የእለት ዜና

የአብረን እንሥራ ጥሪውና የፓርቲዎች ዕይታ (አዲስ መንገድ)

Views: 2105

ለሦስት አስርት ዓመታት በብዙ ቅሬታዎች እና ትችቶች ያለፈው የኢትዮጵያ ፓርላማ አሁን ላይ በአዲስ አደረጃጀት እና ስልት ይቀየራል ሀሳቦች ከወዲሁ መሰማታቸውን ተከትሎ ብዙ ተስፋ ተጥሎበታል፡፡
ቀድሞ በፓርላማው ውስጥ የነበሩ የበዙ ችግሮችን ቀርፎ በአዲስ መልክ ይመጣል ተብሎ የሚጠበቀው አዲስ አደረጃጀት በስሩ በጣት የሚቆጠሩ የተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች ተካተውበታል፡፡
በአዲሱ ፓርላማ አብዛኛውን መቀመጫ ያገኘው ገዥው ፓርቲ በምርጫው የተሳተፉ ፖለቲካ ፓርቲዎችን በየደረጃው ባሉ የመንግሥት ተቋማት ለማሳተፍ ማሳቡን ጠቁሟል፡፡ ከዚህ በፊት ያልተለመደ አዲስ መንገድ መምጣቱ እንደ መልካም ጅምር እየታየ ይገኛል፡፡
የፖለቲካ ፓርቲዎችን ለማካተት የታሰበው አዲስ መንገድ የዜጎችን ፍላጎትና መተባበር በሚጠናክር ሁኔታ በደራጀት እንዳለበት ከወዲሁ እየተጠቆመ ነው፡፡ የአዲስ ማለዳው ወንድማገኝ ኃይሉ የባለሙያዎችን ሀሳብ አካቶ ጉዳዩን የሐተታ ዘማለዳ ርእሰ ጉዳይ አድርጎታል፡፡

ላለፉት ግማሽ ክፍለ ዘመናት የአገሪቱ ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ በሆነ መንገድ በነጻ ፈቃዱ የመረጠው መንግሥት ይኖረው ዘንድ ብዙ ሙከራዎች ሲደረጉ ቢቆዩም በተለያዩ ምክንያቶች ሲሰናከሉ ነበር።
በሂደቱ በርካታ ተማሪዎችና ወጣቶች፣ ገበሬዎችና የቤት እመቤቶች፣ ምሁራንና መለዮ ለባሾች፣ በአጠቃላይ መላው የአገሪቱ ሕዝብ ከፍተኛ ዋጋ ከፍሏል። ባለፉት ያልተሳኩ የዴሞክራሲ ተሞክሮዎች ጠባሳ ሰበብ፣ የአሁኑም ምርጫ ዴሞክራሲያዊነቱ ተጠብቆ ባይጠናቀቅስ? ብጥብጥ እና አለመረጋጋት ቢፈጠርስ? በሚሉ ስጋቶች ያለፉት ወራት እንደ አገር በፍርሃት ወጥመድ ውስጥ የተገባባቸው እንደነበሩ ይታወቃል።

ይሁን እንጂ ኢትጵያውያን የተሰጋውን ሳይሆን የሚፈልጉትን ማድረግ እንደሚችሉ አሳይተዋል። በሂደቱም ዜጎች ዝናብና ፀሐይ ሳይገድባቸው፣ በረጃጅም ሰልፎች ሳይሰለቹ፣ እስከ እኩለ ሌሊት ታግሰው በስድስተኛው አገራዊ ምርጫ ሰኔ 14/2013 ፍላጎታቸውን በካርዳቸው ገልጸዋል።

ከዚህ ባሻገር በብዙ ውሱንነቶች ውስጥ አልፈው፣ በዴሞክራሲና በሕዝብ ድምፅ ላይ ባላቸው ጽኑ እምነት፣ ሐሳብና ፖሊሲያቸውን ለሕዝብ አቅርበው ብርቱ ውድድር ያደረጉ ተፎካካሪ ፓርቲዎች የዴሞክራሲያዊ ሂደቱ ድል አድራጊዎች ናቸው ተብሎላቸዋል።
ይህንን ምርጫ ልዩና ታሪካዊ የሚያደርጉት ብዙ ጉዳዮች ቢኖሩም፣ በውስጡ ግን ከዚህ ቀደም በነበሩ ምርጫዎች ተደርገው የማይታወቁ፣ ምርጫውን ኢ-ዴሞክራሲያዊ የሚያስብሉ ችግሮች እና በርካታ ቅሬታዎች እንደነበሩበት በፖለቲካ ፓርቲዎች በኩል ተገልጿል።
በአንጻሩ በአዎንታዊ መልኩ መንግሥት ካነሳቸው ጉዳዮች መካከልም የምርጫ ፍርድ ቤት መቋቋሙ እና ምርጫዉ ቁጥራቸው የበዙ የግልና የመንግሥት ሚዲያዎች፣ የሲቪል ተቋማት፣ የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን፣ ፍርድ ቤቶችና ሌሎችም ተቋማት በግልጽ የተከታተሉት መሆኑ ከመቼም ጊዜ በላይ ተአማኒነቱን የተጠበቀ እና ፍትሐዊ ምርጫ እንዲሆን ማድረግ መቻሉን ነው።

በሌላ በኩል ደግሞ በስድስተኛው አገር አቀፍ ምርጫ ላይ የተስተዋሉና ከአንድ መቶ ሥልሳ በላይ የምርጫ ጣቢያዎች ላይ የፖለቲካ ፓርቲዎች ያቀረቧቸው የተለያዩ ቅሬታዎች እና አቤቱታዎች ለቦርዱ ትልቅ ተግዳሮት ሆኖበትም አልፏል።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የስድስተኛውን አገር አቀፍ ምርጫ ውጤት ባለፈው ሳምንት ይፋ ማድረጉ ይታወሳል። ከዚህ ጋር ተያይዞም የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ፓርቲያቸው ምርጫውን ማሸነፉን ተከትሎ በምርጫው ለተሳተፉ ለተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች የአብረን እንሥራ ጥሪ ማቅረባቸው ይታወቃል።

ታዲያ ይህ ከዚህ ቀደም በነበረው በኢትዮጵያ የምርጫ ታሪክ ሂደት ተስተውሎ የማያውቀውን እና ያልተለመደውን የአብረን እንሥራ ግብዣ ፓርቲዎች እንዴት ተመለከቱት ስትል አዲስ ማለዳ የተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎችን አነጋግራለች።
የእናት ፓርቲ ዋና ጸኃፊ ጌትነት ወርቁ ለአዲስ ማለዳ እንደተናገሩት፣ ከዚህ ቀደም በነበረው የምርጫ ታሪክ ያልነበረ እና ፈጽሞ ያልተሰማ ጥሪ በመሆኑ አስደሳች እንደሆነ ጠቁመዋል።

ይልቁን ከዚህ በፊት የተለመደው በምርጫ ማግስት ምርጫውን መቶ በመቶ አሸንፈናል በማለት የበዛ ሆታ የሚሰማበት፣ ተቃዋሚዎች ወደ እስር ቤት የሚወረወሩበት፣ መራጩ ሕብረተሰብ ድምጼ ተዘረፈ በሚል ወደ አለመረጋጋት የሚገባበት እንደሆነ አስታውሰዋል።
አሁን ላይ ይህ የተሰማው አስደሳች ዜና ለኢትዮጵያ ብርቅ ነው ያሉት ጌትነት፣ መንግሥት የወሰደው እርምጃ ሊደነቅ የሚገባ ተግባር ነው ሲሉም አሞካሽተዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አሕመድ ያቀረቡት ሐሳብ የሰለጠነ እና ለፍጹም ዴሞክራሲያዊ አሠራር የተዘጋጁ መሆኑን የሚያሳይ እንደሆነም ጌትነት አንስተዋል።

ብልጽግና የሚያሸነፍ ከሆነ የተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች በአስፈጻሚው አካል በኩል ገብተው የራሳቸውን አስተዋጽኦ እንዲያበረክቱ እናደርጋለን ማለታቸው ገንቢ ሐሳብ ነው በማለት አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።
ያሉትን ባያደርጉት እንኳ ይህን ማሰባቸው በራሱ እጅግ የሚያስደስት ነው ብለዋል የፓርቲው ዋና ጸኃፊ።

በፓርቲያቸው ውስጥ በርካታ ምሁራን እና ልምድ ያላቸው እንዳሉ ገልጸው፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሚጋብዙን ከሆነ እጅግ አመርቂ በሆነና አረአያ ሊሆን በሚችል መንገድ የተሰጠንን ቦታ ከሙስና በጸዳና ሰዓትን ባከበር መለኩ ለአገር ጠቃሚ የሆኑ እቅዶችን በማቀድ እና መንግስት ያወጣውን ፖሊሲ ተግባራዊ በማድረግ ቁርጠኛ በሆኑ ባለሙያዎችችን በኩል ለመስራት ዝግጁ ነን ሲሉ ተደምጠዋል።
ይህ ጥሪ በምርጫ ማግስት መሆኑ ለአፍሪካ ብሎም ለዓለም ትልቅ ትምህርት የሚሰጥ ነው ሲሉ ገልጸዋል።

የተቃዋሚ ፓርቲዎች እና መንግሥት ኢትዮጵያ ከገባችበት አዘቅት ውስጥ እንድትወጣ እጅ ለእጅ ተያይዘው ለመሥራት እና በአንድነት ሆ ብለው ለመነሳት መፈለጋቸው አገሪቱን በከፍታ ማማ ላይ ሊያስቀምጣት ይችላል ሲሉ ሐሳቡን በበጎ ወስደውታል።
ይሁን እንጂ፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ብልጽግና እና መንግሥትን ወክለው ይህን ጥሪ ቢያደርጉም፣ የፖለቲካውን ምህዳር በሚገባ ማስፋት ላይ ሊሠራበት ይገባል ይላሉ።
ከምርጫ በፊት የነበሩ በርካታ ችግሮች እና መሰል አይነ ጥላዎችን ከኢትዮጵያ መግፈፍ እንደተቻለ የጠቀሱት ጌትነት፣ ይህ እንዲሆንም ፓርቲቸው የበኩሉን አስተዋጽኦ እንዳበረከተ አንስተዋል።
አሁን አሁን በምርጫ፣ ኢትዮጵያ እና ብጥብጥ ተለያይተው ምርጫ አና ኢትዮጵያ ብቻ የድል ጉዟቸውን ጀምረዋል ነው ያሉት።
ከዛሬ አምስት አመት በኋላ የሚደረገው ምርጫም ከዚህ የተሻለ ሊሆን እንደሚችል ግምታቸውን አስቀምጠዋል።

ጳጉሜን ላይ የትግራይ ክልልን ሳይጨምር ከሰማኒያ በላይ ለሚሆን ወንበር ምርጫ ይደረጋል ያሉት ዋና ጸሀፊው፣ ከሰማኒያ ወንበር ውስጥ ሀያው ወንበር እንኳ በተቃዋሚ ፓርቲዎች እጅ ውስጥ የሚገባ ከሆነ የተሻለ አደረጃጀት ለመፍጠር ያስችላል ይላሉ።
በኢትዮጵያ ውስጥ ለበርካታ ዓመታት አስተዳደራዊ በደል ስር ሰዶ እንደነበር አውስተው፣ አንዳንድ ባለሥልጣናት ተቋማት ላይ ለተቀመጡበት ወንበር ሳይመጥኑ ደሃውን ሕዝብ ለእንግልት እና ስቃይ ሲያዳርጉ ከርመዋል ሲሉ የቀድሞውን ስርአት ተችተዋል።
ይሁንና ይህ አሁን ላይም እንዳይቀጥል ስጋት አለኝ ያሉት ጌትነት፣ እነዚህ እና መሰል ችግሮች ለጠቅላይ ሚኒስትሩ እና ለብልጽግና ብቻ የሚተው ስላልሆነ ሁላችንም ኃላፊነት አለብን፤ የሁላችን እዳ ናት ኢትዮጵያ ብለዋል።
ኢትዮጵያ ላይ የተከመረውን ውዝፍ እዳዋን መቅረፍ አለብን ሲሉም የእናት ፓርቲ ዋና ጸኃፊው ተናግረዋል። ይሁን እንጂ በሥልጣን ስም ብልጽግናን ከመጠጋት ይልቅ በበጎ ፈቃደኝነት አገርን እና ሕዝብን በማገልገል የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት ማስጠበቅ በይደር የሚቆይ እንዳልሆነም አመልክተዋል።

ኢትዮጵያ እውነትም አሸንፋለች ስንል እንደ አገር ትልቁን ምስል በማየት ነው የሚሉት ደግሞ የአፋር ሕዝብ ፓርቲ ሊቀ መንበር ሙሳ አደም ናቸው።
አገር እና ሕዝብ ከምንም በላይ ናቸው በማለት ከመቼውም ጊዜ በላይ በቁርጠኝነት መሥራት እንደሚገባ ጠቅሰዋል።
የቀረበው ሐሳብ ከዚህ ቀደም በኢትዮጵያ ታሪክ ያልተለመደ እና ለብዙዎቻችን እንግዳ የሆነ ነው ያሉት ሙሳ፣ አሁን የተጀመረው መልካም አካሄድ አገርን ያሳድጋል እንጂ ጉዳት አይኖረውም ብለዋል።
እንደ ዴሞክራሲ አካሄድ ይህ በጎ ጅምር ነው በማለት ጉዳዩ በቀላሉ ሊታይ የሚገባው ነገር አይደለም በማለት የጠቅላይ ሚኒስትሩን ጥሪ አድንቀዋል።
የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ /አብን/ ምክትል ሊቀመንበር የሱፍ ኢብራሂም በበኩላቸው፣ ይህ ጥሪ ለአገሪቱ የሚበጃት፣ ለጋራ በጋራ ወደፊት የሚያራምዳት እና ሐሳብ በማዋጣት በአንድነት እንድንሰራ የሚያደርግ ነው ሲሉ አስተያየታቸውን ሰንዝረዋል።

የአገርን ዘላቂ ጥቅም እና ፍላጎት ከግምት ውስጥ ያስገባ አገራዊ ትብብር ያስፈልጋል ያሉት ምክትል ሊቀመንበሩ፣ ጉዳዩ የሥልጣን ግብ ግብ መሆን የለበትም ነው ያሉት።
“አሁን ላይ እርስበርስ አብረው ሊሰሩ እና ሊስማሙ የማይችሉ ኃይሎች ድንገት ተነስተው የሽግግር መንግስት የሚያቋቁሙበት ምህዳር አይደለም” ሲሉ የሱፍ ገልጸዋል።
ሥልጣን በመያዝም ይሁን ኃላፊነትን በመውሰድ፣ ተባብሮ ለመሥራትና ለአገር ጠቃሚ የሆነውን ሁሉ ለማድረግ በመካከላችን ያሉትን ችግሮችን እና አለመግባባቶችን ወደ ጎን መተውና ለአገር ሉዓላዊነት እና አንድነት በጋራ መቆም አለብን ብለዋል።
የጠቅላይ ሚኒስተሩ ግብዣ አገሪቱን ወደ አንድ የዕድገት ምዕራፍ የሚያሸጋግራት ድልድይ እና የዕድገት መሰላል ነው በማለት የጠቅላይ ሚኒስትሩን የአብረን እንስራ ጥሪን በበጎ ወስደውታል።
ሕዝብን ወክለው ፓርላማ የሚገቡ የተፎካካሪ ፓርቲዎች አዲስ እና ገንቢ ሐሳቦችን ማምጣትና ማሳየት አለባቸው ተብሏል።

ወደ ፓርላማ የገቡ ተፎካካሪ ፓርቲዎች ቁጥር አነስተኛ ቢሆንም፣ በቀጣይ አምስት አመታት አገሪቷን እና ሕዝቦቿን ወደ ተሻለ የሽግግር ምዕራፍ ለማድረስ ገንቢ ሐሳቦችን በማመንጨት ጠቃሚ ሥራዎችን መሥራት እንዳለባቸው በዲላ ዩኒቨርሲቲ የታሪክ እና ዓለም አቀፍ ጉዳዮች ረዳት ፕሮፌሰር የሆኑት አብዱ መሐመድ (ዶ/ር) ተናግረዋል።

ይሁን እንጂ አዳዲስ ሐሳቦችን የማምጣት ግዴታዎች የተፎካካሪ ፓርቲዎች ብቻ ሳይሆን አጠቃላይ ሕዝብን ወክለው ወደ ፓርላማ የገቡ ኹሉም ተወካዮች የጋራ ሥራ መሆኑን አመልክተዋል።
መስከረም ላይ የምናያቸው እና ፓርላማ የሚገቡ የተፎካካሪ ፓርቲ ተወካዮች በጣም ውስን በመሆናቸው ያን ያክል የጎላ ተጽዕኖ ሊኖራቸው ይችላል ተብሎ አይገመትም ብለዋል።
እነዚህ ውሱን ተወካዮች አጀንዳ የማስያዝ አቅሙ ወይንም መብቱ እንደሌላቸው ገልጸው፣ ነገር ግን ሕዝብን ወክለው እንደመግባታቸው ኹሉ የራሳቸውንና ከዚህ በፊት በተቃውሞ ጎራ ተሳታፊዎች ላይ ያላየነውን አዲስ ነገር እንዲያሳዩ እንጠብቃለን ነው ያሉት።
ይህ ኃላፊነት ለተፎካካሪ ፓርቲዎች ብቻ የሚተው እንዳልሆነ የገለጹት ምሁሩ፣ ዴሞክራሲ የሚገነባው በጋራ ስለሆነ የገዢው ፓርቲ ብልጽግናን ወክለውም ሆነ በግል ተወዳድረው ፓርላማ የገቡ አካላትም ሚናቸውን በአግባቡ መወጣት እንዳለባቸው ጠቁመዋል።

እንደ አብዱ ገለጻ በኢትዮጵያ ያለፉት አምስት ፓርላማዎች በርካታ ክፍተቶች ነበሩባቸው። እነዚያ አምስቱ ፓርላማዎች ለስም የሕዝብ ተወካዮች ይባሉ እንጂ የፓርቲ ተወካዮች ምክር ቤት ሆነው ነው ያለፉት።
በድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካል ሳይንስ እና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ትምህርት ክፍል መምህር እና የትምህርት ክፍሉ ኃላፊ የሆኑት አሰፋ ካሳ በበኩላቸው፣ የሕዝብን ድምጽ አግኝተው ወደ ፓርላማ የገቡ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ የወከሉትን ማሕበረሰብ ሐሳብ እና ድምጽ ከመንግስት ፖሊሲ እና ስትራቴጂ ጋር በማዛመድ መሞገት እና ጠቃሚ የሆኑ ሐሳቦችን ማበርከት እንደሚኖርባቸው ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል።

የሕዝብን ድምጽ ያገኙ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች የፓርላማ አባል ሆነው ሥራ ከጀመሩ በኋላ የሚጠበቅባቸው የወከሉትን ሕዝብ በታማኝነት ማገልገል መሆኑን አጽንኦት ሰጥተውበታል።
ሕዝቦች ደግሞ ሐሳባቸውን፣ ጭንቀታቸውን እና ችግሮቻቸውን ከማሰማት ባለፈ መፍትሄ እንዲበጅላቸው ይፈልጋሉ ያሉት ምሁሩ፣ ተወካዮች ይህን መሰረት በማድረግ ድምጻቸውን በአግባቡ ሊያስተጋቡላቸው ይገባል ብለዋል።
ተወካዮቹ የግል ሐሳባቸውን ከማንጸባረቅ በመቆጠብ የወከላቸውን ሕዝብ ድምጽ በማንጸባረቅ ብዝኃነት ያለበት ፓርላማ እንዲኖር ማድረግ እንዳለባቸው ምሁራኑ ጠቁመዋል ።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የስድስተኛውን አገር አቀፍ ምርጫ ውጤት ይፋ ማድረጉን እና ፓርቲያቸው ምርጫውን እንዳሸነፉ የሚገልጽ የድል ብስራት ዜና ማሰማቱን ተከትሎ ባደረጉት ንግግር “ፓርቲያችን በሕዝብ ይሁንታ አግኝቶ አገር ለማስተዳደር መመረጡ አስደስቶናል” ብለዋል።

ነገር ግን፣ መንግሥት የሚመሠረተው በሕዝብ በተመረጡ ፓርቲዎች ቢሆንም፣ አገርን መምራትና ማስተዳደር ግን ለተመረጡ ፓርቲዎችና መሪዎች ብቻ የሚተው አይደለም ሲሉ አስረድተዋል።
ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎችና መሪዎቻቸውም እስከሚቀጥለው ምርጫ በመንግሥት አስተዳድርና ሕዝብን በማገልገል ሂደት ውስጥ ሚናቸው ሰፊ ሊሆን እንደሚገባ አስታውሰዋል።
በቀጣይ ወራት ብልጽግና በሚመሠርተው መንግሥት ውስጥ በአስፈጻሚው አካልም ሆነ በፍርድ ቤቶች፣ በሌሎችም የፌደራልና የክልል ተቋማት ላይ ንቁ ተሳትፎ እንዲኖራቸው፣ በዘንድሮው ምርጫ በኃላፊነትና በብቃት የተወዳደሩ የሕዝብ አለኝቶችን ከዚህ በፊት ካተደረገው በእጅጉ ከፍ ባለና አዎንታዊ ለውጥ በሚፈጥር መልኩ እንደሚካተቱ ገልጸዋል።

በተጨማሪም እስከሚቀጥለው ምርጫ የበለጠ ተጠናክረውና ተቋማዊ አቅማቸው ደርጅቶ ብርቱ ተወዳዳሪ እንዲሆኑ አስፈላጊውን ድጋፍ ኹሉ ከማድረግ ወደ ኋላ አንልም ብለዋል።
በዚህ ምርጫ የፈጠርነው አሸናፊና ተሸናፊን ሳይሆን፣ ጠያቂና ተጠያቂ ያለበት የዴሞክራሲ ሥርዓትን ነው። በዚህ ደግሞ ያሸነፉት በምርጫው የተሳተፉት ኹሉም አካላት ናቸው ሲሉም ጠቅላይ ሚኒስትሩ አብራርተዋል።
አያይዘውም ከዚህ ቀደም እንደነበረው አይነት መንግሥት ኢትዮጵያ ደግማ እንድትፈጥር ማድረግ የለብንም ነው ያሉት።እኛ ምንፈልገው ከየፓርቲው የተሻሉ የሚባሉ ሰዎች በካቢኔ ውስጥ፣ በየኤጀንሲው እና በየክልሉ እየገቡ አገርን እና ሕዝብን እንዲያገለግሉ ነው ሲሉም አስረድተዋል።

ተቃዋሚ ፓርቲ የሆኑትን በሙሉ ወድቃችኋል እና ጠብቁ አንልም ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ነገር ግን በተለያዩ ምክንያቶች ያልተሳተፉ ፓርቲዎች ከዚህ በኋላ አምስት አመታትን እንዲጠብቁ ይገደዳሉ እንጂ የዚህ ጥሪ ተሳታፊ አይሆኑም በማለት ተናግረዋል።
ከዛ ባሻገር በወድድር ውስጥ ያለፉት በሙሉ በየደረጃው በአስፈጻሚ ውስጥ እና በተለያየ ተሳትፎዎች ውስጥ ጠንካራ እና አገር የሚያሸጋግር መንግሥት ለመፍጠር አብረን እንሠራለን ብለዋል።
ይህ ከዚህ ቀደም በነበሩት አምስት የፓርላማ ታሪኮች እና በኢትዮጵያ የፖለቲካ የሥልጣን ዘመን ታይቶ እና ተሰምቶ የማያውቀው የመንግሥት ከተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር በጋራ የእንስራ ጥያቄ አስደሳች መሆኑን የተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲዎች ገልጸዋል። ይህ አገርን የመለወጥ እና ከዚህ ቀደም የነበረውን ችግር የመቅረፍ ዘመቻ መሬት ወርዶ እንዴት ይተገበር ይሆን የሚለውን ጊዜ ይፈታዋል።


ቅጽ 3 ቁጥር 141 ሐምሌ 10 2013

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com