የእለት ዜና

በአዲስ አበባ ከተማ በትራፊክ አደጋ ሳቢያ ይደርስ የነበረውን ሞት በ13 በመቶ መቀነስ መቻሉ ተገለፀ

በአዲስ አበባ ከተማ በትራፊክ አደጋ ሳቢያ ይደርስ የነበረውን ሞት 13 በመቶ በቀነስ መቻሉን የከተማዋ ትራፊክ ማኔጅመንት ኤጀንሲ አስታወቀ።

በአዲስ አበባ ከተማ በትራፊክ ግጭት ምክንያት ከሚደርሰው የሞት፣ የአካል ጉዳት እና የንብረት ውድመት ባሻገር ለከፋ ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ቀውስ እያስከተለ ይገኛል።

በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትራፊክ ማኔጅመንት ኤጀንሲም የትራፊክ አደጋን ለመቀነስ የሚያስችል የመንገድ ደህንነት ስትራቴጂን በመንደፍ ወደ ትግበራ መግባቱ ተገልጿል።

ይህ የመንገድ ደህንነት ስትራቴጂ ተግባራዊ በመደረጉ በየዓመቱ በትራፊክ ግጭት ሳቢያ የሚደርሰውን ሞት እና የአካል ጉዳት ለመቀነስ በተደረገ ጥረት በተገባደደው የ2013 በጀት ዓመት ከአምና ተመሳሳይ ወቅት ከነበረው በ13 በመቶ በመቀነስ የ59 ሰዎችን ህይወት ከሞት መታደግ መቻሉን ኤጀንሲው አስታውቋል።

በዘንድሮም በከተማዋ በትራፊክ ግጭት አደጋ የደረሰው ሞት 389 ሲሆን በ2012 በጀት ዓመት የተመዘገበው የሞት መጠን 448 እንደነበር ተገልጿል፡፡

በተመሳሳይ ሁኔታ በትራፊክ ግጭት ከባድ የአካል ጉዳት የደረሰባቸው ሰዎች ቁጥር ዘንድሮ 1ሺህ 824 ሲሆን አምና 1847 ሆኖ ተመዝግቧል፡፡ በዚህም 1.25 በመቶ ወይም 23 ሰዎችን ከከባድ የአካል ጉዳት መታደግ መቻሉም ተገልጿል፡፡

በአጠቃይ በበጀት ዓመቱ የደረሰው የትራፊክ ግጭት አደጋ ንብረት ላይ ጉዳት ማድረስ በቁጥር 27882 (89.6 %) ፣ ከባድ የአካል ጉዳት 1824 (6 %)፣ ቀላል የአካል ጉዳት 994 (3.19 %) እንዲሁም በሰው ላይ የደረሰ ሞት በቁጥር 389 (1.25 %) አደጋዎች በመሆን በቅደም ተከተል መመዝገባቸውን ኤጀንሲው አስታውቋል፡፡

ለነዚህ የትራፊክ ግጭት አደጋው እና ጉዳቶቹ እንዲቀንሱ በመንገድ ደህንነት ስትራቴጂ መሠረት የተቀመጡ ተግባራት በአግባቡ በመተግባራቸው መሆኑን ኤጀንሲው አመልክቷል፡፡

በተለይ በተደጋጋሚ የትራፊክ ግጭት አደጋ የሚደርስባቸው ቦታዎችን በጥናት እና ከትራፊክ ግጭት አደጋ ሪፖርት በመለየት በዘመናዊ ቴክኖሎጂ የታገዘ የምህንድስና ማሻሻያ ስራዎች ተግባራዊ በማድረግ፣ ለአሽከርካሪዎች እና ለህብረተሰቡ የግንዛቤ ስራዎች እንዲሁም በአሽከርካሪዎች ላይ ጥብቅ ቁጥጥር በመደረጉ መሆኑን ከኤጀንሲው ያገኘነው መረጃ ያስረዳል።

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

error: Content is protected !!