የእለት ዜና

ብሔራዊ ባንክ ለክፍያ ሥርዓት ኦፕሬተሮች ፈቃድ ሊሰጥ መሆኑን ገለጸ

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ይፋ ባደረገው የናሽናል ዲጂታል ፔይመንት ስትራቴጂ ስር በተካተተ አዲስ መመሪያ መሰረት ከ10 በላይ ለሆኑ ተቋማት ፍቃድ ለመስጠት የታሰበ ሲሆን፣ በቅርቡ አብዛኛዎቹ ወደ ሥራ ይገባሉ ተብሏል።
የፋይናንስ ዘርፉን ለማሳደግ የግል ተቋማትን በማሳተፍ ማሻሻያ ያደረገው ብሔራዊ ባንክ ባንኮች በዲጂታል ፋይናንስ አገልግሎት ላይ እንዲሰማሩ ምቹ ሁኔታ እየፈጠረ እንደሚገኝ የባንኩ የክፍያ ሥርዓትና ሴትልመንት ዳይሬክተር ማርታ ኃይለማርያም አስረድተዋል።
በዚህም መሰረት ለባንኮች ብቻ ይፈቀድ የነበረውን የዲጂታል ባንክ አገልግሎት፣ ባንክ ላልሆኑ ለአገር ውስጥ የክፍያ መፈጸሚያ ሰነድ እና ለክፍያ ሥርዓት ኦፕሬተሮች ፍቃድ እየሠጠ ይገኛል ብለዋል።

የዲጂታል ክፍያ አገልግሎት በአጠቃላይ ከግለሰብ ጀምሮ እስከ መንግሥት በተለይም በፋይናንስ ዘርፍ ውስጥ ትልቅ አስተዋጽኦ እንዳለው ይታወቃል።
ዲጂታል ፋይናንስ በኢትዮጵያ በጅምር ደረጃ ላይ ቢሆንም የክፍያ አገልግሎትን ለኹሉም የሕብረተሰብ ክፍል በቀላሉ፣ በአነስተኛ ወጪ እና በጊዜ እንዲሁም አስተማማኝ በሆነ መልኩ በማድረስ፣ የፋይናንስ አገልግሎት ተጠቃሚዎችን ፍላጎት በመጨመር የፈይናንስ ዘርፉን ዓለም አቀፍ ውድድር ውስጥ ለማስገባት ታቅዷል ሲሉ ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የአገራችን የፋይናንስ ዘርፍ በመምራት እና በመቆጣጠር ይታወቃል። የአገሪቱን የክፍያ ስርዓት በተመለከተ በፈረንጆቹ አቆጣጠር 2011 የብሔራዊ ሲስተም አዋጅ በማውጣትና በተግባር በማዋል በኹሉም ባንኮች ደንበኞች አማካይነት ከአንዱ ባንክ ወደ ሌላ ባንክ የሚደረጉትን የክፍያ ትዕዛዞች ወድያውኑ ክፍያው እንዲፈጸም የሚስችል ሥርዓት ዘርግቶ እያስተዳደረ ይገኛል።
ብሔራዊ ባንክ ባሳለፍነው ሳምንት ሀሙስ ቀን የብሔራዊ ዲጂታል ክፍያ ስትራቴጂን በይፋ ሥራ ማስጀመሩ ይታወሳል።

የብሔራዊ ዲጂታል ስትራቴጂ ደህንነቱ የተጠበቀ፣ ጥሬ ገንዘብን የሚጠቀምና የፋይናንስ አካታችነትን የተላበሰ ኢኮኖሚ እንዲኖር የማገዝ ዓላማን መያዙን ማርታ አስረድተዋል። ይህን ተከትሎ ሲስተም ኦፕሬተር ፍቃድ ከሚሰጣቸው ተቋማት መካከል አንዱ አሪፍ ፔይ የተሰኘ ሞባይል መተግበሪያ ይገኝበታል።

ሞባይል መኒ አንድ የጥሬ ገንዘብ ወደ ቨርቹዋል ኤልክትሮኒክ የሚቀይር ሲሆን፣ ሲስተም ኦፕሬተር ደግሞ ያለንን የባንክ አካውንት ክፍያ ስረዓት መፈጸም የሚያስችል ነው።
እንደነዚህ አይነት ሥርዓት መጠቀም ባንክ ያለንን ገንዘብ ሞባይል መኒ ሳይከፈት ቀጥታ ከባንኩ ጋር የሚያገናኝ ነው ሲሉ የአሪፍ ፔይ ፋይናንሻል ቴክኖሎጂ ሼር ካምፓኒ መስራች ሀብታሙ ታደሰ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።
ባንካችን ጋር ባለን ገንዘብ ቴክኖሎጂውን በመጠቀም ማንኛውም አይነት ክፍያ መክፈል ያስችላል ብለዋል።

አሪፍ ፔይ በቅርቡ ፍቃድ ከሚሰጣቸው ተቋማት አንዱ ሲሆን ፍቃድ ለማግኘት 4 ወር ያህል በሂደት ላይ እንደነበር ሀብታሙ ጠቁመዋል።
አሪፍ ፔይ ወደ ሥራ በሚገባበት ጊዜ የታክሲ ራይድ አገልግሎት፣ የኦንላይን ግብይት እና የመንግሥት ተቋማት ክፍያዎችን ለመፈጸም ያስችላል።

ይህን መሰል ቴክኖሎጂ ኢትዮጵያ ውስጥ ባለመኖሩ እንደ አዲስ ቴክኖሎጂ አቅራቢ ፈተና ሊገጥመን እንደሚችል ጥያቄ የለውም ሲሉ አብራርተዋል። ዓመት ያልሞላው አዲስ የዲጂታል መመሪያ እንደመሆኑ መጠን ትግበራው ተግዳሮት ሊኖረው ይችላል ተብሏል።
የብሔራዊ ባንክ መመሪያ ከመውጣቱ በፊት ቴክኖሎጂ ቀድሞ በመምጣቱ ልክ መመሪያው እንደወጣ በአጭር ጊዜ ውስጥ ወደ ተግባር ለመግባት ችለናል ሲሉ ነው ሀብታሙ የገለጹት።

ዲጂታል ኢኮኖሚ መፍጠር አስፋለጊ መሆኑ የሚታወቅ ሲሆን፣ አዲሱ ስትራቴጂ በመንግሥት ተቋማት ያሉ ዝግ አሰራሮችን የሚከፍት ስለሆነ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን ለመተግበር መዘጋጀት ያስፈልጋል ብለዋል። ተቋማቱ በሚፈጠርላቸው አዳዲስ ቴክኖሎጂ አቅራቢዎችን መርጠው አገልግሎታቸውን በጋራ ለሕዝብ ማድረስ ይችላሉ።

የውጭ ትልልቅ ፊንቴክ ተቋማት እየመጡ እንደመሆኑ መጠን እንደ እነሱ ጀማሪ ለሆኑ ቴክኖሎጂ አቅራቢዎች ተጽእኖ ስለሚኖረው ስጋት እንዳለባቸው ገልጸዋል።
አሪፍ ፔይ በኢትዮጵያውያን የተሰራ ሲሆን፣ መንግሥትም በማበረታቻዎች ሊደግፈን ይገባል ሲሉ ገልጸዋል።
አሪፍ ፔይ የራሱ ዳታ ሴንተር ያለው በመሆኑ ሙሉ በሙሉ ደህንነቱ የተጠበቀ ነው ሲሉ መስራቹ ተናግረዋል።


ቅጽ 3 ቁጥር 141 ሐምሌ 10 2013

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

error: Content is protected !!