የእለት ዜና

ኮቪድ-19 እና የትምባሆ ጉዳት

በኢትዮጵያ የኮቪድ-19 ወረርስኝ ከተከሰተ ጊዜ ጀምሮ በሽታውን ያባብሳሉ የሚባሉ በርካታ ምክንያቶች አሉ። ከእነዚህ ምክንያቶች መካከል አንዱ የትምባሆ አጠቃቀም መሆኑ በርካታ ጥናቶች ያሳያሉ።
ትምባሆ የሚጠቀም ሰው እንኳን በኮቪድ-19 መያዝ ይቅርና ሌሎች የመተንፈሻ ችግሮች ሲፈጠሩ ለከፋ የጤና እክል ብሎም እስከ ሞት ለሚያደርስ ችግር ይጋለጣል።
ትምባሆ የሚጠቀሙ ግለሰቦች ደግሞ የኮቪድ-19 ወረርሽኝን እየተከላከሉ ያሉበት መንገድ እምብዛም የሚባል ስለመሆኑ ኹላችንም እየተመለከትነው ያለ ጉዳይ ነው።
ትምባሆ በባህሪው ሳምባን ጨምሮ አብዛኛው የመተንፈሻ አካላችንን የሚጎዳ ስለሆነ ኮቪድ-19 ሲጨመርበት ደግሞ የሚያደርሰው ጉዳት ተደራራቢ ነው።

የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ለአብዛኘው የዓለም ሕዝብ ፈተና ሲሆን የቆየ ተጽዕኖ ነው። ይህ ዐለምን ያስጨነቀ ተጽዕኖ አሁን እየተበራከተ ከመጣው የትምባሆ ተጠቃሚው ቁጥር ጋር እንዴት ማስማማት እንደሚገባ ዓለምን ግራ እያጋባ ያለ ጉዳይ ነው።
በኢትዮጵያ የመጀመሪያው የተረጋገጠ የኮቪድ-19 ታማሚ መጋቢት 4/ 2012 ሪፖርት የተደረገ ሲሆን፣ በአጠቃላይ በአሁኑ ሰዓት 2.9 ሚሊዮን የላብራቶሪ ምርምራ ተደርጎ፣ ቫይረሱ የሚገኝባቸው ሰዎች ቁጥር 10ሺሕ 964 መድረሱን የጤና ሚኒስትር መረጃ ያሳያል።
መጀመሪያ አካባቢ ከነበረው የኮቪድ -19 ወረርሽኝ በአሁኑ ሰዓት እየቀነሰ የመጣበት ሁኔታ ቢኖርም፣ ሕብረተሰቡ መዘናጋት የለበትም። በተለይም ደግሞ የትምባሆ ተጠቃሚዎች ወረርሽኙን ከማንኛውም ሰው በተለየ ሁኔታ መጠንቀቅ ይገባቸዋል።
በትምባሆ አጠቃቀም እና ከኮቪድ-19 መካከል ስላለው ግንኙነት የተሻለ ግንዛቤ መፍጠር የሚገባቸው ተቋማት እንዳሉ ይታወቃል።
ይህን ግንዛቤ በተቋም ብቻም የሚወሰን ሳይሆን የትምባሆ ተጠቃሚ ሆኖ በኮቪድ-19 ተይዞ የተጎዳ ሰው ምሳሌ ሊሆነን ይችላል።

ከዚህ በተጨማሪ ኮቪድ-19 ተይዞ የሚያጨስ ግለሰብ ከተገኘ ምን ያህል በሽታውን እንዳባባሰበት የሚገልጽ መረጃ ጤና ሚኒስትር መስራት ይጠበቅበታል።
በአጫሽ እና አጫሽ ባልሆኑ ሰዎች መካከል በበሽታ የመጠቃት እና በበሽታ የመያዝ ዕድላቸው ከፍ ያለ እንደሆነ የሚያነጻጽር ጥናት እንደሚያስፈልግም ምሁራን የሚያነሱት ጉዳይ ነው።
በኮቪድ-19 ከሚፈጠረው ሞት ይልቅ፣ በዓለም ላይ ያለጊዜው የሚከሰት ሞት አና በሽታ የሚያስከትለው ትምባሆ መጠቀም መሆኑን ጥናቶች ያሳያሉ። በዓለም ላይ በዓመት 7 ሚሊዮን ሰዎች በትምባሆ ምክንያት ለሞት ይዳረጋሉ። በዓለም ዙሪያ ወደ 1.3 ቢሊዮን የሚጠጉ የትምባሆ ተጠቃሚዎች ሲኖሩ፣ ከእነዚህ ውስጥ 80 በመቶዎቹ በዝቅተኛ እና መካከለኛ ገቢ ባላቸው አገሮች ውስጥ የሚገኙ መሆናቸው የዓለም ጤና ድርጅት መረጃ ያሳያል።

ኢትዮጵያ ውስጥ የትምባሆ አጠቃቀም ከሌሎች ዓለም አገራት ጋር ሲነጻጸር አነስተኛ ቢሆንም፣ በትምባሆ ምክንያት የሚሞተውን ሰው ቁጥር ለመቀነስ እና በሽታ የመከላከል አቅማቸውን ለማሳደግ ኹለም ኃላፊነት ይኖርበታል።
በተለይም ደግሞ እንደ አገር የኮቪድ-19 ከፍተኛ ጫና ማድረሱ ስለሚታወቅ፣ ወረርሽኙን የሚያባብሰውን አንዱ ምክንያት የሆነውን የትምባሆ ማጨስ ልማድ ችላ ማለት እንደሌለብን ልናውቅ ይገባል።
ትምባሆ ማጨስ ከኮቪድ-19 የሚያባብስ ብቻም ሳይሆን አንድ የጤና እክል የሚፈጥር ልማድ መሆኑ ይታወቃል። ኢትዮጵያ የኮቪድ-19 ወረርሽኝ መቆጣጠሪያ ዕርምጃዎችን እንደ አንድ ልዩ አጋጣሚ በመውሰድ የትምባሆ ቁጥጥር ሕጉን ሙሉ በሙሉ ማስፈጸም ይኖርባታል። ይህ በተሳካ ሁኔታ ከተተገበረ በወጣቶች የሚታየውን የትምባሆ ሱስ ለመቀነስና ለመከላከል ወሳኝ ሚና ይኖረዋል።

ሲጋራ እና አጠቃላይ የትምባሆ ምርቶች መጠቀም የሚያደርሰውን የጤና ጠንቅ ለመከላከልና ለመቆጣጠር የሕግ ግዴታዎችንና ክልከላዎች እንዲተገበሩ የሕዝብ ተወካዮች ምክርቤት 2011 ያጸደቀው አዋጅ ቁጥር 1112/2011 አለ።
የኢትዮጵያ የምግብ፣ የመድኃኒትና የጤና ክብካቤ አስተዳደርና ቁጥጥር ባለሥልጣን በትምባሆ ቁጥጥር የሚያወጣቸው መመሪያዎች ይበል የሚያሰኝ ነው። ትምባሆ ተጠቃሚውን ብቻ ሳይሆን በአቅራቢያው የሚገኙ ሰዎችም ላይ ችግር ይፈጥራል። ለዚሀም ማሳያ በተለያዩ መዝናኛ ተቋማት ላይ የሚታዩ ማጨስ አይፈቀድም የሚሉ መመሪያዎች መለጠፋቸው ከአጫሹም አልፎ አጠገቡ ያሉትን ሕብረተሰብ እንዳይጎዳ ሁነኛ መፍትሄ ነው።

አዲስ ማለዳ እንደታዘበችው የኮቪድ-19 ጥንቃቄ በሌለበት አካባቢ የትምባሆ አጠቃቀም ተበራክቷል። ትልቅ የሚባል መዝናኛ ቦታ ላይ መታዘብ የተቻለው ኹለት ወጣቶች አንድ ሲጋራ ለኹለት እየተቀባበሉ የሚያጨሱበትን ሁኔታ ነው።
እንደማንኛውም ሰው ይህንን ጉዳይ ብንመለከተው ራሱ ምን ያህል አግባብ ያልሆነ ድርጊት መሆኑን እንገነዘባለን። ኮቪድ-19 ወረርሽኝ ቀንሷል እንኳን ብለን ጉዳዩን ብናልፈው አንዱን ሲጋራ ለኹለት እየተቀባበሉ ያጨሱበት መንገድ አጸያፊ ድርጊት ብሎ የሚያስወግዝ ህሊና ሊፈጠርብን ያስፈልጋል።

የጤና ሚኒስቴር ከሚያስተላልፋቸው መልዕክቶች መካከል ስለ ሲጋራ አስከፊነት አንዱ ነው።
ሲጋራ ማጨስ የመተንፈሻ አካላት እንደሚጎዳ፣ የልብና ሳንባ ሕመምን እንደሚያባብስና ኮቪድ-19 የመያዝ እድልንም እንደሚጨምር ይነገራል።
ትምባሆ በሚጨስበት ወቅት የሰውነት መቆጣት እንዲሁም አጠቃላይ የሰውነት ሕዋስን በመጉዳት የበሽታ የመከላል አቅምን ያዳክማል።
ኮቪድ-19 ደግሞ በቅድሚያ የመተንፈሻ አካልንና ሳንባን የሚያጠቃ ቫይረስ በመሆኑ የሚያጨሱ ሰዎች ለወረርሽኙ ቅርብ ስለሚሆኑ ከፍተኛ የጤና እክል እንደሚገጥማቸው መረዳት ይቻላል።


ኢትዮጵያ 453 ሺሕ 600 ዶዝ የኮቪድ-19 ክትባት ከአሜሪካ ተረከበች
ኢትዮጵያ 453 ሺሕ 600 ዶዝ የመጀመርያ ዙር የጆንሰን ኤንድ ጆንሰን የኮቪድ-19 ክትባት ከአሜሪካ መንግሥት መረከቧ ተገለጸ፡፡
የኢትዮጵያ መንግሥት የኮቪድ-19 ወረርሽኝን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የሚያደርገውን ጥረት በመደገፍ የአሜሪካ መንግሥት ትልቅ አስተዋጽ ማበርከቱን የጤና ሚኒስትር ዶ/ር ሊያ ታደሰ ተናግረዋል፡፡
ሚኒስትሯ አሜሪካ ከመጀመሪያው ጀምሮ በአጋርነት ስትደግፍ መቀየቷን የገለጹ ሲሆን፣ አሁንም ወረርሽኙ እያደረሰ ያለውን ጫና ለመቋቋም ትብብሯን አጠናክራ በመቀጠል ይህን የክትባት ድጋፍ በማድረጓ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።
በኢትዮጵያ የአሜሪካ ኤምባሲ፣ የኮቫክስ ጥምረት፣ ዩኒሴፍ እንዲሁም ክትባቱን በማጓጓዝ ደግሞ የኢትዮጵያ አየር መንገድንና ሌሎች ባለድርሻ አካላትን ሚኒስትሯ አመስግነዋል፡፡
የአሜሪካ መንግሥት የኮቪድ-19 ወረርሽኝን ለመከላከልና ለመቆጣጠር እየተሸራ ያለውን ሥራና፣ በአጠቃላይ ለጤናው ሴክተር እያደረገ ያለውን ድጋፍ አጠናክሮ እንዲቀጥል ዶ/ር ሊያ ጠይቀዋል።
በኢትዮጵያ የአሜሪካ አምባሳደር ጊታ ፓሲ በበኩላቸው የአሜርካና የኢትዮጵያን የቆየ ወዳጅነትና የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነት አንስተው፣ መንግሥታቸው ኢትዮጵያ የኮቪድ-19 ወረርሽኝን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የምታደርገውን ጥረት ለማሳካት እስካሁን 182 ሚሊዮን ዶላር ኢንቨስት ማድረጉን አስታውቀዋል።
ከአሜሪካ መንግሥት በአጠቃላይ ከአምስት ሚሊዮን ዶላር በላይ ዋጋ ያለው 1.2 ሚሊዮን ዶዝ የጆንሰንና ጆንሰን ክትባት ለኢትዮጵያ ለመለገስ ቃል የተገባ ሲሆን፣ የቀረውን በቀጣይ ሳምንታት ውስጥ ርክክብ እንደሚደረግ ለማወቅ ተችሏል።


የኮሮናን ቫይረስ መነሻ ለማወቅ ለሚካሄደው ተጨማሪ ጥናት የዓለም ጤና ድርጅት ያቀረበውን ጥያቄ ቻይና ውድቅ አደረገች

የዓለም ጤና ድርጅት በኮቪድ 19 መነሻ ላይ በመጀመሪያ ጥናት ያላካተታቸውን ጉዳዮች አስመልክቶ ቻይና መረጃዎችን በመስጠት በኮሮና ቫይረስ ላይ ለሚያካሂደው ተጨማሪ ጥናት ትብብር እንድታደርግ ጠይቋል።
የዓለም ጤና ድርጅት ለሁለተኛ ጊዜ በቫይረሱ መነሻ ላይ ምርምርና በሳይንስ ተቋሞቻችን ላይ ፍተሻ ላድርግ ማለቱ እንዳስደነቃቸው የቻይና ባለስልጣናት ተናግረዋል።
ከዚህ በፊት አስፈላጊውን ትብብር ስናደርግ ብንቆይም ድርጅቱ ለሳይንስ ክብር የሚነፍግ፣ አቀራረቡም ፖለቲካዊ አዝማሚያ የተንፀባረቀበት በመሆኑ ቻይና ጥያቄውን እንደማትቀበለው ተገልጿል።
የቻይና ምክትል ጤና ሚኒስትር ዜንግ ቻይና ከዚህ ቀደም አገራቸው በቫይረሱ መነሻ ላይ ጥናት እንዳደረገችና ምክረ-ሃሳቧንም ለድርጅቱ እንዳቀረበች ጠቁመዋል።
የዓለም ጤና ድርጅት በዚህ ዓመት ጥር ወር ላይ የጥናት ቡድኑን ቫይረሱ ለመጀመሪያ ጊዜ ተከስቶበታል ወደ ተባለው ዉሃን ከተማ እንደላከና ቫይረሱ ከላቦራቶሪ እንዳፈተለከ የሚያመላክት መረጃ እንዳላገኘ በጥናት ግኝቱ ማመላከቱ ይታወሳል።

 

 

 


ቅጽ 3 ቁጥር 142 ሐምሌ 17 2013

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

error: Content is protected !!