የእለት ዜና

በሀገር አቀፍ ደረጃ በትምህርት ብርሃን ምዘና ከ 446ሺህ በላይ ወጣቶችና ጎልማሶች ተመዝነዋል – ትምህርት ሚኒስቴር

የትምህርት ሚኒስቴር በዘንድሮው አመት ተግባራዊ በተደረገው የትምህርት ብርሀን ምዘና እንደ ሀገር ከ446 ሺህ በላይ ወጣቶችና ጎልማሶች መመዘናቸውን አስታወቀ።

የትምህርት ሚኒስቴር ሚኒስትር ደኤታ ዶ/ር ጌታሁን ጋረደው የጎልማሶች ትምህርትን ከዚህ በላይ ውጤታማ ለማድረግ በክረምት የወጣቶች በጎፍቃድ አገልግሎት ሀገር አቀፍ ንቅናቄ በሁሉም ክልሎች ይከናወናል ብለዋል፡፡

በዚህ የክረምት የወጣቶች የበጎ ፍቃድ አገልግሎት ንቅናቄ ማንበብ፣ መፃፍና ማስላት የማይችሉ ወጣቶችና ጎልማሶችን የማስተማር ስራ እንደሚሰራ ገልፀዋል።

መፃፍና ማንበብ የሚችሉትን ጎልማሶችንም ለቀጣይ የትምህርት ብርሃን ምዘና የማዘጋጀት እንዲሁም የክህሎት ስልጠና የሚሰጥባቸውን ቦታዎች የማመቻቸት ስራ እንደሚሰራም ሚኒስትር ዴኤታው ተናግረዋል፡፡

የ ዲቪቪ ኢንተርናሽናል (DVV International) የምስራቅ አፍሪካ ክልላዊ ዳይሬክተር የሆኑት ፍራውካ በበኩላቸው ኢትዮጵያ በጎልማሶችና መደበኛ ባለሆነ ትምህርት ዘርፍ እየሰራች ያለችውን ስራ አድንቀው በቀጣይ በስርዓት ግንባታ እና አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤትን መሰረት ያደረገ የጎልማሶች ትምህርት ላይ በትኩረት አብረን እንሰራለን ብለዋል፡፡

ዲቪቪ ኢንተርናሽናል የጀርመን መንግስታዊ ያልሆነ ድርጅት ሲሆን በሀገራችን የጎልማሶችና መደበኛ ያልሆነ ትምህርት ዘርፍ በርካታ ተግባራትን እያከናወነ እንደሚገኝ ታውቋል፡፡

የትምህርት ሚኒስቴር የጎልማሶችና መደበኛ ያልሆን ትምህርት ዘርፍ የ2013 ዓ.ም በጀት ዓመት እቅድ አፈፃፀምና የ2014 በጀት ዓመት እቅድ ላይ ውይይት እያደረገ እንደሚገኝ ከሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ያገኘነው መረጃ ያስረዳል፡፡

በመድረኩም ከሁሉም ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች የተውጣጡ የቢሮ ምክትል ኃላፊዎችና የዘርፉ ባለሙያዎች፣ የጎልማሶች ትምህርት እያሰለጠኑ ያሉ ዩኒቨርሲቲዎች እንዲሁም ከዲቪቪ ኢንተርናሽናል የተውጣጡ ባለሙያዎች እየተሳተፉበት እንደሚገኙም ታውቋል፡፡

 

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

error: Content is protected !!