የእለት ዜና

በሆሮ ጉድሩ ወለጋ ሦስት ወረዳዎች ሰዎች እየተገደሉና ንብረት እየተዘረፈ መሆኑን ነዋሪዎች ገለጹ

Views: 79

በኦሮሚያ ክልል ሆሮ ጉድሩ ወለጋ ንጹሐን ዜጎች በታጣቂ ኃይሎች እየተገደሉ፣ እየተፈናቀሉና ንብረታቸው እየተዘረፈ መሆኑን ኗሪዎች ለአዲስ ማለዳ ገለጹ።
አዲስ ማለዳ ከአካባቢው ነዋሪዎች እንደሰማቸው ባሳለፍነው ሰኞ ምሽት በሆሮ ጉድሩ ወለጋ ደንጎሮ በምትባል ወረዳ፣ ጃርቲ ቀበሌ ስምንት ንጹሐን ዜጎች በታጣቂ ኃይል ጥቃት ተገድለዋል ተብሏል። ሰኞ ምሽት ላይ በተፈጸመው ጥቃት ከሞቱት ሰዎች በተጨማሪ ቁጥራቸው በውል ያልታወቀ ሰዎች መቁሰላቸው ተገልጿል።

በሆሮ ጉድሩ ወለጋ በተደጋጋሚ በንጹሐን ዜጎች ላይ የታጠቀ ኃይል በሚፈጽመው ጥቃት ተማረው አካባቢውን ለቀው የተፈናቀሉ ዜጎች ንብረት በተደራጁ አካላት እየተዘረፈና እየተቃጠለ መሆኑን የአዲስ ማለዳ ምንጮች ጠቁመዋል። የተፈናቃዮች ንብረት እየተዘረፈና እየተቃጠለ ያለው በጊዳ አያና ወረዳና በሊሙ ወረዳ መሆኑ ተመላክቷል።

በአከባቢው ከዚህ በፊትም ጥቃቶችና ዘረፋዎች እንደነበሩ የሚያስታውሱት የአዲስ ማለዳ ምንጮች፣ ከሰሞኑ የተፈናቀሉ ዜጎችን ንብረት መዝረፍና ማቃጠል እንዲሁም፣ እስካሁን ያልተፈናቀሉ ዜጎችን የማፈናቀል ተግባር ተባብሶ ቀጥሏል ብለዋል። ከዚህ ቀደም በተለያዩ ጊዜያት በተፈጸሙ ጥቃቶች ቤት ንበረታቸውን ጥለው የተፈናቀሉ የሊሙና ጊዳ ወረዳ ኗሪዎች ወቅቱ የእርሻ ስዓት በመሆኑ አካባቢው በጸጥታ ኃይል ተጠብቆ ወደ አካባቢያቸው እንደመለሱ ይደረግ ዘንድ ቢጠይቁም አልተሳካም ተብሏል።
የተፈናቀሉ ዜጎች የእርሻ ጊዜ ሳያልፍ የመመለስ ፍላጎት ቢኖራቸውም፣ ከሰሞኑ የተፈጠረው ጥቃትና የንበረት ዘረፋ ካሰቡት በተገላቢጦሽ እንደሆነባቸው ተጠቁሟል።

በሊሙ ወረዳ የጥቃት ሰለባ ሆነው የተፈናቀሉ ዜጎች ቤት እየተዘረፈና እየተቃጠለ መሆኑን ለአዲስ ማለዳ የገለጹት የአከባቢው ኗሪዎች፣ ችግሩ የተፈጠረው በአከባቢው የጸጥታ አካለት አለመኖራቸውን ተከትሎ ነው ብለዋል። ከዚህ በፊት በአከባቢው የነበረው የጸጥታ አስከባሪ አካባቢውን ለቆ መውጣቱን ተከትሎ የታጠቁ ኃይሎች የተፈናቃዮችን ንብረት ከመዝረፍና ከማቃጠል አልፈው ተደራጅተው የተፈናቃይ አርሶ አደሮችን መሬት እያረሱ ነው ተብሏል።

በሌላ በኩል በተፈጠረ የጸጥታ ችግር ቤት ንብረታቸውን ጥለው የተፈናቀሉ ዜጎች መንግሥት እንዳልተቀበላቸው እና ምንም አይነት የሰብዓዊ ድጋፍ እያገኙ እንዳልሆነ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።
በምስራቅ ወለጋ በተደጋጋሚ በታጣቂ ኃይል በሚደርስ ጥቃት ቤት ንብረታቸውን ጥለው የተፈናቀሉ አርሶ አደሮች ርቀው መሄድ ያልቻሉት በአቅራቢያቸው አንጻራዊ ሰላም ወደ አለበት አከባቢ ቢሸሹም፣ ተቀብሎ ያስተናገዳቸው የመንግሥት አካል እንደሌለ ነው የገለጹት። ከጊዳ አያና ወረዳ አርቁንቢ መንደር አንድ፣ አርቁንቢ መንደር ኹለት፣ አርቁንቢ መንደር ሦስትና አርቁንቢ መንደር አራት የተፈናቀሉ ዜጎች በአሁኑ ጊዜ ከጥቃት ሸሽተው አንገር ጉትን ከተማ ላይ ይገኛሉ።

ይሁን እንጅ የተፈናቀሉ ዜጎችን እንደ ተፈናቃይ የሚቀበል እና መሰረታዊ የሚባሉ የመጠለያና ምግብ አቅርቦት ድጋፍ የሚያደርግ የመንግሥት አካል እስካሁን እንደሌለ ነው የተገለጸው። አንገር ጉትን ከተማ የሚገኙ ተፈናቃዮች ለአዲስ ማለዳ እንደገለጹት ከሆነ፣ እስካሁን በማሕበረሰቡ ትብብር በየበረንዳው ተጠልለው እንደሚገኙ ተናግረዋል።


ቅጽ 3 ቁጥር 141 ሐምሌ 10 2013

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com