የእለት ዜና

ንቅሳትና ዘመናዊነት

Views: 233

ንቅሳት ለገጠሪቱ የአገራችን ክፍል ዛሬ የመጣ እንግዳ ነገር ባይሆንም አሁን ላይ ግን በንቅሳት እያጌጡ ያሉት በዋናነት ዘመነኛ የሚባሉት ከተሜዎች ናቸው። አሁን አሁን በከተማ የሚኖሩ ዕድሜያቸው በአስራዎቹ ከሚቆጠሩት አንስቶ ከፍ ያሉትን ጨምሮ ንቅሳት በእጃቸው፣ በደረታቸው እና በሌሎች የሰውነት ክፍሎቻቸው ላይ ማስተዋል የተለመደ ሆኗል።

ይህ የከተሜዎች በንቅሳት ማጌጥ አሁን ላይ ፍቃድና ዕውቅና ያለው ሥራ ይሁን እንጂ፣ ከዚህ በፊት በየመንደሩ በብዛት ይከወን እንደነበር አዲስ ማለዳ ያነጋገረቻቸው ዳንኤል አዲሴ የተባሉ ባለሙያ ይገልጻሉ። ንቅሳት አሁን የመጣ እንዳልሆነ የሚናገሩት ዳንኤል፣ አሁን የተለየው ነገር የምንጠቀማቸው መሳሪያዎች እና የተለያዩ ንድፎችን መሥራት መቻሉ ነው ይላሉ። “ጥበቡማ በፊትም የነበረ ነው” ሲሉ ያክላሉ።

በዚህ የሥራ ዘርፍ ላይ ከተሰማሩ ስድስት ዓመት እንዳሳለፉ የሚናገሩት ዳንኤል፣ የዚህ ሥራ ገበያ ከቀን ወደ ቀን እጅጉን እየጨመረ እንደመጣ ይገልጻሉ።
ሥራው በተለያየ የዕድሜ እርከን ላይ ያሉ ሰዎች ጋር እንደሚያገናኝ በመጥቀስ፣ ይበልጥ ግን ዕድሜያቸው በሃያዎቹ የሚገኙ ደንበኞች ቁጥራቸው ከፍ ያለ ነው። ሆኖም ቁጥራቸው የማይናቅ በዕድሜ ጠና ያሉ አዛውንቶችም ጭምር የሱቁን በር እንደሚረግጡ ይናገራሉ።
ከሚመጡት ደንበኞች አብዛኛዎቹ ኃይማኖታዊ ይዘቶችን እና የሚወዷቸውን ሰዎች ስም፣ የተወለዱበትን ቀን እና ምስላቸውን እንድሚነቀሱ ይገልጻሉ። ዕድሜያቸው ከፍ ያሉት ሴቶች ደግሞ በሰውነታቸው ላይ ንቅሳት ማሠራት ብዙም ባይሞክሩም ቅንድባቸውን ለማሠራት እንደሚመጡ ያክላሉ።

ከምንም በላይ ግን የሚያስገርመው ንቅሳትን ለማሠራት ከሚመጡት ጥቂት የማይባሉት ደግሞ ማሠራት የሚፈልጉትን እንኳ በአግባቡ የማያውቁ እና “አሁን ፋሽኑ ምንድነው?” ብለው እስከመጠየቅ የሚደርሱ እንዳሉ ይናገራሉ። ከዚህ በተቃራኒው ደግሞ ስለሚሠሩት ንቅሳት አውቀውና ተረድተው የሚመጡ ደንበኞችም እንዳሉ ባለሙያው ያስረዳሉ።

በአሁን ሰዓት ላይ ዕድሜያቸው ከአስራ ስምንት በታች የሆኑ ልጆችም ንቅሳት ለመሠራት እንደሚምጡ የሚናገሩት ዳንኤል፣ እነሱን ግን እንደማይስተናገዱ ይናገራሉ። አንዳንዶቹ ዕድሜያቸው የገፋ ቢሆንም ጥበቡን በደንብ የተረዱ እና መሠራት የሚፈልጉትንም በደንብ ጠንቅቀው የሚያውቁ መሆናቸውን አንስተዋል።

ከጾታ አኳያ ሲታይ ንቅሳት የሚሠሩ ወንዶች ቁጥራቸው ከሴቶቹ ላቅ ያለ እነደሆነ በሙያው ላይ የተሰማሩ ሌላኛው ባለሙያ የሺጥላ ይናገራሉ። የሺጥላ ብርሃኑ በዚህ ሙያ ላይ ከተሰማሩ አምስት ዓመት እንዳስቆጠሩ ይናገራሉ። በነዚህ ዓመታት ውስጥ የወንድ ደንበኞች ቁጥር ከፍ ያለ ቢሆንም፣ ከጊዜ ወደ ጊዜ ግን የሴቶቹ ቁጥርም እያደገ እንደመጣ ይገልጻሉ።

ዳንኤል ለአዲስ ማለዳ ሲናገሩ፣ ሥራ የጀመሩትም ሆነ ዕውቀታቸውን ያዳበሩት ስዕል በመሳል ከነበራቸው ችሎታ እንደሆነ ይገልጻሉ። ስዕል የመሳል ችሎታ እንዳላቸው የሚናገሩት ባለሙያው፣ ከሱ በመነሳት ብቻ ዛሬ የሙያው ባለቤት መሆን መቻላቸውን ያስረዳሉ።
“ሙያውን ለማዳበር ለሚፈልግ ሰው እኛ አገር ምንም አይነት ትምህርት ቤት የለም። ፍላጎት ካለ ግን በድረ-ገጽ የሚሰጡ ኮርሶች ስላሉ እነሱን መውሰድ ይቻላል” ይላሉ ባለሙያው። እነዚህንም ኮርሶች በመጠቀም ራሳቸውን ለማማሻሻል እንደሚጥሩም ይገልጻሉ። ትምህርት ቤቶች ቢኖሩ ኖሮ ከዚህም በላይ ሙያውን ማሳደግ ይቻል እንደነበርም ያነሳሉ።

ብዙዎቹ ደንበኞች የተለያየ ምርጫ እና ፍላጎት ይዘው እንደሚመጡ የሚገልጹት ዳንኤል፣ የሚመጡትን ይዘቶችና ፍላጎቶች በሙሉ ግን እንደማያስተናግዱ ይገልጻሉ። ይህንንም ሲያብራሩ አንዳንዶች የማይሆን ቦታ ላይ እና ከባህል ያፈነገጡ አይነት ንድፎችን የሚጠይቁ ይመጣሉ። ይህን ጊዜ መልሴ አይሆንም ነው ይላሉ ባለሙያው። “እኔ ራሴን የማየው እንደ አርቲስት ነው፤ ጥበብን ደግሞ ማክበር አለብኝ” ሲሉ ያክላሉ።

“አንዳንዶች እንደውም ከቀለሙ ጋር የሚቀላቀል ፓውደር ይዘው በመምጣት ሥራልን የሚሉ አሉ” ይላል ዳንኤል። ለእንደነዚህ አይነት ጥያቄዎች መልሱ አይሆንም እንደሆነ ይገልጻሉ። ምክንያቱንም ሲያብራሩ “ከባዕድ እምነት ጋር የተያያዘ ስለሚሆን እና የሙያውም ሥነ-ምግባር ስላልሆነ” ሲሉ ያስረዳሉ።

አልፎ አልፎም ቢሆን ፊታቸው፣ ዳሌያቸው እና መቀመጫቸው አካባቢ ንቅሳት ለማሠራት የሚመጡ እንዳሉ የሚያነሱት ባለሙያዎቹ፣ በብዛት የተለመደ ነገር ግን እንዳልሆነ ይገልጻሉ። አንዳንዶች ደግሞ በተለያየ አደጋ ምክንያት ያጋጠማቸውን ጠባሳ ለመሸፈንም ንቅሳትን እንደሚጠቀሙ ይናገራሉ።

በሥራ ወቅት ስህተት ሊያጋጥም እንደሚችል የሚገልጹት ዳንኤል፣ በአብዛኛው ግን በራሳቸው በተነቃሾቹ ምክንያት ስህተት እንደሚፍጠር ይናገራሉ ። ከገጠመኛቸውም መካከል “ የሠራነው የእናቱን ስም ነበር። ጽፎ የመጣውና ሊያሠራ የፈለገው ጽሑፉም በእንግሊዘኛ ነበር የተጻፈው። ላመጣው ጽሑፍ ንድፍ ወጥቶ ተሰርቶለት ተነቅሶ ከሄደ በኋላ የፊደል ስህተት አለው ብሎ ተመልሶ መጥቷል” ሲሉ ያስታውሳሉ። ማስተካከልም ስለሚቻል ችግሩን አስተካክለው እንደመለሱት ያስታውሳሉ።

ከጤና አኳያ ችግር ገጥሞ እንደማያውቅ የሚናገሩት የሺጥላ ብርሃኑ፣ ማንኛውም ደንበኛ ከመሠራቱ በፊት የመርፌ አለርጂክ ያለበት መሆን አለመሆኑን ቀድሞ እንደሚጠየቅ ይገልጻሉ። አለርጂክ ያለባችው ከሆነም ከመሠራት እንድሚቆጠቡ ይናገራሉ። የሚሠሩባቸውን መሳሪያዎችንም ሙሉ በሙሉ ስቴሪያላይዝ እንደሚያደርጉ የሚናገሩት ባለሙያው፣ “ይህ ለኔም ለደንበኞቸም ጤንነት በማሰብ ነው” ይላሉ።

የንቅሳት ሥራ በአሁን ጊዜ ለብዙዎች ሰዎች የሥራ ዕድል እየፈጠረ ይገኛል። በተጓዝንባቸው የከተማችን ክፍሎች ንቅሳት የሚሰጡ የንግድ ቤቶች በብዛት በራቸውን ከፍተው ደንበኞችን ሲያስተናግዱ ማስተዋል ከጀምርን ዋል አደር ብለናል።
ይህ የሥራ ዘርፍ በአደጉት የዓለማችን ክፍሎች እጅጉን ከመስፋፋቱ የተነሳ እንደ አንድ የውበት ኢንዱስትሪነት አንደሚታይ የአሜሪካ አካሄድን በአስረጂነት ማቅረብ በቂ ነው። IBIS world የተባለውና በንግዱ ዘርፍ ላይ ጥናት በማድረግ የሚታወቀው ተቋም በአሜሪካ የንቅሳት ዘርፉ በ2020 የ1.7 ቢሊዮን ዶላር ገቢ እንዳመነጨ ይገልጻል።

ይህ ተቋም የዚህ ኢንዱስትሪ ጉዞም በሚቀጥሉት አስር አመታት የስምንት በመቶ እድገት ሊያስመዘግብ እንደሚችል ይተነብያል።
ተቋሙ በሠራው ሌላ ጥናትም በአሜሪካ ውስጥ ከሚኖሩ ዕድሜያቸው ለንቅሳት ተገቢ ከሆኑት ውስጥ 46 በመቶ ያህሉ ቢያንስ አንድ ንቅሳት እንዳላቸው አሳይቷል። በአገራችን በዚህ ጉዳይ ላይ ጥናት የተደረገበት የምርምር ጽሑፍ ማግኘት ባይቻልም፣ አሁን ላይ ብዙዎች በንቅሳት ማጌጥ ላይ መሆናቸው የአደባባይ ምስጢር ነው።

በአገራችን በቁጥር የተደገፈ ጥናት ባናገኝም ባለሙያዎቹ እንደሚያስረዱት ግን የተነቃሾች ቁጥሩ እያደገ እንደሆነ ነው። የደንበኞች ቁጥር ከቀን ወደ ቀን እያደገ መምጣቱን የሚናገሩት ኹለቱ ባለሙያዎች፣ በሥራቸው ላይ የግብዓት ዕጥረት ማነቆ እንደሆነባቸው ያንሳሉ።
ለንቅሳት ሥራ የሚጠቀሟቸው ኹሉም ግብዓቶች ከውጭ የሚገቡ መሆናቸውን የሚገልጹት ባለሙያዎቹ፣ የሚጠቀሙባቸውን ግብዓቶች ለማግኘት ከፍተኛ ውጣ ውረዶች እንዳሉባቸው ያነሳሉ፡ ፡
“የተመዘገብን ግብር ከፋዮች ብንሆንም ግብዓቶችን ስናስገባ ብዙ ውጣ ውረዶች አሉብን” ይላሉ። ይሁን እንጅ ሥራው በእነዚህ ችግሮች የተተበተበ ቢሆንም ጥሩ ገቢ ያለው እንደሆነ ባለሙያዎቹ ይስማማሉ።
በነዚህም ችግሮች ውስጥ ሥራው በጣም ቆንጆ እንደሆነና ከቢዝነስ አንጻር የተሻለ ገቢም እንደሚገኝበት ይናገራሉ።

በ2012 ዓ.ም. ላይ በዓለም ዐቀፍ ደረጃ የተከሰተው እና ከፍተኛ ሰብዓዊና ኢኮኖሚያዊ ቀውስን የፈጠረው የኮሮና ቫይረስ ኢትዮጵያ ውስጥም ሰብዓዊና ኢኮኖሚያዊ ቀውስን ማስከተሉ ይታወቃል።
የኮቪድ 19 ወረርሽኝ በዓለም ዐቀፍ ደረጃ ከተከሰተ ወዲህ አንዳንድ አገራት የሙሉ በሙሉ ክርቸማ በማወጅ በሽታውን ለመቆጣጠር ጥረዋል። እነዚህ ክርቸማዎች የአገራቱን ኢኮኖሚ በከፍተኛ መጠን እንደጎዱ የተስተዋለ ሐቅ ነው። ምንም እንኳን በአገራችን ሙሉ የክርቸማ አዋጅ ባይታወጅም ሕዝቡ ሰው በብዛት ከሚሰበሰብበት አካባቢ እና ንክኪ ካላቸው ጉዳዮች ራሱን አቅቦ መቆየቱ ይታወሳል። በዚህም ገበያቸው እንደበፊቱ አልሆን ብሏቸው ወራትን ከዘለቁት የንግድ ተቋማት መካከል የንቅሳት ዘርፉ አንዱ ነው።
የኮሮና ቫይረስ የኢኮኖሚን መቀዛቀዝ በመላው ዓለም ያስከተለ ጉዳይ እንደመሆኑ መጠን በዚህም ምክንያት በሥራው ላይ ተጽዕኖ መፍጠሩ የማይካድ ሐቅ ነው።

ወረርሽኙ በተከሰተ የመጀመሪያዎቹ ሦስት ወራት ላይ የደንበኛ ቁጥር ቢቀንስም ሙሉ በሙሉ ሥራ አለማቆማቸውን ዳንኤል ያስረዳሉ። “ የኮሮና መከሰት በሥራው ላይ መቀዛቅዝን ያስከተለ ቢሆንም፣ እንደፈራነው ግን ችግር አላመጣብንም” ይላሉ ባለሙያው።
አሁን ባለበት የፍላጎት ፍጥነት መጓዙን ከቀጠለ፣ የንቅሳት ሥራ ወደፊት ከፍ ያለ የገቢ ምንጭ መሆኑ አያጠራጥርም። ይህ እንዲሆን ግን ባለሙያዎቹ ከኹሉም ባለድርሻ አካላት መሟላት አለበት የሚሉትን ያነሳሉ።

መንግሥት ለሙያውና ለባለሙያው ዕውቅና እንዲሰጥና ለሥራው ግብዓት የሚሆኑ ቁሶችን የማስገባት ሂደቱን ቀለል ቢያደርግ ሲሉ ሐሳባቸውን ያነሳሉ። ከዚህ በተጨማሪ ግን ሙያተኛው ተደራጅቶ ማኅበር በመመስረት መብቱን ማስከበርና ሙያውን ማሳደግ እንዳለበት ያክላሉ።
ይህንንም ለማድረግ ሙያው ላይ የተሰማሩ በሙሉ ተሰብስበው ማኅበር መመስረት እንዳለባቸው ያሳስባሉ። ይህ ካልሆነ ግን የሙያው እና የባለሙያው ማደግ ነገር አጠራጣሪ እንደሆነ ይናገራሉ።


ቅጽ 3 ቁጥር 142 ሐምሌ 17 2013

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com