የእለት ዜና

ከቱሪዝም ዘርፍ የውጭ ምንዛሬ ገቢ አለመገኘቱ ተገለጸ

Views: 30

በበጀት ዓመቱ ከቱሪዝም ዘርፍ ምንም አይነት የውጭ ምንዛሬ ማግኘት አልተቻለም ተባለ።
በቱሪዝም ኢትዮጵያ የጽሕፈት ቤት ኃላፊ ፍጹም ካሳሁን ለአዲስ ማለዳ እንደገለጹት፣ የቱሪዝም ገቢ ከተለያዩ አገራት ከሚመጡ ጎብኚዎች የሚገኝ በመሆኑ የኮቪድ 19 ወረርሽኝ እና በአገሪቱ ያለው አለመረጋጋት ከዘርፉ ገቢ እንዳናገኝ ተጽዕኖ አሳድሮብናል ሲሉ ገልጸዋል።

በቱሪዝም ዘርፍ በ2030 በመንግሥት ታቅዶ የነበረው 10 ቢሊዮን ዶላር ገቢ ማስገባት ሲሆን፣ አመታዊ የጎብኚዎችን ቁጥርንም ደግሞ ወደ 7.2 ሚሊዮን ማድረስ ነው።
በዚህ ዓመት የታሰበውን ያህል እንኳ ባይሆን አነስተኛ የሚባል ቁጥር እንኳን ያለው ጎብኚ ባለመኖሩ የተገኘ ገቢ አለ ለማለት አይቻልም ሲሉ ፍጹም ጠቁመዋል።
የውጭ አገር ጎብኚ የማይገባ ከሆነ ገቢ ሊኖር የማይችል እና አንድ ቱሪስት ሲገባ ሊፈጥራቸው የሚችላቸው ለ11 ሰው የሚሆኑ የሥራ ዕድሎች እንዳልተፈጠሩ ይታሰባል። የኮቪድ 19 አይነት ዓለም አቀፍ ችግሮች ሲከሰቱ የአገር ውስጥ ቱሪስቶችን ማበረታት ያስፈልጋል

የሚሉት ፍጹም፣ ለዚህ ማበረታቻ የሚጎበኙ ቦታዎች ባሉበት ቦታ ያሉ ሆቴሎችን የማስከፈት እና የመቆጣጠር ሥራ ያስፈልጋል።
አጠቃላይ እንደ አገርም ሆነ በዓለም አቀፍ ደረጃ የቱሪዝም ዘርፉ ላይ በጣም ከፍተኛ ጉዳት ያስከተለው ኮቪድ 19 ወረርሽኝ መሆኑን ፍጹም አንስተዋል።
በአገር ደረጃ ከ114 በላይ የሚሆኑ የግለሰብ ሆቴሎች እና ከ500 በላይ ቱር ኦፕሬተር እንዳሉ ይታወቃል።

የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊው በአገር ደረጃ የ‹ናሽናል ሪከቨሪ ስትራቴጂ› ተቀርጾ ሲሰራ ቆይቷል ያሉ ሲሆን፣ በዓለም አቀፍ ደረጃም ኢትዮጵያ ለጉብኝት ምቹ ናት የሚለውን ለማስተዋወቅ ጥረት ተደርጓል ብለዋል።
አያይዘውም የቱሪስት አመንጪ የሆኑት እንደ ጣሊያን፣ ስፔን፣ አሜሪካና ጀርመን ያሉት ዐገራት በኮቪድ 19 ምክንያት የተጎዱ ናቸው። እንደገና ለማንሰራራት ኢንሹራንስ ያስፈልጋቸዋል። ኢትዮጵያ እንደ ሌሎች አገራት ለቱሪዝም ኢንሹራንስ የመስጠት አሠራር ልምድ ባለመኖሩ የገቢ ምንጩ ጉዳት ደርሶበታል ብለዋል።

በተያያዘ ዜና ቱሪዝም ኢትዮጵያ በፈንድ ማሰባሰብና ማስተዳደር ዙሪያ የተለያዩ ጥናቶች በማድረግ የቱሪዝም ልማት ፈንድ ረቂቅ አዋጅ አዘጋጅቷል።
ተቋሙ የቱሪዝም ልማት ፈንድ ረቂቅ አዋጅ በውስጥ ሙያተኞች ተዘጋጅቶ፣ በባለድርሻ አካላት ተሳትፎ ዳብሮ ለፓርላማ እንዲቀርብ ለጠቅላይ ሚ/ር ጽ/ቤት መላኩንም አዲስ ማለዳ ሰምታለች።
አዋጁን ለማስፈጸም የሚረዱ ደንብና መመሪያዎችን የማዘጋጀት ሥራም ተጀምሯል።

ለቱሪዝም ፈንድ ድጋፍ ማድረግ የሚችሉ የግል እና የመንግስሥት ድርጅቶች ተለይተው መቅረባቸው ታውቋል።
የቱሪዝም ፈንድ የሚንቀሳቀሰው በአጠቃላይ በመንግሥት በጀት ብቻ ነበር። በመንግሥት በጀት ብቻ ተንቀሳቅሶ የቱሪዝምን ፈንድ ማሳደግ ስለማይቻል የልማት ድርጅት አይነት ባህሪ ኖሮት ፈንድ እንዲሰበስብ እና እንዲያስተዳድር የኢትዮጵያን ቱሪዝም እንዲያስተዋውቅ ታስቦ የተሰራ የቱሪዝም ፈንድ አዋጅ ረቂቅ ነው።

ተቋሙ በአዋጅ ከተቋቋመ በኋላ የፈንድ ረቂቅ መዘጋጀት ነበረበት። ረቂቁ ጥናት ተደርጎበት ወደ ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ተልኮ ውይይት ከተካሄደበት በኋላ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ቀርቧል። ተቋሙ በነበረው አደረጃጀት የራሱ ፈንድ አልነበረውም የሚሉት ፍጹም፣ አዋጁ በአዲስ መልክ ተቋሙን ለማደራጀት የወጣ ሲሆን፣ ድርጅቱ ከዚህ በፊት የኢትዮጵያ ቱሪዝም ድርጅት በሚል መጠሪያ ተጠሪነቱ ለባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ሆኖ ሲሠራ ነበር ብለዋል።
አዲሱ አደረጃጀት ላይ ተቋሙ ሙሉ ለሙሉ ተጠሪነቱ ለጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት ሆኖ ሲደራጅ፣ ከነበሩት ተግባራት በተጨማሪ ሌሎች ሥራዎች ተሰጥተውታል።

አዲስ የሚጨመርለት ተግባርም የቱሪዝም ፈንድ ማሰባሰብና የማስተዳደር ኃላፊነት ያካታል።
ተቋሙ በበጀት ዓመቱ ካቀዳቸው የኢንቨስትመንት ተግባሮች አንዱ ሰንቀሌ ቆርኬዎች መጠለያ ሎጅ በ3ሚሊዮን ብር ወጪ መገንባት ነው።
ተቋሙ ከሚሰራቸው ሥራዎች ውስጥ አንዱ የማሕበረሰብ አቀፍ የቱሪዝም አገልግሎት መፍጠር ሲሆን፣ ይህ አገልግሎት ሲጀምር የየአካባቢው ማሕበረሰብ የራሱ ገቢ እንዲኖረውና በራሱ እንዲንቀሳቀስ የሚያደርግ ሥራ ነው ተብሏል።
ትልቅ አገራዊ ፕሮጀክት መሆኑን ያነሱት ፍጹም በተለይ የቆርኬ ማሕበረሰብ ገቢ እንዲኖራቸው ከማድረግ አንጻር ከPHE ጋር በመሆን የኮሚዩኒቲ ሎጅ ይገነባል።
የግንባታው ወጪ እና ዲዛይን ሥራ በቱሪዝም ኢትዮጵያ የሚሸፈን ሲሆን፣ የኮንትራክተር ሥራውን PHE የሚሠራ እንደሆነ ታውቋል።


ቅጽ 3 ቁጥር 141 ሐምሌ 10 2013

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com