንደተቸገረ ይገለጻል። የሰላም እጦት ለዚህ ሁሉ ጉዳይ እንደ ትልቅ ተግዳሮት ሆኗል። ገንዘቡን ደግሞ የሚያስተዳድረው ከሌለ ዝም ብሎ ሜዳ ላይ አይበተንም የሚሉት በሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርስቲ የልማት፣ ምጣኔ ሀብት እና ሥራ አመራር ትምህርት ክፍል ተባባሪ ፕሮፌሰር ካሳ ተሻገር ናቸው።

ስለዚህ መንግሥት ክልሉን ማረጋገትና ወደ ሰላም መመለስ ይገባዋል። ነገር ግን የህወሓት አመራሮች በተደጋጋሚ እርቅ እንዲያወርዱ ቢጠየቁም አሻፈረን እያሉ ነው። መንግሥትም የጥሞና ጊዜ በማለት የተኩስ አቁም ስምምነት አውጆ ለሰላም ጊዜ ቢሰጥም፣ ሳይሳካ መቅረቱ ይታወሳል።

ተግባራዊ የሚሆን የሰላም አማራጭ መፍጠርም አልተቻለም። ስለዚህ ይላሉ ካሳ ‹‹በእኔ እምነት መሆን ያለበት መጀመሪያ ለአንዴ እና ለመጨረሻ ጊዜ እርምጃ ወስዶ ክልሉን ማረጋጋትና ወደ ነበረበት ሁኔታ መመለስ ነው። ቀጥሎ በጀቱ እንዲደርስ የማድረግ ሥራ መሥራት ያስፈልጋል››ብለዋል።

ትግራይ ክልል ሙሉ ለሙሉ በአሸባሪዎች ውስጥ በመሆኑ ችግር ተፈጥሯል። ሌላ አካባቢ ቢሆን ኖሮ ቢያንስ የሚያስተዳድረው አካል ስለሚኖር ክልሉ ግርግር ቢፈጠርም እንኳን ሕዝቡ የሚጠቀምበት አማራጭ ይፈጠር ነበር።
ትግራይ ክልል እየሠሩት ያለው ሥራ የሚታይ ነው። የትግራይ ክልል ስትራቴጂ መሆን ያለበት ድጋፍ ማቅረብ ላይ ያተኮረ መርህ መከተል ይኖርበታል። ከዚህ ውስጥ ከውጭ በሚገኝ እርዳታ ከበጀቱም ባለፈ ቢሆን ሕብረተሰቡ ጋር በቀጥታ የሚደርስበት መንገድ ማመቻቸት አለበት ሲሉ ካሳ ያብራራሉ። የፌደራል መንግሥት በራሱ አቅም ለክልሎች የድጋፍ አማራጭ መፍጠር አለበት።

መንግሥት ይህን ማደረግ የማይችል ከሆነ ተቀባይ የክልል አካል አይኖርም፤ ቢላክም ለአሸባሪዎች ዓላማ ማስፈጸሚያ እንደሚውል ይታወቃል።
በቅርብ ጊዜ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ያነሱት 100 ቢሊዮን ብር በጀት ለጦርነት ክልሉ ላይ ብቻ የወጣበት ሁኔታ ነበር።
መንግሥት ህዝቡን የመታደግ ግዴታ ስላለበት በአዲስ የስትራቴጂ እቅድ ለሕዝቡ መድረስ ያለበትን ሰብዓዊ ድጋፍ ማቅረብ ይኖርበታል።
‹‹ይህ ብቻ መፍትሄ ይሆናል ለማለት ሳይሆን ወደፊት ክልሉ መሰረተ ልማት ያስፈልገዋል›› የሚሉት ካሳ ተግዳሮቶች በዚሁ አይቀጥሉም ብለዋል። በቅርቡም የጠቅላይ ሚኒስትሩ ቆንጠጥ የሚያደርግ መልዕክት አስተላልፈው ነበር። ጠቅላይ ሚኒስትሩ በመግለጫቸው ግጭት ላለማባበስ ሲባል የተኩስ አቁም ስምምነት የተደረገ ቢሆንም፣ አሁን ግን መንግሥት ትዕግስቱን እንደጨረሰ ተናግረዋል።

‹‹ድመት መንኩሳ አመሏን አትረሳ›› ብለው የተረቱተ ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ጁንታው አሁን ባለበት ሁኔታ ሰላም የሚባል ነገር እንደማይፈልግ ለዚህም ደግሞ ማሳያ ህጻናትን ለውትድርና መስደዱ ነው ሲሉ አንስተዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ አክለውም ሕዝቡ በትብብር ጁንታው የሚሰራውን የጠላት ሥራ ለመከላከል እንደወሰነ ገልጸዋል።
የትግራይን ሕዝብ በረሃብ ሊገል የተቀናጀ የጁንታው ኃይል ጦርነቱን እያስቀጠለው ይገኛል ብለዋል።

የጸደቀው በጀት የ2014 በጀት ዓመት የሚያገለግል እንደመሆኑ መጠን የበጀት አለቃቀቁ ከመጀመሩ በፊት መንግሥት ጊዜ ሳይሰጥ ሰላም ማስጠበቅ አለበት።
ከዚህ በፊት ሕዝቡ እንዳይጎዳ፣ ንጹሃን እንዳይሞቱ እየተባለ ነበር፤ ነገር ግን ዞሮ ዞሮ ሕዝቡ ከመጠቃት አላመለጠም። እንዲያውም ሕዝብ እንዳይጎዳ እየተባለ እርምጃ አለመወሰዱ የባሰ ነውጥ ውስጥ እያስገባው ነው ሲሉ ካሳ ያነሳሉ።
‹‹አሁን መንግሥት አሸባሪውን አካል ሙሉ ለሙሉ በቁርጠኝነት ማጥፋት ይገባዋል። ከዛ በኋላ የተረጋጋ ምርጫ አካሂዶ እስከ መስከረም ክልሉን የሚያስተዳድር አካል መፍጠር ያስፈልጋል›› ብለዋል።
የተበጀተላቸው በጀትም ቢሆን ማንም ሳይነካባቸው የሚቀመጥ ሲሆን፣ ሰብዓዊ ድጋፎችም ቢሆን ለሰብዓዊ እርዳታ ከሚደረጉ ድጎማዎች የሚገኝ ሊሆን ይገባል ሲሉ ለአዲስ ማለዳ አስረድተዋል።

ገንዘብ የሚተዳደረው በመንግሥት መሆኑ ይታወቃል። መንግሥት በሌለበት ሁኔታ በጀት ለግለሰብ መስጠት አይቻልም። መንግሥት በሌለበት በጀት መድቦ እንዴት ላድርስ የሚለውን ጥያቄ ማንሳት ከፈረሱ ጋሪው የቀደመ ይመስላል ሲሉ ለአዲስ ማለዳ አስተያየት የሰጡ ስማቸው እንዳየጠቀስ የፈለጉ ምሁር ገልጸዋል።

ተጠቃሚው ዜጋ ሲሆን በጀት ለማጽደቅ የበጀት ሕግ አውጪ አካል እና አስፈጻሚ ማነው ከተባለ ህወሓት መሆኑ ግልፅ ነው። ነገር ግን ፓርላማው ሕገ-ወጥ አሸባሪ ድርጅት መሆኑን በመግለጹ እና በምርጫ የተቋቋመ መንግሥት ባለመሆኑ ባለን ጊዜ እንጠቀም የሚል ሥራ የያዘ ይመስላል ሲሉ ምሁሩ ይገልጻሉ። የበጀት አፈጻጸም ሕጉም ቢሆን እንደዚህ አይነት ነገሮችን አያካትትም። የበጀት አለቃቅ ሕግ የሚወጣው በሕግ አወጣጥ ሂደት ሕግ አስፈጻሚ አካል እንደሚኖር ታሳቢ አድርጎ ነው ሲሉ ምሁሩ አንስተዋል።
አሁን መንግስት በሌለበት ሁኔታ በጀት አለቃቀቅ ማስፈጸም አይቻልም። ሰብዓዊ ድጋፍ ቢፈለግም እንኳን እውቅና ያለው አስፈጻሚ ተቋም ያስፈልጋል። ትግራይ ክልል ገንዘብ ለመቀበልም ሆነ ገንዘብ ለማመንጨት አሁን ያለበት ቁመና ግራ የሚያጋባ ነው። ‹‹ስለዚህ የሚቀድመው የሚመስለኝ ክልሉን አረጋግቶ ማደራጀት እና መንግሥት መመስረት ነው” ይላሉ ምሁሩ።

በተግባር መንግስት የዜጎችን ደህንነት አስጠብቆ በጀት መልቀቅ ይገባዋል። በሌሎች ዓለም አገራት፣ አገር ሰላም ብትሆንም ገንዘብ የማይለቀቅበት ሁኔታ አለ። ክልሉ አስተዳዳሪ ተቋም የማይኖረው ከሆነ በፌደራል መንግሥቱ ራሱን የቻለ ተቋም ተደራጅቶ ሕዝቡን ተጠቃሚ የሚያደርግበት አማራጭ አለ።

ለክልሎች በጀት የሚመደበው ገንዘብ የሚያመነጭ፣ የሚያወጣ እና የሚያስፈጽም ተቋማት አሉ ተብሎ ነው።
አሁን እነዚህ በሌሉበት ወደ ተፈጻሚነት የሚቀይር የክልሉ ተወካይ ቢፈጠር እንኳን ግልጽ እና ተጠያቂ የሚሆን አካል መሆን ይጠበቅበታል ብለዋል ምሁሩ። በተደራጀ የካቢኔ አባል ተጠያቂ የሆነ አካል በመፍጠር በጀቱን ማግኘት ይገባዋል። ይህንን ለማድረግ ፖለቲካል

ውሳኔዎች ያስፈልጋሉ።: የገንዘብ ድጋፍ አጠቃቀም፣ ሕግን ማክበር እና በሰብዓዊ ድጋፍ መልኩ የሚያስፈልጉ ማንኛውም ነገር ለሕዝብ ማድረስ ያስፈልጋል።
ፖለቲካዊ አደረጃጀት መቀየር አስፈላጊ መሆኑ ይታወቃል። የፌደራል መንግሥት ለክልሎች ድጋፍ የሚያደረግበት አዲስ ቀመር በቅርቡ በፓርላማ ቀርቦ መጽደቁ የሚታወስ ነው።
የዚህ ቀመር መርሆ የነበረው ፍላጎት የውስጥ የማመንጨት አቅም፣ ሕዝብ ብዛት እና ምን አይነት ኢንቨስትመንት ፍሰት እንደሚፈልግ የሚዳስስ ነው።
በዛ መሰረት እስከ አሁን በየቦታው ያለውን የኢንቨስትመንት እደገት እና የነበሩትን በማሰብ ለየክልሎች በጀት ይመድባል። ከዚህ በተጨማሪ መደበኛ የሆነ የጋራ ገቢን ወይም ኢኮኖሚን ተላብሶ የሚመደብበት አጋጣሚዎችም ይፈጠራሉ። አሁን ያለው ሁኔታ ፖለቲካዊ ቀውስ ነው። ይህ ደግሞ ከፍ እያለ መጥቶ ኢኮኖሚያዊ ተጽእኖ ፈጥሯል።

በጀቱን ተቀብሎ አፈጻጸሙን የሚያረጋግጥ አካል በማይኖርበት ሁኔታ ምን እንደሚደረግ በቀመሩ ውስጥ የተካተተ ነገር የለም። ፖለቲካው እና ኢኮኖሚውን እየለየነው አይደለም። ሕዝብ ለማገልገል ምርጫ ራሱ ማካሄድ ይኖርበታል። የክልሉ ሁኔታ መመሰቃቀል እየታየበት ነው። ሕዝቡ ጋር በቀጥታ ሊደርስ የሚችለው ሰብዓዊ ድጋፍ ብቻ መሆኑን ነው ያነሱት ምሁሩ።

ሁኔታው በመንግሥትም ከባድ ሁኔታ ፈጥሮበት የታየበት መሆኑን ያነሱት ምሁሩ፣ በክልልና በፌደራል መንግሥት ግልጽነት ያስፈልጋል ብለዋል።
ክልሉ ሰላም እንኳን ቢሆን የተሰጠውን ገንዘብ ግልጽ በሆነ አሠራር የማይተገብር ከሆነ እና ገንዘቡን ለሕዝብ አገልግሎት የማያውል ከሆነ፣ የሚያስፈጽሙ አካላት ገንዘቡን በአግባቡ መጠቀም መቻላቸውን ማረጋገጥ ያስፈልጋል።
እንኳን እንደዚህ ግርግር ተፈጥሮ ይቅር እና በሰላማዊ ጊዜም ቢሆን ገንዘቡን በትክክል እንደሚጠቀሙት ጥያቄ ውስጥ ይገባል።
የፌደራል መንግሥት ለትግራይ ክልል የተመደበውን የ2014 ዓመታዊ በጀት ለመልቀቅ ውሳኔ ላይ አለመድረሱን ገልጾ እንደነበር ይታወሳል።

የትግራይን ክልል በጀት ለመልቀቅ ሁኔታው አስቸጋሪ መሆኑን የገንዘብ ሚኒስትር አህመድ ሺዴ መግለጻቸው ይታወሰል።
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የ2014 በጀት 561.7 ቢሊዮን ብር አጽድቆ ነበር። ከጸደቀው በጀት ውስጥ 203 ቢሊዮን ብር ለክልሎች የሚውል ሲሆን፣ ለኦሮሚያ ክልል 69 ቢሊዮን ብር፣ ለአማራ ክልል 43 ቢሊዮን ብር፣ ለደቡብ ክልል 32 ቢሊዮን ብር፣ ለሶማሌ ክልል 20 ቢሊዮን ብር፣ ለሲዳማ ክልል 8 ቢሊዮን ብር፣ ለአፋር ክልል 6 ቢሊዮን ብር፣ ለቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል 3.6 ቢሊዮን ብር፣ ለጋምቤላ ክልል 2 ቢሊዮን ብር፣ ለአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር 3.3 ቢሊዮን ብር፣ ለሐረሪ ብሔራዊ ክልል 1.5 ቢሊዮን ብር እንዲሁም ለድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር 1.7 ቢሊዮን ብር ተመድቧል።

ከጸደቀው ውስጥ የትግራይ ክልል 12 ቢሊዮን ብር እንደሚያገኝ የቀረበው የበጀት ሰነድ ያመላክታል።
ይሁን እንጂ የገንዘብ ሚኒስትሩ ለክልሉ በጀት ለመልቀቅ የሚያስችል ምንም የተመቻቸ ሁኔታ አለመኖሩን ጠቁመው ነበር።
በትግራይ ክልል መንግሥት እና ህወሓት ጦርነት ሲያደርጉ የቆየ ሲሆን፣ የፌደራል መንግሥት ክልሉን ሙሉ ለሙሉ ለቅቆ መውጣቱ የቀጣይ ዓመት በጀት በምን መልኩ እንደሚለቀቅ ግራ የሚያጋባ ሆኖ ሰንባብቷል።
ይህ የበጀት አለቃቅ እንደ መንግሥት ግራ የሚጋባ በመሆኑ ሰፊ ውይይት እንደሚያስፈልገው ሚኒስትሩ ገልጸዋል።


ቅጽ 3 ቁጥር 141 ሐምሌ 10 2013

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com