የእለት ዜና

ከአንድ ሺሕ በላይ መንጃ ፈቃድ ማገዱን የአዲስ አበባ ትራንስፖርት ቢሮ ገለጸ

የማሽከርከር ሕግን በመተላለፍ ከባድ ጥፋት አጥፍተዋል ያላቸውን 1ሺሕ 117 አሽከርካሪዎች መንጃ ፈቃድ ማገዱን የአዲስ አበባ ትራንስፖርት ቢሮ አስታወቀ።
የትራንስፖርት ቢሮ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አረጋዊ ማሩ ለአዲስ ማለዳ እንደተናገሩት፣ መንጃ ፍቃዳቸው የታገደባቸው አሽከርካሪዎች ለ290 ሰዎች ሞት እና ለ827 ሰዎች ከባድ የአካል ጉዳት መድረስ ምክንያት የሆኑ በመሆናቸው ነው።
የዕገዳው አጣጣልም እንዳደረሱት ጉዳት የሚወሰን ነው ያሉት ማሩ፣ ዕገዳው ከአንድ ዓመት ተኩል እስከ ስድስት ወር የሚቆይ መሆኑን አንስተዋል።

ከዚህ በተጨማሪም የደህንነት ቀበቶ እና የሕጻናት የደህንነት መደገፊያ በተሽከርካሪዎች ውስጥ መተግበሩን ለማጠናከር በተደረገው ቁጥጥር 4ሺሕ 447 አሽከርካሪዎች ላይ የገንዘብ ቅጣት እርምጃ መውሰዱን የቢሮው የሕዝብ ግኑኝነት ኃላፊ አረጋዊ ማሩ ተናግረዋል።
እንዲሁም በተንቀሳቃሽ ስልክ እየተነጋገሩ ሲያሽከረከሩ የነበሩ 10ሺሕ 330 አሽከርካሪዎችና ከፍጥነት በላይ ባሽከረከሩ 1ሺሕ 20 አሽከርካሪዎች ላይ ቢሮው ተመሳሳይ እርምጃ መወሰዱንም አስታውቀዋል።

በተጨማሪም ለሕዝብ ትራንስፖርት አገልግሎት ተብሎ ለብቻ በቀለም በተለዩት፣ ከሜክሲኮ-ጀርመን፣ ከሜክሲኮ-ስታዲየም፣ ከለገሀር-ፒያሳ፣ ከአንበሳ ጋራዥ ጎሮ እና ከላምበረት-ወሰን-ካራ ያሉ፣ መስመሮች ደንብ በማስከበር ተግባር ሕጉን ተላልፈው በተገኙ 9 ሺሕ አሽከርካሪዎች ላይ ተመሳሳይ የገንዘብ ቅጣት ተጥሏል።

መቆምና ተራን የሚከለክሉ አስገዳጅ ምልክት ለማስከበር በተደረገው ጥረት ሕግ ተላልፈው በተገኙ 30 ሺሕ 011 አሽከርካሪዎች ላይ የገንዘብ ቅጣት መጣሉንም አመልክተዋል።
እንዲሁም 758 አሽከርካሪዎች የተሃድሶ ሥልጠና እንዲወስዱ ወደ ተቋም የተላኩ ሲሆን፣ ከዚህ ውስጥ እግዳቸውን ያጠናቀቁና ሥልጠና ወስደው የተመለሱ 470 አሽከርካሪዎች መንጃ ፈቃዳቸው ተመላሽ እንደተደረገላቸውም አብራርተዋል።
ከጊዜ ወደ ጊዜ በመዲናይቱ እየተባባሰ የመጣው የትራፊክ አደጋ የበርካቶችን ሕይወት እየቀጠፈ እና በብዙ ሚሊዮን ገንዘብ የሚቆጠር ንብረት እያወደመ መሆኑ ታውቋል።

ከዚህ ጋር ተያይዞ የአዲስ አበባ ቀላል የባቡር መንገድ አጥርን ሰብረው በመግባት ተሽከርካሪዎች ተደጋጋሚ ጉዳት በማድረሳቸው ትራንስፖርት ቢሮው ቅሬታ ማሰማቱ አይዘነጋም። ይህን ተከትሎም ቢሮው በብዙ ሺሕ የሚገመት ገንዘብ ወጪ በማድረግ መልሶ ጥገና አካሂዷል።
የአዲስ አበባ ትራንስፖርት ቢሮም በተደጋጋሚ በሰው እና በንብረት ላይ ከፍተኛ ጉዳት እያደረሰ ያለውን የትራፊክ አደጋ ለመቀነስ እና ከምንጩ ለማድረቅ አስተማሪ ያላቸውን እርምጃዎች እየወሰደና በርካታ ሥራዎችን እየሠራ መሆኑን የቢሮው የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አረጋዊ ማሩ ጠቁመዋል።

ይሁን እንጅ አደጋውን ለመቅረፍ የሚቻለው በትራንስፖርት ቢሮው ጥረት ብቻ ሊሆን የሚችል እንዳልሆነ የገለጹት ኃላፊው፣ አሽከርካሪዎችም ኃላፊነት በተሞላ መልኩ ማሽከርከር እንዳለባቸው አሳስበዋል።


ቅጽ 3 ቁጥር 142 ሐምሌ 17 2013

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

error: Content is protected !!