‘አባታዊ ስርዓት’ የሴቶችና ወንዶች አፍ መፍቻ ቋንቋ

0
528

የስርዓተ ፆታ እኩልነት እንዲሰፍን የሚሠሩ ሰዎች የሚገጥማቸው አንዱ ፈተና በፆታዊ መድልዖው ውስጥ ተጠቂ የሆኑት ሴቶች ሳይቀሩ አድሏዊውን ስርዓት ጥብቅና የሚቆሙለት መሆኑ ነው። ሕሊና ብርሃኑ በነባራዊው ዓለም ውስጥ ገዢ የሆነው ‘አባታዊ ስርዓት’ ወንዶቹን ብቻ ሳይሆን ሴቶችንም ተገዢ እንዲሆኑለት አድርጎ ነው የሚቀርጻቸው በማለት ይከራከራሉ።

አብዛኛውን ጊዜ የሴቶች የእኩልነት ማኅበራዊ ንቅናቄዎችን ተከትሎ አልያም አዘውትረው የሚስተዋሉ የማኅበራዊ ብዙኀን መገናኛ ንትርኮች ላይ እኩልነትና ምርጫን የሚጋፉ በርካታ ተቃውሞዎች ከሴቶችም ጭምር ይሰነዘራሉ። በዚህም ሳቢያ አስተያየት ሰጪዎች “ይኸው ሴቶች ራሱ ይቃወሟችሁ የለ እንዴ?”፣ “ለውጡን ከነሱ ብትጀምሩ የተሻለ አይሆንም?”፣ “ከኛ እኮ እነሱ ባሱ!”፣ “በሉ መጀመሪያ እርስ በእርስ ተሥማሙ” የመሳሰሉ አስተያየቶችን ሲሰጡ ይስተዋላሉ። ኧረ ለመሆኑ እኩልነትን መቃወም፣ ተባዕታዊ የበላይነትን መደገፍ ወይም ፆታዊ መድልዖን መሠረት ያደረገ ማኅበረሰባዊ ድልድል ማውጣትን የወንዶች ብቻ ያደረገው ማነው?
ይህ የሁላችንም ችግር ነው፤ ያውም አፍ መፍቻ ቋንቋችን!
‘አባታዊ ስርዓት’ ምንድን ነው?
አባታዊ ስርዓት “ፓትሪያኪ” ከሚለው የዕብራይስጥ ስርወ ቃል የመጣ ሲሆን ነባር ትርጉሙም በወንድ የበላይነት ሥር ያለ ቤተሰባዊ አደረጃጀትን የሚያመላክት ነው።

የአባታዊ ስርዓት ስንል ዘመነኛ ትርጓሜው ወንድ ወይም አባት ማለት ሳይሆን፥ የኀይል አለመመጣጠንን፣ የደረጃ ማውጣት አባዜን፣በአጠቃላይ ስርዓታዊ የወንዶች የበላይነትን የመዘርጋት ዕሳቤ እና ድርጊትን ያካትታል። ይህ ስርዓት ፆተኛ (‘ሴክሲስት’) ማለትም የወንዶች የበላይነትን የሚደግፍና የሴቶች የበታችነትን ተፈጥሯዊ ሕግጋት በማሥመሰል የሚያስቀምጥ ነው። ጥልቅ የሆነና በተለያዩ የማኅበረሰባዊ መገለጫዎችን እና ሰበብ አስባቦችን የሚደግፍ በመሆኑ ወንዶችም ሆነ ሴቶች የዚህ ማኅበረሰባዊ ተፅዕኖ ተጋላጭ ናቸው። ፆተኛ የሚለው አገላለፅ ‘ፆታዊ መድልዖ’ ወይም ማዳላትን የሚያሳይ ሲሆን በዓለማችን ላይ የገነነውን የወንዶች የበላይነት እና ይህም ዕሳቤ ከአባታዊ ስርዓት ጋር ያለውን መመጋገብ ያሳያል። በነገራችን ላይ በወንድና በሴት ተፈጥሮ መካከል ልዩነት የለም ብዬ ስለማስብ ሳይሆን፥ ይህ ልዩነት ወይም የአንደኛው ወገን ተፈጥሮ የተሻለ ተደርጎ መታየቱና ማኅበራዊ ሽልማትን በሌሎች ትከሻ ላይ ተንጠልጥሎ ማጋበሱ ቁጣዩን ጉዳይ ስለሚቀሰቀስብኝ ነው።

የአባታዊ ስርዓት መገለጫዎች ምን እና እነማን ናቸው?
አባታዊ ስርዓትን ከወንዶች ጋር አንድ አድርጎ ማየት የተሳሳተ አመለካከት ነው። ይህ ስርዓት በሁሉም ድጋፍ የተገነባ ሲሆን እንደ ባሕል፣ ሃይማኖት፣ ቋንቋ ወይም ድርጅታዊ አሠራሮችን ታክኮ ብቅ የሚል ሰፊ ማኅበራዊ መዋቅር አለው። ስለሆነም ወንዶችም ሆነ ሴቶች ከአባታዊ ስርዓት ጋር ያላቸው ትሥሥር በተለየ እና በአሉታዊ መልኩ ታይቶ ሊወቀሱ አይገባም።
በመሆኑም “ጥያቄሽ ተገቢ አይደለምና አርፈሽ ተቀመጪ፣ አበስ ገበርኩ!”፣ “ወንድማ ወንድ ነው ድሮውንስ?” የሚለውን ተቀባብለው የሚዘፍኑ፣ ጥቅሙን ባይጋሩም አባታዊ ስርዓትን አለሁልህ የሚሉት፣ እንደ ዐሥርቱ ትዕዛዛት ፆተኝነትን የሚያጣቅሱ ብዙ ሴት ተከታዮች መኖራቸው የአደባባይ ምስጢር ነው።

ለምሳሌ ያህል በተለምዶ “ሴት ጓደኞች መጥፎ ናቸው፤ ወንዶች ናቸው ጥሩ” የሚሉና የሴቶች ማኅበራዊ ትሥሥርና ግንኙንትን ጥናት ላይ ያልተመሠረተ ግምታዊ ፆተኝነት የሚጭኑ፣ ያለ ዕድሜ ጋብቻን ስንቃወም “ወግ ነው ሲዳሩ ማልቀስ፣ ደስ ይላል በልጅነት ‘እስከነክብር’ ትዳር መያዝ” የሚሉ፣ አልያም እነርሱ ያመኑበትን ማኅበራዊ ማንነት አስገድዶ የጋራ ከማድረግ አልፎ በወንዶች ዘንድ ተወዳጅነትን ለማትረፍ የሌሎች ሴቶችን ምርጫ የሚያንቋሽሹ የአባታዊ ስርዓት እርካቦች ብዙ ናቸው።
ይህም ስሜት ከማኅበረ መስተጋብራዊ ትዝብት በተጨማሪ በጥናትም የተደረሰበት እውነታ ነው። ለምሳሌ ያህል በየአምስት ዓመቱ የሚካሔደው የማዕከላዊ ስታትስቲክስ ኤጀንሲ የሥነ ሕዝብ ጤና ጥናት ውጤት እንደሚያሳየው በቅርቡ እንኳን 63% የሚሆኑ ዕድሜያቸው ከ15-49 የሆነ ኢትዮጵያዊያን ሴቶች ባል ሚስትን ቢደበድብ አግባብ እንደሆነ ገልጸው፥ ባሎችን ሊያስቆጣ ይችላል ብለው ያሰቡትን (በማብሰል ወቅት ምግብ ማሳረርን ጨምሮ) የተለያዩ ምክንያቶችን አስቀምጠዋል።

እንዲህ ያሉ አመለካከቶች መገለጫቸው ቀላል ከሚመስሉ አስተያየቶች ጀምረው እስከ የሴቶችን ሰብኣዊ ክብር እና በሕይወት የመኖር መብት አደጋ ላይ የሚጥሉ፣ ለመስማት የሚከብዱ እርምጃዎችን ሲያስከትሉ ማየት የቀን ተቀን ኑሯችን ከሆነ ሰነባብቷል። ይህ እየሆነ አባታዊ ስርዓትና መገለጫዎቹን እንደ ቅንጦታዊ ምልከታ እና ውይይት የሚያዩት ሰዎች ብዙዎች ናቸው። “ፅድቁ ቀርቶ በቅጡ በኮነነኝ” እንዲሉ በአንድ ግንባር ተሰልፈን መታገሉ ቢያቅተን እንኳን በመሠረታዊ ሐሳቡ ላይ እንዴት መሥማማት ያቅተናል? ‘አካፋን አካፋ’ ብለን ችግሩን ካልጠቆምን ለመፍትሔውም ሳይንሳዊ መላ ሲሰነዘር መሥማት ከከበደን እኩልነትን ወይም የሰብኣዊ መብቶችን እንረዳለን ማለትስ አይከብድምን?

እንደእኔ ‘ፌሚኒስት’ ወይም የፆታ እኩልነት አቀንቃኝ መሆን የተለየ ዓለም ላይ መፈጠር ሳይሆን፣ ማንነት ተብሎ የተሠራልንን ድልድል በየጊዜው መጠየቅ፣ የተሻለ ለመሆን ንቁ ጥረት ማድረግ እንዲሁም ከተለያዩ ፆተኛ ልማዶቻችን ጋር የሚደረግ ግላዊ እርማትን ይጠይቃል። የዚህ ማኅበረሰብ ውጤት እንደመሆኔ እኩልነትን ብሻም የተባዕታዊ አገዛዝ መገለጫዎችን የቀን ተቀን ውሎና ሥራዬ ላይ በተለያዩ አጋጣሚዎች ብቅ ሲሉ አስተውላለሁ። “ተው ሽሸኝ አልሸሽም” ለኔም አልቀረልኝም።

ታዲያ እኩልነት ለማምጣትና የተሻለ ማንነትን ለመፍጠር የሚደረግ ጥረት ከሌለ በቀር ይህ ‘አባታዊ ስርዓት’ (ቅድመ መግባቢያ ‘አፍ መፍቺያችን’ እንደመሆኑ መጠን)ተንሠራፍቶ መቀጠሉ አይቀርም። ስለዚህም ለለውጥ ፈላጊ ወንድም ይሁን ሴት ዜጎች የአባታዊ ስርዓት ምንነትን በሚገባ ማወቅ ለእኩልነት ድርድሮቻችን እንዲሁም ለምንሻቸው ለውጦች በእጅጉ አስፈላጊ ነው።

ሕሊና ብርሃኑ የሕግ መምህርና የስርዓተ ፆታ ባለሙያ ናቸው። በኢሜይል አድራሻቸው bhilina.degefa@gmail.com ሊገኙ ይችላሉ።

ቅጽ 1 ቁጥር 31 ሰኔ 1 ቀን 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here