የእለት ዜና

አገራዊ ምርጫው ከመነሻው ጀምሮ ዴሞክራሲያዊ እንደነበር ተገለጸ

የአዲስ ትውልድ ፓርቲ ፕሬዝደንት ሰለሞን ታፈሰ፣ የዘንድሮውን ጠቅላላ ምርጫ ክንውን ተከትሎ የፓርቲያቸውን አቋም በማስመልከት መግለጫ ሰጥተዋል።
ፓርቲው ስድስተኛው ጠቅላላ ምርጫ ከመነሻው ጀምሮ ሰላማዊ፣ ፍትሃዊና ዴሞክራሲያዊ መሆኑን ጠቅሰው፣ በሂደቱ ዴሞክራሲያዊ የክርክር መድረክ የታየበትና ሰፊ የሚድያ ሽፋን ያገኘ እንደነበር ገልጸዋል።
ፓርቲዎች ተንቀሳቅሰው አማራጮቻቸውን ለሕዝብ በመሸጥ ዕመርታ የታየበትና መራጩ ሕዝብም በነጻነት እስከ ምሽት ስድስት ሰዓት ድረስ የመረጠበት መሆኑን ገልጸዋል። የምርጫ ሂደቱ ለሌሎች የአፍሪካ አገራትም ተምሳሌት ሆኖ ማለፉንም አዲስ ትውልድ ጠቁሟል።
አልፎ አልፎ የተፈጠሩ ችግሮችም ከኹሉም ፓርቲዎች ጋር በጋራ ምክር ቤት እና ከምርጫ ቦርድ ጋር በመነጋገር ለቀጣዩ ምርጫ ብዙ ነገሮችን ተምረን እንድናልፍ አድርገዋል ብሏል ፓርቲው። አዲስ ትውልድ ፓርቲ በመግለጫው “ኢትዮጵያዊያን ኹለት አገር የለንም አንድ አገር ነች ያለችን፤ ማንም ያሸንፍ አገራችን ኢትዮጵያ የጠላቶቿን አንገት አስደፍታ አሸንፋለች እና ልንኮራ ይገባል” ብሏል።
ፓርቲያቸው የምርጫውን ውጤት በጸጋ እንደተቀበለው የገለጹት አቶ ሰለሞን፣ ሕዝቡም ይህንኑ ተገንዝቦ ለአገር ልማት እና እድገት በጋራ እንዲቆም ጠይቀዋል። ፓርቲው በውድድሩ አሸናፊ ባይሆንም፣ ከአሸናፊው ፓርቲ ጋር በቀጣይ በብሔራዊ መግባባት ላይ እንዲሁም አገራዊ የሆኑ ግዙፍ ፕሮጀክቶች ላይ በጋራና በትብብር ይሰራል ብለዋል።


ቅጽ 3 ቁጥር 141 ሐምሌ 10 2013

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com