የእለት ዜና

አዲስ የሚመሰረተው መንግሥት ተጠያቂነት ላይ መሥራት እንዳለበት ተጠቆመ

አዲስ የሚመሰረተው መንግሥት ተጠያቂነትን ማስፈን ላይ በቁርጠኝነት መሥራት እንደሚጠበቅበት የኮተቤ ሜትሮፖሊታን ዩኒቨርሲቲ የታሪክና ሕግ ባለሙያ አልማው ክፍሌ(ዶ/ር) ጠቁመዋል።
ከኹለት አስርተ ዓመታት በላይ ኢትዮጵያን ያሥተዳደረው ‘ኢህአዴግ’ መራሹ መንግሥት አገርና ሕዝብን ያላስቀደመ እንደነበር ያስታወሱት የሕግ ባለሙያው፣ ስርዓቱ ለሕዝቦች አብሮነት እንዲሁም የዜጎችን ከቦታ ቦታ ተዘዋውሮ የመሥራት መብትን በተጨባጭ ማስከበር ተስኖት መቆየቱን ነው የገለጹት።
በመሆኑም አዲስ የሚመሰረተው መንግሥት የሕዝቦችን አብሮነት በማጎልበትና የዜጎችን መብቶች በማስከበር ረገድ በቁርጠኝነት ሊሰራ እንደሚገባም ጠቁመዋል። ለዚህ ደግሞ ግልጽነትና ተጠያቂነት ያለው አሠራርን ማስፈን ወሳኝ መሆኑን ነው ያብራሩት።
ኢትዮጵያ ከውጭ አገራት ጋር ያላትን ግንኙነት ይበልጥ ማጠናከር የሚያስችሉ ዲፕሎማሲያዊ ሥራዎችን ማከናወን እንደሚጠበቅበትም ጨምረው ገልጸዋል። ከዚህ አንጻር የኢትዮጵያን ጥቅም ማስከበር የሚችሉና የመደራደር አቅም ያላቸውን ዲፕሎማቶች ወደ ኃላፊነት ማምጣት ይገባል ነው ያሉት።
የአምባሳደሮችን ሹመት ጨምሮ በዘርፉ ያሉ ሌሎች አሰራሮች ሊፈተሹ እንደሚገባም አልማው ጠቁመዋል። አመራሩ ወጣቶችን በማስተባበር ኢትዮጵያ ያላትን ለም መሬትና ውሃ ለልማት ብሎም በምግብ ራስን ለመቻል ማዋል ላይ ከፍተኛ ኃላፊነት እንዳለበትም ተናግረዋል። ይህም እየተባባሰ ያለውን የኑሮ ውድነት በመቅረፍ ረገድ ሚናው የጎላ መሆኑን ነው አልማው የገለጹት።


ቅጽ 3 ቁጥር 141 ሐምሌ 10 2013

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com