የእለት ዜና

የክረምቱ የጎርፍ አደጋ ስጋት

Views: 62

በኢትዮጵያ የተለያዩ አካባቢዎች በክረምት ወቅት ከዝናብ መክበድ ጋር ተያይዞ የጎርፍ አደጋዎች፣ የመሬት መንሸራተት፣ የመንገድ መበላሸትና ድልድል ስብራቶች ያጋጥማሉ። ይህ ችግር በሚከሰትበት አከባቢ ከሰው ሕይወት መጥፋት እስከ ማሕበረሰብ መፈናቀልና ንብረት ውድመት የሚደርሱ ጉዳቶች ይከሰታሉ።

በጎርፍ ምክንያት የሚከሰቱ አደጋዎች የበርካታ ሰዎችን ሕይወት የቀጥፉ እና በሺሕዎች ለሚቆጠሩ ሰዎች የንብረት መጥፋት ምክንያት የሆኑ ናቸው። ከዚህ በተጨማሪ አደጋዎቹ ሰዎች ሀብት ንብረታቸውን ትተውና ከመኖሪያ አካባቢያቸው ለቀው ወደ ተለያዩ አጎራባች አካባቢዎች እንዲፈናቀሉ ምክንያት ይሆናሉ።

በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች በሚዘንበው ከባድ ዝናብ ምክንያት በሚፈጠር የጎርፍ አደጋና የመሬት መንሸራተት የተለያዩ የማሕበረሰብ ክፍሎች ለከፍተኛ ጫና መዳረጋቸው ይታወሳል። በተለያየ ጊዜ ድንገተኛ ጎርፍ በመከሰቱም ከፍተኛ የሆኑ አደጋዎች በዜጎች ላይ መድረሳቸው አይዘነጋም።

በአዲስ አበባም በተለያዩ አካባቢዎች በክረምት ወቅት ጎርፍ አስፋልት ላይ ስለሚተኛ ከፍተኛ ለሆነ የመንገድ መጨናነቅና ለመኪና አደጋ ሕብረተሰቡ ይጋለጣል። በዚህም ምክንያት ሰዎች ሕይወታቸውን ያጣሉ፤ በተጨማሪም ለንብረት ውድመት ይጋለጣሉ።
የዝናብ ስርጭቱ መጠን በሚጨምርበት ወቅት የሚከተው ጎርፍ በነዋሪዎች ቤት ውስጥ በመግባት የሕይወት፣ የአካል ጉዳት ብሎም የንብረትን ውደመት ያስከትላል።

በከተማዋ አንዳንድ አካባቢዎች ላይ ከመጠን ያለፈ ውኃ ከቱቦ ወስጥ በመውጣትም በእግረኛ ፣በተሽከርካሪና በመኖሪያ ቤቶች ላይ ከፍተኛ ጉዳት ሲያደርስ መታየቱ የተለመደ የክረምት ክስተት ነው።
የንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ነዋሪው ክንፈ ቢቂላ በክፍለ ከተማው ከሚገኝ ወንዝ ዳር ከቤተሰቦቹ ጋር የሚኖር ሲሆን፣ ክረምት በመጣ ቁጥር እሱና በአካባቢው ያሉት ነዋሪዎች ሁሉ ለጎርፍ አደጋ ተጋላጭ ናቸው። የመኖሪያ ቤታቸው ወንዝ ዳር በመሆኑ ምክንያት በክረምት ወራት አብዛኛውን ጊዜ ለጎርፍ አደጋ ተጋላጭ ሆነው ኖረዋል።

በ2011 ክረምት ወቅት ላይ ባቅራቢያቸው የሚገኘው የወራጅ ውኃ ማስተላለፊያ መስመር (ቱቦ) በመጥበቡ ምክንያት በወቅቱ በጣለው ከፍተኛ ዝናብ ጎርፉ ከድልድዩ በመውጣት ወደ ነዋሪዎች ቤት በመግባቱ ለጉዳት ተጋላጭ ሆነው ነበር።
የጎርፉ አደጋ የተከሰተው ከቀትር በኋላ ወደ 11 ሰዓት አካባቢ በመሆኑ በቦታው የነበሩ ሰዎች እራሳቸውን በፍጥነት ለማትረፍ ቢችሉም፣ ንብረታቸውን ግን ማዳን አለመቻላቸውን ነዋሪዎች ለአዲስ ማለደ ተናግረዋል። በጊዜው በተከሰተው የጎርፍ አደጋ በአካባቢው ነዋሪ ላይ የሕይወት መጥፋትና የአካል ጉዳት ባይደርስም፣ በመኖሪያ ቤቶች ላይ ሙሉ በሙሉ ለማለት በሚቻል መልኩ ጉዳት ደርሷል።

በመኖሪያ ቤቶች ላይ የደረሰውን ጉዳት በቁጥር ለመግለጽ ቢከብድም የመኖሪያ ቤታቸው በሙሉ መውደሙን ክንፈ ከአዲስ ማለዳ ጋር በነበራቸው ቆይታ ነግረውናል።
ነዋሪዎቹ ጎርፍ ወደ መኖሪያ ቤታቸው በመግባቱ በወቅቱ የነበራቸውን የምግብ እህል፣ የኤሌክትሮኒክስ መገልገያዎች፣ እንዲሁም አልባሳትና መሰል ቁሳቁሶች ላይ ከፍተኛ ጉዳት እንዳደረሰ አዲስ ማለዳ ማወቅ ችላለች።
እንደ ክንፈ ገለጻ የውኃ ማስተላለፊያ ቱቦው በተጠራቀመ ቆሻሻ ምክንያት በመደፈኑ ጎርፉ ከትቦ አልፎ ወደ መኖሪያ ቤታቸው መግባቱን ጠቁመዋል። በተከሰተውም አደጋ ምክንያት በንብረታቸው ላይ ከፍተኛ ጉዳት በመድረሱ ለ3 ቀናት ያህል ከቤታቸው ወጪ እንደተጠለሉ ያስታውሳሉ።

ጉዳቱ በሕይዎታቸው ላይ ጫና በመፍጠሩም የአከባቢው ማሕብረሰብ ትብብር አድርጎላቸው እንደነበር አስረድተዋል። በጊዜው ማሕበረሰቡ በገንዘብ፣ ለግንባታ የሚያስፈልጉ መሳሪያዎችን በመስጠት እና የጉልበት እገዛ በማቅረብ እርዳታ ሲያደርጉላቸው እንደነበር ጠቅሰዋል።

ክፍለ ከተማው ለተጎጅዎቹ የገንዘብ እና ሌሎች ድጋፎችን ባይደረግላቸውም፣ በጎርፍ አደጋው ምክንያት የፈረስባቸውን ቤት ያለ ፈቃድ የማደስ መብት እንደሰጣቸው ጠቁመዋል።
ይህ አይነቱ አደጋ ለኹለተኛ ጊዜ ከ1 አመት በፊት ዳግም ተከስቶ እንደነበር የሚናገረው ክንፈ፣ በአካባቢያቸው የሚገኝ ነዋሪ ለግንባታ በሚል የመኖሪያ ቤቱን አጥር በማፍረሱ በዝናብ ወቅት ጎርፍ ነዋሪዎቹ ቤት ዳግም ለመግባት መቻሉን ተናግረዋል።
ለጎርፍ አደጋ እንደ መንስኤ ከሚጠቀሱት መካከል የውኃ ማስተላለፊያ ቱቦዎች በቆሻሻ መደፈን እንዲሁም ደረጃቸውን የጠበቁ መከላከያ ግንቦችና ድልድዮች አለመኖራቸው ነው። በመሆኑ የአካባቢው ነዋሪዎች ገንዘብ በማሰባሰብ ድልድይ በመገንባት፣ በውኃ መፍሰሻ ቱቦዎች ላይ የማጽዳት ሥራ በመሥራት የአደጋ አጋላጭ ሁኔታዎችን ለመፍታት እንደቻሉ አዲስ ማለዳ ለማወቅ ችላለች።

ኹለተኛው አደጋ በማሕበረሰቡ ላይ ከፍተኛ ጉዳት ባያስከትልም በወቅቱ መጠነኛ ችግሮች አስከትሎ እንደነበር ግን ነዋሪዎቹ ጠቁመዋል። እነዚህን የጎረፍ አደጋዎች ለመቀነስ የሚያስቸሉ ያሏቸውን መፍትሔዎችም ነዋሪዎቹ ያነሳሉ። እንደ ክንፈ ገለጻ በማሕበረሰቡ ላይ ክረምትን ጠብቀው የሚከሰቱ የጎርፍ አደጋዎችን ለመቀነስ እንዲቻል አዲስ በሚገነቡ መሰረተ ልማቶች ላይ ባለድርሻ አካላት በተናጠል ከመወሰን ይልቅ ማሕበረሰቡን ተሳታፊ ቢያደርጉ መልካም እንደሆነ ነው።

ከዚህም በተጨማሪ በአከባቢው የሚኖሩ ነዋሪዎች ግንባታ ሲጀምሩ ወቅቱን ባማከለ ሁኔታ መሆን እንዳለበት አንስተዋል። ከዚህ ጋር በተያያዘ የማሕበረሰቡ አባላት እርስበርስ መተባበርና የሚኖርባቸውን ግዴታ በጋራ ቢወጡ መልካም እንደሆነ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።
በሌላ በኩል፣ በቂርቆስ ክፍለ ከተማ ነዋሪና የጎርፍ አደጋ ሰለባ የሆኑት አመለወርቅ ዘውዱ ከአዲስ ማለዳ ጋር በነበራቸው ቆይታ እንደተናገሩት፣ ቤታቸው መንገድ ዳር ላይ በመሆኑ ምክንያት ብዙውን ጊዜ ከባድ ዝናብ ሲዘንብ አስፋልት ላይ ውኃው ስለሚተኛ ወደ መኖሪያ ቤታቸው ዘልቆ በመግባት በንብረታቸው ላይ ከፍተኛ ጉዳት እንደሚያደርሰባቸው ነው።

በአንድ ወቅት ወደ ቤታቸው የገባው ጎርፉ እስከ ወገባቸው የደረሰ በመሆኑ እራሳቸውን ማትረፍ ቢችሉም በመኖሪያ ቤታቸው የሚገኙ የመገልገያ ዕቃዎችን ግን ማዳን እንዳልቻሉ ገልጸዋል።
አመለወርቅ ለደረሰባቸው የጎርፍ አደጋ እንደ መንስኤ የሚያነሱት ነገር በከተማዋ ላይ የሚስተዋለው አግባብነት በሌለው መንገድ የሚፈጸም የቆሻሻ አወጋገድ ሂደት ነው።
በተጨማሪም በጎዳናዎች ላይ የሚገኙ የፍሳሽ ማስወገጃ ቱቦዎች መደፈን በክረምት ወቅት ለሚከሰቱ የጎርፍ አደጋዎች መንስኤ መሆናቸውን አመልክተዋል።

በብሔራዊ አደጋ ስጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን የሕዝን ግንኙነት ዳይሬክተር ደበበ ዘወዴ ከአዲስ ማለዳ ጋር ባደረጉት ቆይታ እንደተናገሩት፣ ብሔራዊ አደጋ ስጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን በሦስት ዋና ዋና ጉዳዎች ላይ አተኩሮ እንደሚሰራ ገልዋል። እነዚህም ቅድመ-አደጋ መከላከል ዝግጅት፣ አደጋዎች ሲከሰቱ ምላሸ መስጠትና ከአደጋዎች በኋላ ተጎጂዎችን መልሶ የማቋቋም ሥራን ማከናወን እንደሆነ ተናግረዋል።

እንደ ብሔራዊ ሜትሮሎጂ ኤጀንሲ መረጃ መሰረት በሐምሌና ነሐሴ ወራት ከባድ ዝናብ ስለሚጠበቅ ለጎርፍና ለመሬት መንሸራተት ተጋላጭ የሆኑ አከባቢዎች መለየታቸውን ዳይሬክተሩ ጠቁመዋል።
ከዚህ ጋር በተያያዘ በጋምቤላ 3 ዞኖች፣ ቤንሻንጉል ጉምዝ አሶሳ ዞን፣ በኦሮሚያ 12 ዞኖች፣ በአማራ 9 ዞኖች፣ አፋር 4 ዞኖች፣ በሱማሌ 10 ዞኖች፣ በትግራይ 4 ዞኖች፣ በደቡብ ብሔሮች፣ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል 14 ዞኖች፣ ሲዳማ ክልል፣ ድሬደዋ ከተማ አስተዳደር፣ ሐረሪ ክልል ሐረር ከተማ እንዲሁም አዲስ አበባ በጎርፍ ተጋላጭ መሆናቸውን አዲስ ማለዳ ማወቅ ችላለች።

በሌላም በኩል ከክረምቱ ጋር ተያይዞ በአማራ ክልል 4 ዞኖች፣ በኦሮሚያ 6 ዞኖች፣ በደቡብ 12 ዞኖች፣ እንድሁም በሲዳማና ትግራይ ክልሎች ላይ የመሬት መንሸራተት አደጋ ሊኖር እንደሚችል አብራርተዋል።
በአገሪቱ ላይ የሚከሰቱ የጎርፍ አደጋዎችን የመከላከልና ምላሽ የመስጠት ሥራ የብሔራዊ አደጋ ስጋት ሥራ አመራር ብቻውን የሚሠራው ሥራ ሳይሆን ከውኃ፣መስኖና ኢነርጂ ሚኒስቴርና ከተፋሰሶች ባለሥልጣን ጋር በጋራ መሠራት ያለበት እንደሆነ አስረድተዋል።
ዳይሬክተሩ ሥራው ከፌደራል፣ ከክልል እንዲሁም በጎርፍ ዙሪያ ከሚሰሩ አካላት ጋር በቅንጅት እየተሠራ መሆኑን ተናግረዋል። በተጨማሪም በተፋሰስ አካባቢ የሚገኙትን የአፋር፣ አማራ፣ ኦሮሚያና ሱማሌ ክልሎችን በዋናነት በማሳተፍ ጎርፍን ለመከላከል ወደ ትግበራ መገባቱን ጨምረዋል።

ባለፈው ዓመት በአፋር ክልል በደረሰው የጎርፍ አደጋ ምክንያት 45 ሚሊዮን ብር በመመደብ በጎርፉ አደጋ ተጠቂ በነበሩ አካባቢዎች ላይ ዳግም ጎርፉ ሰብሮ እንዳይወጣ ትቦዎችንና ድልድዮችን የመጠገን ሥራ አየተሰራ መሆኑን አብራርተዋል።
በተጨማሪም በአፋርና ሱማሌ ክልሎች ላይ አደጋው ቢያጋጥም አፋጣኝ እርመጃ ለመውሰድ እንዲቻል 4 ጀልባዎች ለመግዛት በሂደት ላይ እንደሚገኝ ገልጸዋል። እንዲሁም በአማራ ክልል ባለፈው ዓመት ጎርፍ ተከስቶባቸው የነበሩ አከባቢዎችን (በተለይም ደንቢያ) የአደጋ ተጋላጭነት ለመቀነስ ግድቦች እየተሰሩ መሆናቸውን አስታውሰዋል።

በተመሳሰይ፣ ከተሞች ላይ የውኃ ተፋሰሶች ላይ በጋራ መሥራት የሚያስፈልግ ሲሆን፣ ማሕበረሰቡም በመንገዶች ላይ የሚስተዋሉ ተገቢ ያልሆኑ የቆሻሻ አወጋገድ ልማዶችን በማስወገድ ለፍሳሽ መተላለፊያ ትቦዎች ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚገባ አመልክተዋል። አክለውም ኢትዮጵያን እየጎዳት ያለው የማታውቀው አደጋ ሳይሆን የተለመዱ አደጋዎች መሆናቸውን አውቀን ልንማር ይገባል ብለዋል።

ከክልሎች የጎርፍ አደጋ ቅድመ ዝግጅት ጋር በተያያዘ የተፋሰስ ልማት ባለሥልጣን የቅድመ ዳሰሳ ጥናትን መሰረት በማድረግ የጎርፍ ስጋት አለባቸው ተብለው በተለዩ ሰባት ክልሎች ላይ በ600 ሚሊዮን ብር የጎርፍ ቅድመ መከላከያ ሥራዎች እየተሠሩ መሆኑን አዲስ ማለዳ ለማወቅ ችላለች።


ቅጽ 3 ቁጥር 141 ሐምሌ 10 2013

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com