የእለት ዜና

በወረባቦ ወረዳ ዘንድሮም የበረሃ አንበጣ ሰብል እያወደመ ነው

Views: 34

-ግብርና ሚኒስቴር በወረዳው የኬሚካል እርጭት ማድረግ አልቻልኩም ብሏል

በአማራ ክልል በደቡብ ወሎ ዞን ባለፈው የምርት ዘመን የበረሃ አንበጣ ተከስቶ ከፍተኛ ጉዳት አድርሶበት በነበረው ወረባቦ ወረዳ ሰሞኑን የተከሰተው የአንበጣ መንጋ በአርሶ አደር ሰብል ላይ ዳግም ጉዳት እያደረሰ መሆኑን አርሶ አደሮች ለአዲስ ማለዳ ገለጹ።
ከዚህ ከቀደም ባልተለመደ ሁኔታ በዚህ ወቅት የተከሰተው የበረሃ አንበጣ መንጋ በወረዳው የለሙ የሰብል እህሎችን እያወደመ መሆኑን አርሶ አደሮች ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል። የበረሃ አንበጣው ከፍተኛ ጉዳት ማድረስ የጀመረው ከባለፍው ሐምሌ 5/2013 ጀምሮ መሆኑን አርሶ አደሮቹ ጠቁመዋል።

በወረዳው የሚገኙ አርሶ አደሮች ያለሙት የሰብል እህል ገና በቡቃያ ላይ ያለ መሆኑን የጠቆሙት አርሶ አደሮቹ፣ መንጋው ካረፈበት ዳግመኛ ማገገም የማይችልበት የእድገት ደረጃ ላይ መሆኑን ጠቁመዋል። የበረሃ አንበጣው በወረዳው ተከስቶ በለሙ ሰብሎች ላይ ጉዳት እያደረሰ ቢሆንም፣ እስካሁን ድረስ በመንግሥት በኩል የመከላከል ሥራ አለመጀመሩ ጉዳቱን ሊያሰፋው እንደሚችል አርሶ አደሮች ጠቁመዋል።

በወረዳው የተከሰተውን የበረሃ እንበጣ በሰው ኃይል ለመከላከል የማይቻልበት ሁኔታ እየተፈጠረ መሆኑን ከወረዳው አርሶ አደሮች አንዱ የሆኑት አህመድ ያሲን ለአዲስ ማለዳ ጠቁመዋል። “ከተከሰተበት ጊዜ ጀምሮ እስካሁን ድረስ የመከላከል ሥራ በመንግሥት በኩል አልተሠራም፤ የበቀሉ ሰብሎች እየወደሙ ነው” ሲሉ አርሶ አደር አህመድ ተናግረዋል።

የግብርና ሚኒስቴር በበኩሉ በወረዳው የበረሃ አንበጣ መከሰቱን አምኖ፣ የሄሊኮፕተር ኬሚካል ርጭት ማካሄድ አልቻልኩም ብሏል። ሚኒስቴሩ በወረዳው የተከሰተውን የበረሃ አንበጣ መከላከልና የኬሚካል ርጭት ማድረግ ያልቻለው የተከሰተው መንጋ እያረፈ ያለው በመንደሮችና በውኃ አከባቢዎች መሆኑን ተከትሎ መሆኑን በግብርና ሚኒስቴር የእጽዋት ጥበቃ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር በላይነት ንጉሴ ተናግረዋል።

እንደ ዳይሬክተሩ ገለጻ ግብርና ሚኒስቴር የበረሃ አንበጣ በወረዳው መከሰቱን መስማቱን ተከትሎ የሄሊከፕተር ኬሚካል ርጭት ለማድረግ ቢሞክርም፣ አንበጣው መንደር ውስጥና ውኃ አካባቢ በማረፉ ከጥቅሙ ጉዳቱ ሊያመዝን ስለሚችል የኬሚካል ርጭት ማድረግ አልተቻለም ብለዋል።

በወረዳው የተከሰተው የበረሃ አንበጣ ከሰኔ 20/2013 ጀመሮ ከጊዜ ወደ ጊዜ የመንጋ መጠኑን እያሰፋ መጥቶ አሁን ላይ በተዘሩ ሰብሎች ላይ፣ በቁጥቋጦዎች እንድሁም በግጦሽ ላይ ጉዳት እያደረሰ መሆኑ ተገልጿል። አርሶ አደሮቹ በባህላዊ መንገድ ማሕበረሰቡን በማስተባበር አንበጣው ጉዳት እንዳያደርስ እየተከላከሉ ቢሆንም፣ ጉዳቱን ማስቀረት አልተቻለም ተብሏል።

መንግሥት መከላከል የሚቻልበት ሁኔታ ተፈጥሮ የኬሚካል ርጭት እስከሚያደረግ ድረስ አርሶ አደሩ በተደረጃ የሰው ኃይል ሰብሉን ከጉዳት እንድከላከል በላይነህ አሳስበዋል። ግብርና ሚኒስቴር የበረሃ አንበጣ በተከሰተባቸው አከባቢዎች ኹሉ የኬሚካል ርጭት ማድረግ የሚችልበት ሁኔታ ካለ ጉዳት ከመድረሱ ቀድሞ ለመከላከል እንደሚሰራ ተመላክቷል።

በአማራ ክልል ምስራቃዊ ክፍል፣ በአፋር አዋሳኝ አከባቢዎች የበረሃ አንብጣ መከሰቱን የጠቆሙት በላይነህ፣ ግብርና ሚኒስቴር በማንኛው አካባቢ የሚከሰት ጉዳትን ለመከላከል ከባለፈው ዓመት የተሻለ አቅም ፈጥሮ እየሠራ መሆኑን ጠቁመዋል። የበረሃ አንበጣ እንደተከሰተ ግብርና ሚኒስቴር ወዲያውኑ ደርሶ መከላከል በማይችላባቸው ሁኔታዎች አርሶ አደሩ የመከላከል ሥራዉን አጠናክሮ መቀጠል አለበት ብለዋል። በአማራ ክልል የተከሰተውን የበረሃ አንበጣ ለመከላከል ከከልሉ መንግሥት ጋር በቅርበት እየተሠራ መሆኑ ተመላክቷል።
የበረሃ አንበጣው አፋር ክልል ከሚፈለፈለው በተጨማሪ ከሶማሊያ እና ከጅቡቲ የገባ እንደሆነ በላይነህ ጠቁመዋል። አሁን ላይ የተከሰተው የበረሃ አንበጣ ወደ ትግራይ ክልል እየገባ መሆኑንም ነው በላይነህ አክለው የገለጹት። ግብርና ሚኒስቴር የአየር ላይ አሰሳ በማድረግ የኬሚካል ርጭት ለማድረግ እየሠራ መሆኑ ተገልጿል።

ባለፈው ዓመት የተከሰተው የበረሃ አንበጣ በግብርና ምርት ላይ ተጽኖ መሳደሩ የሚታወስ ሲሆን፣ የዘንድሮው አንበጣ መንጋ በባለፈው ዓመት ልክ ጉዳት እንደማያስከትል በላይነህ ጠቁመዋል።


ቅጽ 3 ቁጥር 141 ሐምሌ 10 2013

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com