የእለት ዜና

በኦሮሚያ 500 ግለሰቦች ከ‹ኤልአውቶ ኢንጅነሪንግ› መኪና ለመግዛት የገባነው ውል አልተፈጸመልንም አሉ

Views: 136

በኦሮሚያ ክልል 500 ግለሰቦች ከኤል አውቶ ኢንጅነሪንግ እና ትሬዲንግ ኃ/የተ/የግ/ማኅበር፣ በኦሮሚያ ክልል ኢንዱስትሪና ኢንተርፕራይዝ ቢሮ በኩል መኪና ለሚፈልጉ ግለሰቦች ለማቅረብ የመጀመሪያ ከፍያ 300 ሺሕ ብር ቢከፍሉም፣ በገቡት ውል መሰረት መኪና እንዳልቀረበላቸው መኪና ገዥዎች ለአዲስ ማለዳ ገለጹ።

የኦሮሚያ ክልል ኢንዱስትሪና ኢንተርፕራይዝ ቢሮ በክልሉ መኪና መግዛት የሚፈልጉና አቅም ያላቸውን ግለሰቦች በመለየት፣ በኤል አውቶ ኢንጅነሪንግ በኩል መኪና እንዲቀርብላቸው በመስማማት የካቲት 5/2013 መኪና መግዛት የሚፈልጉት ግለሰቦችና ኤል አውቶ ኢንጅነሪንግ የገዥና ሻጭ ውል ተፈራርመዋል።

መኪና ለመግዛት ውል ከፈረሙ ግለሰቦች መካከል ስማቸውን መግለፅ ያልፈለጉ በምስራቅ ወለጋ ነቀምት ኗሪ የሆኑ ግለሰብ ይገኙበታል። እኚህ ተዋዋይ መኪና ለመግዛት የመጀመሪያ ቅድመ ክፍያ በውሉ መሰረት 300 ሺሕ ብር እንደከፈሉ ለአዲስ ማለዳ ጠቁመዋል። እሳቸው እንደሚሉት ከሆነ ከነቀምት ከተማ ብቻ ከ13 በላይ ወጣቶች በወረዳ ደረጃ 23 ግለሰቦች መኪና ለማግኘት 300 ሺሕ ብር የመጀመሪያ ዙር ክፍያ ከፍለዋል።

ኤል አውቶ ኢንጅነሪንግ እና መኪና ለመግዛት የመጀመሪያ ዙር ክፍያ ማለትም 300 ሺሕ ብር የከፈሉ ግለሰቦች የተፈራረሙት ውል፣ ውሉ ከተፈጸመበት ቀን ጀምሮ እስከ ኹለት ወር ባለው ጊዜ ውስጥ ኤል አውቶ ኢንጅነሪንግ ለገዥዎቹ መኪና እንደሚያስረክብ ያስረዳል። በውሉ መሰረት ኤልአውቶ በተጠቀሰው ጊዜ ውስጥ መኪና ማቅረብ ካልቻለ ለገዥዎች 10 በመቶ የጉዳት ካሳ እንደሚከፍል ይገልጻል።

በተጨማሪም መኪና አቅራቢው በውሉ መሰረት ለገዥዎች መኪና ማቅረብ ካልቻለ፣ በየሦስት ወሩ የ300 ሺሕ ብር 10 በመቶ እንደሚከፍል በውሉ መካተቱን ገዥዎች ጠቁመዋል። ይሁን እንጅ መኪና ለመግዛት የመጀመሪያ ዙር ክፍያ የፈጸሙ ገዥዎች እስካሁን ድረስ በውሉ መሰረት የተከፈላቸው ክፍያ እንደሌለ ጠቁመዋል።

ቅሬታ አቅራቢዎቹ ለአዲስ ማለዳ እንዳሉት ከሆነ፣ በውሉ መሰረት የገዥና የሻጭ ግዴታዎች ከተከበሩ አሁንም መኪናቸውን መቀበል እንደሚፈልጉ ጠቁመዋል። ይሁን እንጅ ገዥና ሻጭ ከተፈራረሙት ውል ውጭ የሚኖር አሠራር ካለ በውሉ መሰረት የሚገባቸሰውን ክፍያ እንደሚጠይቁ ገለጸዋል።

ኤልአውቶ ኢንጅነሪንግ መኪናዎቹን ለገዥዎች የሚያቀርበው ከቀረጥ ነጻ በማስገባት እንደሆነ የኤላ አውቶ ኢንጅነሪንግ ሥራ አስኪያጅ በቀለ አበበ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል። ሥራ አስኪያጁ እንደሚሉት ከሆነ መኪኖቹን ለማስገባት ከቀረጥ ነጻ ለማስፈቀድ ጊዜ መውሰዱን ተከትሎ መኪኖቹ እስካሁን ወደ አገር ውስጥ መግባት ሳይችሉ ቆይተዋል ብለዋል። ከቀረጥ ነጻ የመፍቀድ ኃላፊነት የተሰጠው ገንዘብ ሚኒስቴር ባሳለፍነው ሰኔ ወር ላይ መኪኖቹ ከቀረጥ ነጻ እንዲገቡ መፍቀዱን በቀለ ጠቁመዋል። ገንዘብ ሚኒስቴር ከቀረጥ ነጻ እንዲገቡ የፈቀዳቸው መኪኖች 10 በመቶ ቀረጥ ከፍለው እንዲገቡ መሆኑንም በቀለ ጠቁመዋል።

በውሉ መሰረት መኪኖቹን በኹለት ወራት ውስጥ ማቅረብ ያልተቻለው ከቀረጥ ነጻ ሂደቱ በፈጠረው መዘግየት መሆኑን የጠቆሙት በቀለ፣ መኪኖቹን ለማስገባት በሂደት ላይ መሆናቸውን ለአዲስ ማለዳ ጠቁመዋል። መኪኖቹ ቀድመው የተገዙ መሆናቸውን ያስታወሱት በቀለ፣ ከአንድ ወር በኋላ መኪኖቹን በማስገባት ለገዥዎቹ የማስረከቡ ሂደት እንደሚጀመር ጠቁመዋል። በመሆኑም ብር የከፈሉ ገዥዎች ሂደቱ የዘገየበትን ምክንያት በመረዳት በትዕግስት እንዲጠብቁ አሳስበዋል።

በውሉ ላይ የተቀመጠው የጉዳት ማካካሻ ክፍያ በተመለከተ ከቅሬታ አቅራቢዎች የቀረበውን ጥያቄ የመክፈል ሂደት መጀመሩን በቀለ ጠቁመዋል። በቀለ ለአዲስ ማለዳ እንዳሉት ከሆነ የጉዳት ማካካሻ ከፍያ የተከፈላቸው መኖራቸውን ጠቁመዋል። ይሁን እንጅ ቅሬታቸውን ለአዲስ ማለዳ ያቀረቡ ገዥዎችን የጉዳት ካሳ እንዳልተከፈላቸው ጠቁመዋል።


ቅጽ 3 ቁጥር 141 ሐምሌ 10 2013

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com