የእለት ዜና

በቤንች ሸኮ ዞን ሸኮ ወረዳ ሰዎች መገደላቸው ተገለጸ

በደቡብ ክልል ሸኮ ዞን ሸኮ ወራዳ ታጣቂ ኃይሎች በፈጸሙት ጥቃት የኹለት ሰዎች ሕይወት ማለፉን የአከባቢው ነዋሪዎች ለአዲስ ማለዳ ተናገሩ።
ይህ ችግር እየተስተዋለ ያለው በሸኮ ወረዳ ብቻ ሳይሆን በሸኮ ዞን ጉራ ፈርዳ እና ሌሎች አካባቢዎች ጭምር መሆኑን ነዋሪዎቹ አንስተዋል።

በዞኑ የተለያዩ ወረዳዎች ችግሩ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰ መሆኑን ያነሱት ነዋሪዎቹ፣ ነገር ግን የሸኮ ወረዳ ችግር አሁንም ድረስ መልኩን እየቀያየረ መቀጠሉን ጠቁመዋል።
በቅርቡ በሸኮ ዞን አንድ የልዩ ኃይል አባል መገደሉን ነዋሪዎቹ ጠቁመዋል። በአካባቢው አሁንም ድረስ ሕዝቡ ከስጋት እና መፈናቀል ያልወጣ መሆኑን ጠቅሰው፣ ችግሩ እየተባባሰ በመምጣት ለኹለት ንጹኃን ሰዎች ሕይወት ሕልፈትም ምክንያት ሆኗል ብለዋል።
ነዋሪዎቹ አክለውም ታጣቂዎች የተዘጋ በር እየሰበሩ እና ቤቶችን እያወደሙ የንብረት ዘረፋ እየፈጸሙ መሆኑንም ተናግረዋል።

አሁንም ድረስ ሥርአት አልበኝነቱ እና የሕገ-ወጥ ተግባሩ በስፋት እየተስተዋለ በመሆኑ፣ የአከባቢው ነዋሪዎች በከፍተኛ ስጋት እና ፍርሀት ውስጥ እንደሚገኙ አመልክተዋል።
በዚህም የሸኮ ወረዳ ነዋሪዎች ሕይዎታቸው አደጋ ላይ መውደቁን በስጋት ተናግረዋል።

በወረዳው ምንም አይነት የጸጥታ አስከባሪ ኃይል እንደሌለ ያነሱት ነዋሪዎቹ፣ ቀድሞ የነበሩትም ምክንያቱን ባላወቁት ሁኔታ እንዲወጡ መደረጉን ገልጸዋል።
ውድመት፣ ዘረፋ እና ግድያ እየተፈጸመ መሆኑን ለወረዳ እና ዞን አስተዳደር ያመለከትን ቢሆንም፣ ምንም አይነት ምላሽ ልናገኝ አልቻልንም ሲሉም ቅረታቸውን አሰምተዋል።
ስለ ጉዳዩ ወረዳ ሄደን ስናመለክት ወደ ዞን ሂዱ፣ ዞን ስንሄድ ደግሞ ወረዳ ሄዳችሁ ጠይቁ የሚል ምላሽ በመስጠት እንግልትም ደርሶብናል ብለዋል ነዋሪዎቹ።

አዲስ ማለዳ በ140ኛ ዕትሟ በወረዳው አርሶ አደሮች ላይ የተደራጁ ኃይሎች ዘረፋና ድብደባ እየፈጸሙባቸው መሆኑን መዘገቧ የሚታወስ ነው። የተደራጁ ሽፍቶች ናቸው የተባሉት አካላት ከሰኔ 23 እስከ ሰኔ 26/2013 ብቻ ከ10 በላይ መኪኖችን አስቁመው የጫኑትን ዕቃ መዝረፋቸውን የዘረፋው ሰለባዎች ተናግረው ነበር። ዘረፋ የተፈጸመባቸው መኪኖች የጫኑት ዕቃ ወደ ገበያ የሚጓጓዝ የአርሶ አድሮች ንብረት መሆኑ ተመላክቷል።

በሸኮ ዞን ከፍተኛ ዘረፋ የሚፈጸምበት ቦታ ሰንቃ ተብሎ በሚጠራ ቀበሌ መሆኑን የጠቆሙት የአከባቢው ኗሪዎች፣ የተደራጁ ሽፍቶች በአካባቢው እየተዘዋወሩ በአርሶ አደሩ ላይ በሚፈጽሙት ዘረፋና ድብደባ አርሶ አድሩ ተንቀሳቅሶ የእርሻ ሥራ ለመከወን እንዲቸገር አድርጎታል ብለዋል። የተደራጁ ሽፍቶች ናቸው የተባሉት አካላት በተለይ በሰንቃ ቀበሌ ያለ ማንም ከልካይ ቀን በቀን እየተንቀሳቀሱ በግልጽ ዘረፋ እየፈጸሙ መሆኑን መግለጻቸው ይታወሳል።

የነበረውን የጸጥታ ችግር መሰረት አድረጎ በአካባቢው ተሰማርቶ የነበረው ጸጥታ አስከባሪ ልዩ ኃይልና መከላከያ ከግንቦት 2013 አጋማሽ በኋላ አካባቢውን ለቆ መውጣቱን ተከትሎ ዘረፋዎችና ድብደባዎች እንደተባባሱ ተነግሯል። የአካባቢው አርሶ አደሮች ቆሞ የነበረው የጸጥታ ችግር፣የጸጥታ አስከባሪ ኃይሉ ከአከባቢው ከወጣ በኋላ ዘረፋዎችና ድብደባዎች ተባብሰው ወደ ግድያ እያመሩ መሆኑን ነው የገለጹት። ነዋሪዎቹ ጸጥታ አስከባሪ ወደ አከባቢው ተመልሶ እንዲገባ ቢጠይቁም ምላሽ ማግኘት እንዳልቻሉ ጠቁመዋል።
አዲስ ማለዳ በተደጋጋሚ ከኗሪዎች የሰማቸውን ቅሬታ ይዛ የቤንች ሸኮ ዞን ሰላምና ጸጥታ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ኮማንደር ዳዊት ጢሞቲዎስን በተደጋጋሚ ስልክ ደውላ ብታገኛቸውም፣ ስብሰባ ላይ ነኝ በማለት ምላሽ ሳይሰጡ ቀርተዋል።


ቅጽ 3 ቁጥር 142 ሐምሌ 17 2013

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

error: Content is protected !!