የእለት ዜና

ኢዜማ በ28 ምርጫ ወረዳዎች ምርጫው እንዲደገም ለጠቅላይ ፍርድ ቤት አቤቱታ አቀረበ

የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) በ28 ምርጫ ወረዳዎች ሰኔ 14/2013 የተደረገው ምርጫ በድጋሚ እንዲደረግ ለጠቅላይ ፍርድ ቤት አቤቱታ አስገባ።
ኢዜማ ሰኔ 14/2013 ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እና ለክልል ምክር ቤቶች የተደረገው ምርጫ ላይ ከድምጽ አሰጣጥ ጋር ተያይዞ፣ ከቀበሌ እስከ ክልል ባሉ የገዢው ፓርቲ አመራሮች፣ ከቀበሌ ሚሊሻ እስከ ክልል ልዩ ኃይል ድረስ ባሉ የጸጥታ አስከባሪዎች፣ የምርጫ ጣቢያ የምርጫ አስፈጻሚዎች እና ለጊዜው ማንነታቸውና ሕጋዊ የሥራ ኃላፊነታቸው በግልጽ ያልታወቀ ግለሰቦች፣ በድምጽ አሰጣጥ ሂደት እና በምርጫው ውጤት ላይ እጅግ ከፍተኛ ተጽዕኖ ያሳደሩ እና የኢፌዲሪ ሕገ-መንግሥትን፣ የምርጫ አዋጅን እና ምርጫ ቦርድ ያወጣቸውን መመሪያዎች በቀጥታ የሚጻረሩ ተግባሮች መኖራቸውን ፓርቲው ገልጿል።
ፓርቲው በተፈጸሙት ስህተቶች የሰው፣ የሰነድ፣ የቪድዮ እና የምስል ማስረጃዎችን በማያያዝ ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሰኔ 18/2013 ቅሬታ ማስገባቱን ጠቁሟል። ፓርቲው ለኢፌዲሪ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ባስገባው አቤቱታ፣ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የቀረቡለትን ቅሬታዎች እና ማስረጃዎች በአግባቡ ሳይገመግም ውሳኔ ማስተላለፉን ጠቅሶ፣ ፍርድ ቤቱ ከበቂ በላይ ማስረጃ በቀረቡባቸው 28 ምርጫ ወረዳዎች ምርጫው በድጋሚ እንዲካሄድ ውሳኔ እንዲያስተላልፍ ጠይቋል።
ፓርቲው ምርጫው እንዲደገም አቤቱታ ያቀረበባቸው ኹሉም ምርጫ ክልሎች በደቡብ ክልል የሚገኙ ሲሆኑ፣ አቤቱታ ከቀረበባቸው የምርጫ ክልሎች ውስጥ 24ቱ ለፓርላማ እና ለደቡብ ክልል ምክር ቤት መቀመጫዎች ዕጩዎች ያቀረበባቸው አካባቢዎች እንደሆኑ ተገልጿል። በቀሪዎቹ አራት የምርጫ ክልሎች ደግሞ የክልል ምክር ቤት ምርጫ ብቻ የተካሄደባቸው እንደሆነ ተመላክቷል።


ቅጽ 3 ቁጥር 142 ሐምሌ 17 2013

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com