የእለት ዜና

ከአላማጣ ለተፈናቀሉ ሰዎች በቂ ድጋፍ እየቀረበ አይደለም ተባለ

Views: 97

ሰሞኑን ህወሓት በከፈተው ጥቃት ከራያ አላማጣ ተፈናቅለው በቆቦ መጠለያ ካምፖች የሚገኙ ተፈናቃዮች ድጋፍ እየቀረበላቸው እንዳልሆነ ተናገሩ።
ከቀናት በፊት መከላከያና የአማራ ክልል ልዩ ኃይል አካባቢውን ለቆ መውጣቱን ተከትሎ የህወሓት ታጣቂዎች አካባቢውን ተቆጣጥረውት ነበር። ይህን ያልተጠበቀ ለውጥ ተከትሎ ለሕይወታቸው ስጋት ያደረባቸው ነዋሪዎች አላማጣን ለቀው በአቅራቢያ ወደምትገኘው ቆቦ ከተማ ገብተዋል።

አዲስ ማለዳ በቆቦ መጠለያ ካምፕ የሚገኙ ነዋሪዎችን እንዳነጋገረችው ከሆነ ለተፈናቃዮቹ በመንግሥት በኩል የተደረገላቸው ድጋፍ የለም።
አሁን ላይ በአካባቢው ባለው የጸጥታ ችግር ምክንያት ወደ አካባቢያቸው ለመመለስ የደህንነት ስጋት እንዳለባቸው የገለጹት ተፈናቃዮቹ፣ ከሰብዓዊ ድጋፉ በተጨማሪ የሠላም እና ደህንነቱ ስጋት አሳሳቢ ሆኖብናል ነው ያሉት።
ስለዚህም የክልሉ እና የፌዴራል መንግሥት ወደ ቀድሞ ሠላማችን ሊመልሱን ብሎም ዘላቂ የመፍትሄ አቅጣጫ ሊያስቀምጡልን ይገባል ሲሉ ጠይቀዋል። አክለውም በቀያቸው ቀድሞ የነበረው ሠላም እና መረጋጋት በመራቁ ከመቼውም ጊዜ በላይ ትኩረት ተሰጥቶበት ሊሠራ እንደሚገባ ተፈናቃዮቹ አንስተዋል።

“አሁን ባለንበት ቆቦ መጠለያ ውስጥ እኛም ሆንን ልጆቻችን ከጸጥታው ስጋት ውጪ በቂ ሰብዓዊ ድጋፍ እያገኘን አይደለም” ያሉ ሲሆን፣ ቀያቸውን በችኮላ ጥለው ስለወጡ የሚለብሷቸው አልባሳትን ጨምሮ አስፈላጊ ፍጆታዎች በቅጡ እየቀረቡልን አይደለም ብለዋል።
መንግሥት ወደ አካባቢው በመጣንበት ወቅት በቂ ያልሆነ እህል እና ድንኳኖችን ያቀረበ ቢሆንም፣ በጥቅሉ የሚደረገው ሰብዓዊ ድጋፍ አነስተኛ ነው ብለዋል።
አዲስ ማለዳም የተፈናቃዮችን ቅሬታ በመያዝ የከተማዋን ከንቲባ ካሳ ረዳን አነጋግራለች።

ከንቲባው ለቀረበላቸው ጥያቄ ሲመልሱ፣ አሁን ላይ ተፈናቃዮቹ ያቀረቡት ቅሬታ ተገቢ ነው ብለው፣ እየቀረበ ያለው ሰብዓዊ ድጋፍ በቂ አለመሆኑን አስረድተዋል።
ይሁን እንጂ በኹሉም ካምፖች ለሚገኙት ተፈናቃዮች በተቻለ እና አቅም በፈቀደ መጠን ድጋፍ ይደረጋል የሚል ምላሽ ሰጥተዋል።

ተፈናቃዮቹ ወደቦታችን ብንመለስ ለደህንነታችን እንሰጋለን ያሉትን ቅሬታ በተመለከተም፣ መንግሥት ስፍራውን በመቆጣጠሩ ምንም አይነት ስጋት ሊኖር እንደማይገባ ጠቁመዋል።
አያይዘውም፣ የአማራ ክልል ልዩ ኃይል ከሌሎች የጸጥታ ኃይሎች ጋር በመሆን አላማጣንና ዙሪያውን መቆጣጠሩን ገልጸው፣ ወደ ከተማዋም ተፈናቃዮቹን ለማስገባት አደረጃጀት ፈጥረን እስኪነሱ ነው የምንጠብቀው ሲሉ አብራርተዋል።
አሁን ላይ ቆቦ መቀመጫቸውን ያደረጉ የአላማጣ ከተማ ነዋሪዎች በቂ ድጋፍ ባይደረግላቸውም መንግሥት አላማጣን ነጻ በማውጣቱ በሕዝቡ ዘንድ መጠነኛ መረጋጋት እና ደስታ እየተስተዋለ መሆኑንም ከንቲባው ሳያነሱ አላለፉም።
ቀድሞ የነበራቸው የተፈናቃዮች ጥያቄም መከላከያ እና ልዩ ኃይል ወደ ከተማችን ይገባልን የሚል እንጂ የእህል እና ውሃ ጥይቄ አልነበረም ብለዋል።

በዚህም ረገድ አሁን አንጻራዊ ሠላም ስለመስፈኑ ከከተማው አስተዳደር መረጃ እያገኙ በመሆኑ ሰላማዊ ድባብ እየታየ መጥቷል በማለት የከተማዋን ወቅታዊ ሁኔታ አብራርተዋል።
የብሔራዊ አደጋ ስጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ደበበ ዘውዴ በበኩላቸው፣ ከሰሞኑን ህወሓት በፈጠረው አለመረጋጋት ምክንያት ሰብዓዊ ድጋፉን ለማድረስ የመንገዶች መዘጋጋት እክል ፈጥሮብናል ሲሉ ለአዲስ ማለዳ አስረድተዋል።
በነዚህ እና መሰል ምክንያቶች የተነሳ ለተፈናቃዮች ሰብዓዊ ድጋፍ ማድረግ አለመቻሉን ጠቅሰው፣ ከከተማው የአደጋ ስጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን ጋር በመነጋገር የመፍትሄ አቅጣቻዎችን እናስቀምጣለን ሲሉ አመልክተዋል።

ፌዴራል መንግሥት ያወጀውን የተናጥል የተኩስ አቁም ውሳኔ ተከትሎ፣ ይፋዊ ወረራ ከፍቶብኛል ያለውን ህወሓትን በግልጽ ማጥቃት መጀመሩን የአማራ ክልል መንግስት ማስታወቁ ይታወሳል።
ትህነግ ከስህተቱ ተምሮ ሕዝብን ከከፋ ስቃይ መታደግ ሲገባው በአማራ ክልል ግዛቶች ላይ መጠነ ሰፊ ወረራ ከፍቷል ሲል የክልሉ መንግሥት ኮምዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት መግለጫ ሰጥቷል።
የአማራ ክልል ልዩ ኃይል እና ሚሊሻ አባላት የህወሓት ታጣቂዎችን ወረራ ስልታዊ በሆነ መንገድ ለመከላከል ጥረት ሲያደርጉ መቆየታቸውን ገልጸው፣ ከዚህ በላይ ትዕግስት የከፋ ዋጋ ስለሚያስከፍል ከመከላከል አልፈን በግልጽ ማጥቃት ጀምረናልም ነው ያለው።


ቅጽ 3 ቁጥር 141 ሐምሌ 10 2013

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com