የእለት ዜና

በተሽከርካሪ አካል ውስጥ ተደብቆ ወደ አዲስ አበባ የገባ ጥይት በቁጥጥር ስር ዋለ

በተሽከርካሪ አካል ውስጥ ተደብቀው ወደ አዲስ አበባ የገቡ ከዘጠኝ ሺሕ በላይ ጥይቶች ከነተጠርጣሪ ግለሰቦቹ በቁጥጥር ስር ውሎ ምርመራ እየተካሄደ መሆኑን የአዲስ አበባ ፖሊስ ገለጸ።
የሰሌዳ ቁጥር ኮድ 3 B-13357 አ/አ የሆነ አይሱዙ ተሽከርካሪ ጥይቶችን ጭኖ በሕገ-ወጥ መንገድ ሲንቀሳቀስ ከሕብረተሰቡ በደረሰ ጥቆማ መሰረት የብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት እና የአ/አ ፖሊስ በጋራ ባደረጉት ክትትል በአዲስ ከተማ ክ/ከተማ ወረዳ 4 ልዩ ቦታው 18 ማዞሪያ መብራት ኃይል ቀለበት መንገድ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ በቁጥጥር ስር ውሏል።
በወቅቱ አራት ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር ውለው ምርመራ እየተጣራ መሆኑን የገለጸው የአዲስ አበባ ፖሊስ፣ በተሽከርካሪው ላይ በተደረገ ፍተሻ 8ሺሕ 400 የክላሽንኮቭ ጠብመንጃ እና 998 የኢኮልፒ ሽጉጥ፣ በአጠቃላይ 9ሺሕ 398 ጥይቶች በጥይት ማሸጊያ ሳጥን እና በጨርቅ ተጠቅልለው ቅያሪ (እስኮርት) ጎማ ውስጥ እንዲሁም በተሽከርካሪው የፊተኛው ክፍል ተደብቀው ተይዘዋል።
ሕገ-ወጥ የጦር መሳሪያ ዝውውር በአገር እና በሕዝብ ላይ ሊያስከትል የሚችለውን ኹለንተናዊ ጉዳት ከግምት ውስጥ በማስገባት፣ ሕብረተሰቡ በዚህ እና በሌሎች ከጸጥታ ጋር በተያያዙ ጉዳዮች ላይ የሚሰጠውን ጥቆማ አጠናክሮ እንዲቀጥል የአዲስ አበባ ፖሊስ ጥሪውን አቅርቧል።


ቅጽ 3 ቁጥር 142 ሐምሌ 17 2013

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

error: Content is protected !!