የእለት ዜና

ኢትዮ ቴሌኮም በ41 ሚሊዮን ዶላር ወጪ የሲስተም ማሻሻያ ማድረጉን ገለጸ

Views: 63

ኢትዮ ቴሌኮም ‹ኔክስት ጀነሬሽን ቢዝነስ ሰፖርት› የተባለውን ሲስተም ለማሻሻል 41 ሚሊዮን ዶላር ወጪ ማድረጉን የተቋሙ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ፍሬሕይወት ታምሩ ገለጹ።
የቢዝነስ ሰፖርት ሲስተም ፕሮጀክት አንደኛው የቴሌኮም የልብ ምት ነው የሚሉት ሥራ አስፈጻሚዋ፣ ቴክኖሎጅው አጠቃላይ የደንበኞች ፕሮፋይል የሚመዘገብበት፣ ታሪፍ የሚወጣበትና ቻርጅ የሚደረግበት ነው ብለዋል። ይህ ቴክኖሎጂ የአገልግሎት ዘመኑን በመጨረሱ መተካቱ አስፈላጊ ነበር። በመሆኑም ኹሉንም ደንበኞችን የሚያስተናግደውን ትልቅ ቴክኖሎጂ ለማሻሻል 41 ሚሊዮን ዶላር ወጪ ተደርጓል ብለዋል።

ኢትዮ ቴሌኮም ከፍተኛ መዋዕለ ንዋይ የፈሰሰባቸው የኢትዮ ቴሌኮም መሰረተ ልማቶችን በማስፋፈት እና በማጠናከር የኔትወርክ ሽፋንና አቅምን ለማሳደግ፣ እንዲሁም የገቢ ምንጭ ለማግኘት የሚረዱ 132 ፕሮጀክቶች በማከናወን ላይ ይገኛል። ከእነዚህ ፕሮጀክቶች መካከል የ4ጂ ኔትወርክ አድቫንስድ ማስፋፊያዎች፣ የሞባይል ጣቢያዎች ማስፋፊያ፣ ስማርት ፖሎች ተከላን ጨምሮ ሞጁላር ዳታ ሴንተር ግንባታ፣ እንዲሁም የቢዝነስ ሰፖርት ሲስተም ፕሮጀክትን ማሻሻል ይጠቀሳሉ። የሚሻሻለው ሲስተም 80 ሚሊየን ደንበኞችን ማስተናገድ የሚችል አቅም ያለው ሲሆን፣ በሰከንድ 41ሺ 800 ትራንዛክሽን ፕሮሰስ ያደርጋል።

በቅርቡም ወደዚህ አዲስ ሲስተም ደንበኞች ይገባሉ ተብሏል። በአሁኑ ሰዓት የተወሰኑ አካባቢዎችን በመምረጥ የሙከራ ሥራ እያደረገ ነው ሲሉ ፍሬህይወት ገልጸዋል። ይህ አዲስ ሲስተም ተቋሙ በ2022 ላሰበው የ5ጂ ቴክኖሎጂ አገልግሎትን ማስተናገድ የሚችል አቅም እንዲኖረው ተደርጎ የተሠራ ነው ሲሉ አብራርተዋል።

ከዚሁ ጋር በተያያዘ፣ በዓለም አቀፍ ሕግ መሠረት ማሟላት ያለበትን መስፈርት ባሟለ መልኩ የራሳችን ዳታ ሴንተር አልነበረንም የሚሉት ሥራ አስፈጻሚዋ፣ ሞጁላራይዝ ዳታ ሴንተር በመገንባት በርካታ አገልግሎት እየተሰጠ ይገኛል ብለዋል። ይህ ዳታ ሴንተር በዋናነት የቴሌብር አገልግሎት የሚሰጥ ሲሆን፣ ኹለት የተለያዩ መሆናቸውም ታውቋል።

ኹለተኛው ዳታ ሴንተር የመጀመሪያው አገልግሎት ቢቋረጥ ተጠቃሚ ሳያውቀው አገልግሎቱን የሚያስቀጥል ነው። በከፍተኛ ሁኔታ የተቋሙን ወጪ ይቀንሳል የተባለለት ይህ ዳታ ሴንተር ወደ ገበያ የሚወጡ አገልግሎቶችን በአጭር ጊዜ ለማስፈጸም የሚረዳ አስተማማኝ አገልግሎት መሆኑ ተገልጻል። ተቋሙ የነበረብኝን ስጋት ቀርፎልኛል ያለው ዳታ ሴንተር በተደጋጋሚ ሲገጥመው የነበረውን የመቆራረጥ ሁኔታ የቀነሰና የበርካታ ደንበኞች ትራንዛክሽን የሚያስቀምጥ ነው።

ከዚህ በፊት አንድ ዳታ ሴንተር አዲስ አበበ ላይ የነበረ ቢሆንም፣ አገልግሎቱ ሲቋረጥ ሙሉ ሲስተሙ ይቋረጥ ነበር። የኢትዮ ቴሌኮም መሰረተ ልማቶች ውስጥ የአገልግሎት ዘመናቸውን የጨረሱ ሲስተሞችን ለመተካት በጣም ከፍተኛ የሆነ የውጭ ምንዛሬ ይጠይቃሉ።
ኢትዮ ቴሌኮም እየተከናወኑ ባሉ ከ74 በላይ በሆኑ የመንግሥት የልማት ፕሮጀክቶች ምክንያት መሰረተ ልማቶቼ ተስተጓጉለውብኛል ብሏል። በዚህ መስተጓጎል ጊዜያዊ መሰረተ ልማት ለመትከል፣ለመቀጠልና ቋሚ ለማድረግ 166 ሚሊዮን ብር ድረስ ወጪ ማውጣቱ ተሰምቷል። ይህ ገንዘብ ለደንበኞች አገልግሎት ቢውል ኖሮ 93ሺሕ አዳዲስ የብሮድባንድ ተጠቃሚዎችን ማፍራት ይቻል ነበር ተብሏል።

ኢትዮ ቴሌኮም ካሰባቸው 132 ግዙፍ ፕሮጀክቶች ውስጥ በፈረንጆቹ 2020/21 ላይ 119 ሚሊዮን ዶላር እና 2.7 ሚሊዮን ዩሮ ወጪ የተደረገባቸውን ማሳካት መቻሉን አስታውቋል።
በተያያዘም የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ክፍያ እና የትራፊክ ቅጣትን መክፈል የሚያስችል ሙሉ በሙሉ በሞባይል ቴክኖሎጂ የታገዘ ክፍያ ሊሰጥ መሆኑም ተነስቷል። ኢትዮ ቴሌኮም ከእነዚህ ተቋማት ጋር ሥራውን የሚሰራው በቅርቡ ይፋ ባደረገው የቴሌብር ሞባይል መኒ ሲሆን፣ ለዚህም ይረዳ ዘንድ ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ፣ ከአቢሲኒያ ባንክ እና ከአዋሽ ባንክ ጋር እየሠራ ይገኛል።

ኢትዮ ቴሌኮም የኤሌክትሪክ አገልግሎት በስፋት ከሚጠቀሙ ተቋማት አንዱ ቢሆንም፣ ኤሌክትሪክ ማግኘት በማይችልባቸው ቦታዎች በበጀት ዓመቱ 22 በመቶ የተቋሙ ጣቢያዎች ሶላርን በመጠቀም ሲሠሩ መቆየታቸውን ፍሬሕይወት ገልጸዋል። ከፕሮጀክቶቹ መካከል በዋናነት የሚጠቀሰው የ4ጂ አገልግሎት ሲሆን፣ በ2013 አዲስ አበባ ላይ ውስን ቦታዎች ላይ ነበር። በአሁኑ ሰዓት 68 የክልል ከተሞች ላይ እና በአዲስ አበባ በኹሉም ስፍራ አገልግሎቱን ማዳረስ ችሏል።


ቅጽ 3 ቁጥር 141 ሐምሌ 10 2013

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com