የእለት ዜና

የመጀመሪያው ዙር ምርጫ ያልተካሄደባቸው ክልሎች ዝግጅት

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ስድስተኛውን አገራዊ ምርጫ ለማካሄድ ሲያደርግ የነበረውን ዝግጀት አጠናቆ አገራዊ ምርጫው ሰኔ 14/2013 ማካሄዱ ይታወሳል።
ይሁን እንጅ ቦርዱ ስድስተኛውን አገራዊ ምርጫ ሙሉ በሙሉ ሰኔ 14 ማካሄድ አልቻለም። በዚህም ምርጫውን በኹለት ዙር ለማካሄድ ተገዷል። ቦርዱ ምርጫውን በኹለት ዙር ማድረጉ በአንዳንድ ፖለቲካ ፓርቲዎች በኩል ቅሬታ ያስነሳ ጉዳይ መሆኑ የሚታወስ ነው።
ምርጫውን በኹለት ዙር ለማካሄድ የተገደደው ምርጫ ቦርድ፣ የመጀመሪያውን ዙር ምርጫ ሰኔ 14 አካሂዶ አሸናፊውን ይፋ ማድረጉ የሚታወስ ነው። ቦርዱ ይፋ ባደረገው የመጀመሪያ ዙር ምርጫ ገዥው ፓርቲ ብልጽግና አብላጫውን ድምጽ ያገኘ ሲሆን፣ በምርጫው ከተሳተፉት ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች የተወሰኑት የሕዝብ ተወካዮችና የክልል ምክር ቤት መቀመጫዎችን ማግኘት ችለዋል።

ምርጫው በኹለት ዙር መካሄዱ በመራጩ ሕዝብ ዘንድ የሥነ-ልቦና ችግር ሊፈጥር ይችላል የሚል ሐሳብ ሲነሳ እንደነበርም የሚታወስ ነው። የመጀመሪያ ዙር ምርጫ ውጤት ከታወቀ በኋላ በተወሰኑ አካባቢዎች የሚካሄድ ምርጫ በአጠቃላይ ውጤቱ ላይ ለውጥ ሊያመጣ አይችልም የሚለው ሀሳብ እንደምክንያት ይነሳል። ይሁን እንጅ ምርጫው በኹለት ዙር መካሄዱ እርግጥ ሆኖና የመጀመሪያው ዙር ምርጫ ውጤት የታወቀ ቢሆንም፣ ፖለቲካ ፓርቲዎች የኹለተኛውን ዙር ምርጫ በመጠባበቅ ላይ ይገኛሉ።
ምርጫ ባልተካሄደባቸው ክልሎች የሚደረገው እና ለጳጉሜ 1/2013 ቀነ ቀጠሮ የተሰጠው ምርጫ በአንዳንድ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች በመጠኑም ቢሆን ለውጥ ሊያመጣ ይችላል የሚል ተስፋ ተጥሎበታል።

ምርጫ በሕዝብ እና የጋራ ጉዳዮቹን በተመለከተ እንዲያስተዳድር ሥልጣን በሰጠው መንግሥት የሚባል ተቋም መካከል ያለውን ግንኙነት ለማስተካከል፣ እንዲሁም የፖለቲካ ሥልጣን በሕዝብ ይሁንታ ብቻ የሚገኝ እንዲሆን መሠረት ለመጣል የሚያስችል እንዲሆን ይጠበቃል ይላሉ ፓርቲዎቹ።

የኢትዮጵያን መጻኢ ዕድል የሚወስነው ይህ አገራዊ ምርጫ እንደ አገርም ሆነ እንደ ክልል ጠንካራ እና ዘላቂ ዲሞክራሲያዊ ሥርዓትን ለመገንባት እና በአሁኑ ወቅት በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች የሚስተዋሉቱን አሳሳቢ የሰላም መደፍረስ ችግሮችን ከምንጮቻቸው ለማድረቅ በረጅም ጊዜ እይታ የተቃኙ እርምጃዎችን ለመውሰድ እንደሚረዳ እየተገለጸ ነው።

በአገር እና በሕዝብ ላይ ሲፈጸም የኖረውን ውስብስብ የአስተዳደር በደል፣ ስር የሰደደ ኢ-ፍትሐዊ አሠራር እና ኢ-ዲሞክራሲያዊ አካሄድ መሰረታዊ በሆነ መልኩ በመቀየር፣ እንደ አገር በፊታችን የተደቀነውን አስከፊ ሁኔታና የሕልውና አደጋን ለማስወገድ ብቸኛው አማራጭ ምርጫ መሆኑን ብዙዎች ይስማማሉ።

በመሆኑም ከነባራዊው የፖለቲካ፣ የምጣኔ ሐብት እና ማኅበራዊ ሁኔታዎች በመነሳት፣ እንዲሁም ለሕዝብ ፍላጎት በመገዛት ሰፊ የሪፎርም ሥራ ከግብ ለማድረስ በቅድሚያ ሠላም እና መረጋጋት እንዲሁም የሕግ የበላይነት መረጋገጥ እንዳለበትም ይታመናል።
ይህን ለማድረግም ኹሉም ዜጋ እና የማሕበረሰብ ክፍል በተረጋጋ ሁኔታ፣ በንቃት እና በስፋት በምርጫ መሳተፉ ፍጹም አስፈላጊ ከመሆኑ ባለፈ፣ ዘላቂ ዋስትና ያለው ሠላም እና ዲሞክራሲ እንዲሰፍን፣ ምጣኔ ሐብታዊ እና ማኅበራዊ ዕድገት እንዲፋጠን፣ በሕግ የበላይነት እና በሕዝቡ ፈቃድ ላይ የተመሠረተ አንድ የፖለቲካ ማሕበረሰብ በጋራ ለመገንባት መሥራት ያስፈልጋል የሚሉት የቦሮ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊው መብራቱ አለሙ(ዶ/ር) ናቸው።
በቤኒሻንጉል ምርጫ ባልተካሄደባቸው መተከል እና ካማሺ ዞኖች አሁንም ድረስ የጸጥታ ችግሮች በመስተዋላቸው ስጋት እንዳለባቸው መብራቱ ለአዲስ ማለዳ ጠቁመዋል።

በተለይም በኹለቱ ዞኖች የነበረው ሰላም እንዳልተመለሰ የገለጹት መብራቱ፣ ከሰሞኑ ደግሞ ችግሩ እየተባባሰ መምጣቱን አንስተዋል። በዚህም ረገድ እስካሁን የምርጫ ጊዜ ሰለዳ ማውጣት እና እንቅስቃሴ ማድረግ እንዳልተቻለ ጠቁመዋል።
በመተከል እና ካማሺ ዞኖች ላይ የዜጎች መፈናቀል እና ጥቃት መልኩን እየቀያየረ እንደመጣ የጠቆሙት መብራቱ፣ ዜጎች ተረጋግተው በማይኖሩበት አከባቢ ላይ ምርጫ ማካሄድ ትልቅ ተግዳሮት ይኖረዋል ብለዋል። አያይዘውም ምክንያቱ ባልታወቀ ሁኔታ የፓርቲያቸው ዕጩ ተወዳዳሪ ከሰሞኑ ተገድሎ እንደተገኘም አንስተዋል።

በሌላ በኩል ባለፈው ሰኔ 14/2013 ከተካሄደው ምርጫ የመገናኛ ብዙኃንን አስፈላጊነት እንደትምህርት ወስደናል ያሉት መብራቱ፣ የሲቪክ ማኅበራት እና ምርጫ ታዛቢዎች ወሳኝነትንም በሚገባ ተረድተናል ይላሉ።
በዚህም እነዚህ ተቋማት ምርጫው ነጻ፣ ፍትሐዊ እና ዲሞክራሲያዊ እንዲሆን የራሳቸው የሆነ ከፍተኛ ሚና ሊጫወቱ እንደሚችሉ አስረድተዋል።

እንደ ፓርቲ ምርጫው በሠላም እንዲጠናቀቅ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር እየተሰራ ስለመሆኑ አንስተው፣ ምርጫውን ለማካሄድ በቂ ዝግጅት እንደተደረገም ጠቅሰዋል።
ከዚህም ባሻገር በአገሪቱ እየተፈጠረ ያለውን የዲሞክራሲ መድረክ ለሕዝቦች አብሮነት፣ መቻቻል፣ መተሳሰብ እና ሕገ-መንግስታዊ መብቶች መከበር ምቹ ሁኔታ እንዲፈጠር ለማስቻል የሚደረገው አገራዊ ንቅናቄ፣ ሰኔ 14 ከተካሄደው ምርጫ ባልተናነሰ መልኩ ከፍተኛ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል ብለዋል።

እነዚህን ኹሉ ተስፋ የተጣለባቸውን መጻኢ ዕድሎች ለመወሰን እና ዕውን ለማድረግ ሰላማዊ፣ የተረጋጋ፣ ፍትሐዊ እና ዲሞክራሲያዊ የሆነ ምርጫ ማካሄድን ኹሉም የሚመለከተው አካል ትኩረት ሊሰጥበት እንደሚገባ አመልክተዋል።
የምዕራብ ሱማሊ ዴሞክራቲክ ፓርቲ ሊቀመንበር ሂርሲ ዶል ሂርሲ በበኩላቸው፣ ካለፈው ጠቅላላ አገር አቀፍ ምርጫ በርካታ ትምህርቶችን ወስደናል ብለዋል።
በዚህም ረገድ ምርጫው ነጻ፣ ፍትሐዊ እና ተዓማኒ እንዲሆን የፓርቲው ታዛቢዎች በንቃት እንዲከታተሉ የማድረግ ሥራ እየተሠራ ነው ሲሉ ገልጸዋል።

ችግሮች ቢኖሩ እንኳን ፓርቲዎች አንድ ላይ በመሆን ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ምርጫው በሠላም እንዲጠናቀቅ የበኩላችንን ለመወጣት እየሠራን ነው ሲሉ አመልክተዋል።
በክልሉ ምርጫ በሚካሄድባቸው አካባቢዎች ላይ ምንም አይነት የጸጥታ ስጋት እንደሌለ ያነሱት ሊቀመንበሩ፣ በዚህም ረገድ ከሌሎች ክልሎች የተሻለ የጸጥታ ሁኔታ እንዳለ ጠቁመዋል።
በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል እና ሌሎች አካባቢዎች ላይ የጸጥታ ችግር በሚስተዋልባቸው አካባቢ ለአስፈጻሚዎች ሥልጠና መስጠት አለመቻሉን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ማስታወቁ ይታወሳል።
የምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ብርቱካን ሚደቅሳ ለፖለቲካ ፓርቲዎች ተወካዮች እንዳሉት፣ የመራጮች ምዝገባ በኹሉም የአገሪቱ ክፍል መጀመር ቢኖርበትም በተወሰኑ አካባቢዎች ለምርጫ አስፈጻሚዎች የሚሰጠው ምዝገባ ላይ መጓተት ተከስቷል።
“ከጸጥታ እና ከእንደዚህ አይነት መሰል አሳሳቢ ሁኔታዎች ጋር በተያያዘ ሥልጠና ያላደረግንባቸው ቦታዎች አሉ” ያሉት ሰብሳቢዋ፣ በቦታዎቹ ላይ ለምን ሥልጠና ማካሄድ እንዳልተቻለ አስረድተዋል።

በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ሥልጠና ያልተደረገባቸው ቦታዎች የመተከል እና ካማሺ ዞኖች መሆናቸውን የጠቆሙት ብርቱካን፣ የክልሉ መንግሥት በሚያቀርበው መረጃ ላይ በመመስረት ለኹለቱ ቦታዎች “የተለየ የአመዘጋገብ ሂደት” እንደሚከተሉ ተናግረዋል። በመተከል ዞን ሥልጠናውን ማካሄድ ያልተቻለው “ምን ያህሉ የሕብረተሰብ ክፍል ተፈናቅሎ እንደሚገኝ እና ምን ያህሉ ደግሞ ወደ ቀዬው እንደተመለሰ” ከክልሉ መንግሥት የተጠየቀው መረጃ በቶሎ ባለመላኩ መሆኑን አብራርተዋል።
የክልሉ መንግሥት የትኞቹ ቦታዎች ለሥልጠና ሆነ ለመራጮች ምዝገባ አፈጻጸም ምቹ እንደሆኑ፣ የትኞቹ አሳሳቢ እንደሆኑ ለይቶ እንዲያቀርብ ተጠይቆ ምላሽ ስላልሰጠ ምላሹን እየጠበቅን ነው” ሲሉ ከምዝገባው መስተጓጉል ጀርባ ያለውን ምክንያት ገልጸዋል።
በሱማሌ እና ሐረሪ ክልሎችም እንደ ቤኒሻንጉል ኹሉ ከክልሎቹ መንግሥታት የሚጠበቅ መረጃ ተጠናቅቆ ስላልገባ ችግሮች እንደገጠሟቸው ጠቅሰዋል።

ከሦስቱ ክልሎች በተጨማሪ የጸጥታ መደፍረስ ችግር በተከሰተባቸው፣ የአማራ ክልል የሰሜን ሸዋ እና የኦሮሞ ብሔረሰብ ልዩ ዞን አራት ምርጫ ክልሎች ላይ፣ የምርጫ አስፈጻሚዎች ሥልጠናም ሆነ የመራጮች ምዝገባ ቁሳቁሶች ስርጭት ቦርዱ ማካሄድ አለመቻሉን ሰብሳቢዋ መግለጻቸው የሚታወስ ነው።

በጸጥታና በሌሎች ችግሮች ስድስተኛው አገራዊ ምርጫ በአንድ ዙር ማካሄድ ያልቻለው ኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ፣ ምርጫውን በኹለት ዙር ለማካሄድ መገደዱን ተከትሎ የመጀመሪያ ዙር ምርጫ ውጤት ይፋ አድርጎ ለኹለተኛው ዙር ምርጫ እየተዘጋጀ ይገኛል።
ቦርዱ የመጀሪያውን ዙር ምርጫ ሲያካሂድ ከገጠሙት ችግሮች በመነሳት፣ ሙሉ በሙሉ ምርጫ ባልተካሄደባቸውና የሰኔ 14 ምርጫ በተካሄደባቸው ክልሎች ውስጥ ተቆርጠው በቀሩ አከባቢዎች የተሻለ ምርጫ ያካሂዳል ተብሎ ይጠበቃል።

ምርጫ ባልተካሄደባቸው ክልሎችና ተቆርጠው በቀሩ አከባቢዎች፣ በተለይም በቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል መተከልና ካማሺ ዞን፣ ያለው የጸጥታ ሁኔታ ምርጫ ለማካሄድ አስቻይ ካልሆነ ቦርዱ ጳጉሜ 1/2013 ለማካሄድ እንደሚቸገር የቦርዱ ሰብሳቢ መግለጻቸው የሚታወስ ነው።
በአብዛኛው የአገሪቱ አካባቢዎች ሰኔ 14/2013 ስድስተኛው አገር አቀፍ ምርጫ ሲካሄድ፣ በሱማሌ፣ ሐረሪ እና ቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልሎች በጸጥታ ችግር፣ የድምጽ መስጫ ወረቀት ብልሽትና በክልሎቹ መንግሥታት በቀረቡ የፍርድ ቤት ክርክር ጉዳዮች ምርጫ አለመካሄዱ የሚታወስ ነው።

አዲስ ማለዳ ያነጋገረቻቸው በሱማሌ፣ ሐረሪ እና ቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል የሚገኙ ፓርቲዎች ሰኔ 14/2013 የተካሄደው የመጀመሪያ ዙር ምርጫ በክልላቸው አለመካሄዱ ቅሬታ እና ስጋት እንደፈጠረባቸው ገልጸዋል።
በእነዚህ ክልሎች በተለያዩ ምክንያቶች ምርጫ ማካሄድ አለመቻሉን የገለጸው ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ፣ በመጪው ጷግሜ 1/2013 በክልሎቹ ምርጫ እንደሚያካሂድ ማስታወቁ ይታወሳል።


ቅጽ 3 ቁጥር 142 ሐምሌ 17 2013

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

error: Content is protected !!