የእለት ዜና

ቅጥ ያጡ የውጊያ ዘገባዎች

በኢትዮጵያ ሰሜናዊ ክፍል እየተካሄደ ካለው ውጊያ ጋር በተገናኘ የጦር ሜዳ ውሎዎችን የተመለከቱ ዘገባዎች ሰሞኑን መነጋገሪያ ሆነዋል። መከላከያ ከመቀሌ ወጣ መባሉን ተከተሎ እየተቀዛቀዘ የነበረው የሰሜኑ ወሬ እንዳዲስ አገርሽቶ ነበር። በተለይ በአሸባሪነት ተፈርጆ ተበትኗል ሲባል የነበረው ታጣቂ ቡድን ራያንና ከፊል ወልቃትን ተቆጣጠረ መባሉ ግራ አጋብቶ ነበር። ይህ ተወርቶ ሳያልቅ ባናት ባናቱ ሌላ ወሬ ተተክቶበት ነበር። የአማራ ክልል ታጣቂዎች መልሰው እንደተቆጣጠሩና መልሰው የተወሰኑትን እንደለቀቁም ይነገር ነበር።

የአማራ ክልል ፕሬዝዳንት ተናገሩ የተባለውም ጉዳይ ለ2 ቀን ያህል መነጋገሪያ ከሆነ በኋላ ምንም ሳይሉ መቅረታቸው ወሬውን አጋግሎት ነበር። ታጣቂዎቹ ድል ተደርገዋል ከተባለ በኋላ ከተለያዩ ክልሎች ልዩ ኃይሎች ጥሪ ተደርጎላቸው ወደ ሰሜን እያመሩ ነው መባሉም “ለምን?” እስከማስባል ደርሶ ነበር። ትግራይ ክልል ውስጥ ተመልሶ ላይገባ ማሰባሰቡ የት ለመዋጋት ነው? ቢያስብልም የደቡብ፣ የሲዳማና የጋምቤላ ልዩ ኃይሎች መተከል ተገኙ ተብሎ መነገሩ ግራ የገባውን ፌስቡከኛ የሚለው መላምት አሳጥቶታል።

የልዩ ኃይሎቹ አስፈላጊነት ላይ የነበረው የቃላት ምልልስ እንዳለ ሳይቋጭ፣ የትግራዩ ታጣቂ ቡድን ወሰን አልፎ የአፋርና የአማራ ክልል ቦታዎችን ያዘ፣ ወልዲያ ለመግባትም ትንሽ ቀረው የሚል ፕሮፓጋንዳ አይሉት ሀዘኔታ መናፈሱን ተከትሎ፣ በወልዲያ ሰዓት ዕላፊ ታወጀ መባሉ ለማረጋገጥ ነው እስከማስባል ደርሶ ነበር። ያም ተባለ ይህ፣ ይካሄድ የነበረው ውጊያ ብዙ ሰዎች እንዳለቁበት ሲነገር ነበር። አስከሬን በጭነት መኪናዎች ተሞልቶ እየተወሰደ ነው በሚል ቁጭት ይሁን ሀዘኔታ ለመፍጠር ባይታወቅም፣ በድል ዜና መልክ ብዙዎች ወሬውን ሲያናፍሱት ቆይተዋል።

አንዳንዶች በዚህ በዚህ ግንባር የመጣው ጦርን ይህ ብርጌድ እየጠበቀው ነው እያሉ ለጠላት ይሁን ለወዳጅ የሚጠቅም ዓላማው ያልታወቀ ዘገባን ሲያሰሙን ቆይተዋል። እንዲህ ቦታ ድል ተደረገ፤ እዚያ ቦታ ተሸነፈ እያሉ አጋዥ ለማስላክ በሚመስል መልኩም ለሕዝብ አስፈላጊ ያልሆኑ፣ ቅጥ አምባራቸው የጠፋ ዘገባዎች በማኅበራዊ ሚዲያ ሲያንሸራሸሩ ቆይተዋል። በጦር ያልተፈታውን በወሬ ለመፍታት እንደሚሞከር ግልጽ ቢሆንም፣ ወልዲያ ወሬ ሲያናፍሱ በጥቆማ 2 ወጣቶች ተያዙ ከሚል ውጭ በዚህ ረገድ የቃላት ፍልሚያው አሸናፊው አለየለትም።


ቅጽ 3 ቁጥር 142 ሐምሌ 17 2013

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

error: Content is protected !!