የእለት ዜና

የዓባይ ግድብ ኹለተኛ ዙር የውኃ ሙሌት እና አንድምታዎቹ

ኢትዮጵያ የታላቁ ሕዳሴ ግድብን መገንባት ከጀመረችበት 2003 ጀምሮ ግብጽ በተለያዩ መንገዶች ተቃውሞዋን ስትገልጽ ቆይታለች። ኢትዮጵያ፣ ግብጽና ሱዳን ላለፉት አስርት ዓመታት በዓባይ ወንዝ ጉዳይ ሲደራደሩ የቆዩ ቢሆንም ተስማሙ በማይባልበት ሁኔታ ኢትዮጵያ የግድቡን ኹለተኛ ዙር የውኃ ሙሌት አከናውናለች። ግድቡ ተገንብቶ ሲጠናቀቅ 6ሺሕ ሜጋዋት የኤሌክትሪክ ኃይል ያመነጫል ተብሎ እንደሚጠበቅ መረጃዎች ያሳያሉ።

የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ሲጠናቀቅ ለአገሪቱ በርካታ ጥቅሞች እንደሚሰጥ ኹሉም የሚስማማበት ጉዳይ ነው። ከነዚህ ጥቅሞች አንዱ ኢትዮጵያ በሚቀጥለው ዓመት መስከረም ሲገባ የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጨት እንደምትጀምር መገለጹ ነው።
ይህ ደግሞ የግድቡ የውኃ ሙሌት መጠናቀቁን ተከትሎ የመጣ አንዱ ማሳያ ነው የሚሉት በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የአረብኛ ቋንቋ መምህር፣ የአባይ ጉዳይ ትንታኝ እና የአባይ ጓዳ የተሰኘ የሬዲዮ ፕሮግራም አዘጋጅና አቅራቢ የሆኑት ዑመር መኮንን ናቸው።
ዓለም ዐቀፍ ተቀባይነታችንን የሚያሳድግ ትልቅ ድል ኢትዮጵያ አስመዝግባለች የሚሉት ዑመር፣ ባለፈው ዓመት 4.9 ቢሊዮን ሜትሪክ ኪዩብ፣ እንዲሁም ዘንድሮ 13 ቢሊዮን ሜትሪክ ኪዩብ የያዘ የውኃ ሙሌት ማከናዋኗ ኤሌክትሪክ ማምረት የሚቻልበት አቅም ላይ መድረሳችንን ያሳያል ብለዋል።

ከዚህ በተጨማሪ ይላሉ ዑመር፣ የአገሪቱ የኢኮኖሚ ዕድገት በሚፈለገው ደረጃ ማደግ ይችላል። ኢኮኖሚያችን ማደጉ ዓለም ዐቀፍ ውድድር ውስጥ እንድንገባ ያስችለናል።
ግብጾች የአፍሪካ ቀንድ አካባቢዎችን ወይንም ምስራቅ አፍሪካን በተለያዩ ጉዳዮች እያሰሩ የበላይነትን ማሳየት የሚፈልጉ መሆናቸው እስከዛሬ እየታየ ያለ ነው።
በቀደመው ጊዜም ቢሆን ኢትዮጵያን ከጎረቤት አገራት ጋር በጦርነትና በመሳሰሉ ጉዳዮች የመለየት ሥራ ሲሠሩ ቆይተዋል።
እንደ ጅቡቲ እና ሱማሊያ ያሉ የኢትዮጵያ አጎራባች አገራት ግብጾች እንደፈለጉ ሲያሽከረክሯቸው ይስተዋል ነበር።
ከአሁኑ የሕዳሴ ግድብ ሙሌት በኋላ የግብጽ ጫና ይቀጥላል ወይ የሚለው አንዱ አከራካሪ ነው ይላሉ ዑመር።

አንደኛ ከዲፕሎማሲ አንጻር የነበረውን ጫና እና ኹለተኛ ደግሞ ዛቻና ማስፈራሪያውን መመልከት ይቻላል። ‹‹ከዲፕሎማሲ አንጻር ጫናው ይቀጥላል። ምክንያቱም የጸጥታው ምክር ቤት ለስብሰባ ከመቀመጡ ከሶስት ቀን በፊት ኢትዮጵያ ሙሌቱን መተግበር መጀመሯን ይፋ አድርጋ ነበር›› ብለዋል ዑመር።

በስብሰባውም ኢትዮጵያ ይዛ የመጣችው አቋም ጠንካራ አቋም ነበር። የአፍሪካ ሕብረት ነው የአፍሪካን ችግር የሚፈታው በማለት ጥንካሬዋን አሳይታለችም ሲሉ ተደምጠዋል።
ኢትዮጵያ የዓለም ዐቀፍ ማሕበረሰብን ንቃለችና የኢኮኖሚ ጫና ይደረግባታል፣ኹለተኛው ዙር ሙሌት ይወገዛል እንዲሁም በዚህ አያያዟ እንዳትቀጥል ይደረጋል የሚል የግብጾች እና ዐረቦች ፍላጎት ነበር።
ከድርድሩ ጋር በተያያዘ የአፍሪካ ሕብረት ሳይሆን የአውሮፓ ሕብረት፣ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እና አሜሪካ በአደራዳሪነት ተጨምረው ድርድሩ ይካሄዳል ተብሎ ነበር፤ ግን አልተሳካም። ስለዚህ የውጭ ኃይሎች ካሰቡት ነገር በሙሉ የተሳካላቸው ነገር የለም። የዲፕሎማሲ ጫናው ይቀጥላል የተባለበት ሌላኛው ምክንያት ይላሉ ዑመር፣ የግብጽ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሳሚ ሽኩሪ ከጸጥታው ምክር ቤት ስብሰባ በኋላ ወደ ግብጽ አልተመለሱም ነበር። ቀጥታ ከአውሮፓ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ጋር ሲመክሩ ነበር። በዚህ ሳምንት ከቻይና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጋር ያደረጉትም ምክክር አንዱ ነበር። እንደሚታወቀው ኢትዮጵያና ሩሲያ የወታደራዊ ስምምነት ፈጽመዋል። ይህ ስምምነት ስህተት ነው።

ይህ ስህተታችን ስትራቴጂካሊም አያስኬደንም ሲሉ ዑመር አንስተዋል። የዲፕሎማሲ ጫናም እያሳደረብን መሆኑ እየታየ ነው። ግብጾች ሳይተኙ የማያድሩበት ጉዳይ ቢኖር ኢትዮጵያ አሳሪ ሕግ እንድትፈርም የማድረጉን ሥራ ነው።
የግብጾች ሌላኛው ሴራ ተብሎ ተፈርቶ የነበረው ኢትዮጵያ ኹለተኛውን ዙር ሙሌት የምትፈጽም ከሆነ ውኃውን በመልቀቅ ጉዳይ የምንችለውን ኹሉ በማድረግ እናስተጓጉላለን እንዲሁም ኢትዮጵያ ቀይ መስመር አልፋለች የሚሉት ይገኙበታል።
እንደነዚህ አይነት ዛቻዎች ግን የተሳኩላቸው አይመስልም፤ ይቀጥሉበታል ብዬም አላስብም። ምክንያቱም ኢትዮጵያ ኹለተኛውን ሙሌት ያደረገችው ከፍ ባለ የዉኃ መጠን ነው። ማለትም የሱዳን ሪሶርስ ግድብ ከኢትዮጵያ በ100ኪ.ሜ ርቀት ላይ የሚገኝ ሲሆን፣ የኢትዮጵያ የሕዳሴ ግድበ ሙሌት የሱዳኖቹ ከያዘው ውኃ ኹለት እጥፍ መሆኑ ነው።

የሱዳን ምክር ቤት ጄኔራል አብዱልፈታህ አል ቡርሃን ከዚህ በኋላ ከኢትዮጵያ ጋር ያለንን አለመግባባት መፍታት ያለብን በንግግርና በውይይት ብቻ ነው ሲሉ ተደምጠዋል። ይህ ደግሞ ግብጾችን አስቆጥቷል። በተለይ ደግሞ ከአል ቡርሃን እንደዚህ አይነት የተለሳለሰ ምላሽ መምጣቱ ግብጽና ሱዳን እንዳይስማሙ አድርጎ ነበር። በየሚዲያዎቻቸውም አል ቡርሃንን ሲተቹ ነበር። ነገር ግን የሱዳኖች አቋም ምን አገባችሁ የሚል ይመስላል።
ይህን ተከትሎ ግብጽና ሱዳን እየተለያዩ ነው የሚል ነገር ሲመጣ፣ ሱዳኖች ደግሞ ኢትዮጵያ ስለምታደርገው የግድቡ ሙሌት ጠቅላላ መረጃ እንዲደርሳቸው ይፈልጋሉ።
ይህንን የሱዳንን ፍላጎት ለማሟላት የሚመስል ኢትዮጵያና ሱዳን ብቻቸውን የተነጋገሩበት ወቅት ነበር። ይህ ደግሞ በግብጽና በሱዳን ላይ በድጋሜ ቁርሾ የፈጠረ ነው።

ሰሞኑን ደግሞ የግብጽ ሚዲያዎች እያነሱት ያለው ማስተባበያ ግብጽና ሱዳን ተቃቅረዋል የሚባለው ጉዳይ ውሸት መሆኑን ነው ሲሉ ዑመር ለአዲስ ማለዳ ያስረዳሉ። ሱዳኖች በበኩላቸው ከኢትዮጵያ ጋር ብቻቸውን መምከራቸውን እየካዱ ይገኛሉ።
ግብጾች የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብን ኹለተኛ ዙር ሙሌት ተቀብለውታል ወይ ካልን አማራጭ የላቸውም ነው መልሱ። ምክንያቱም የ2015 የካርቱም ላይ የሶስትዮሽ ስምምነት ትልቅ ድል ነው። የአውሮፓ አገራት ይህንን ስምምነት እያስታወሱ በዛ ተስማሙ የሚል ሐሳብ ሲያነሱ ነበር። አገራቱ ይሕ ስምምነት ሦስቱን አገራት እንደሚያስማማቸው ሲያነሱም ተደምጠዋል።

ስምምነቱ እንደሚለው ከሆነ አንደኛውን ዙር ሙሌት 4.9 ቢሊዮን ሜትሪክ ኪዩብ፣ ኹለተኛውን ዙር 13.5 ቢሊዮን እና ሦስተኛውን ደግሞ 10 ቢሊዮን ሜትሪክ ኪዩብ ውኃ ኢትዮጵያ እንድትሞላ የሚገልጽ ነው።
ትልቁ እና የሚያኮራ የተባለው የኢትዮጵያ ስትራቴጂ ግብጾችም ሆኑ ሱዳኖችም አስተያየት ሲሰጡበት የነበረው ጉዳይ አለ። ይህም ደግሞ ኢትዮጵያ ሥራዋን እየሠራች ያለቸው እየተደራደረች መሆኑ ነው።
ስትራቴጂ ደግሞ ትክክለኛውን መንገድ የሚይዘው ሥራዋን እየሠራች ከኹለቱ ጋር መደራደሯ ነው። ኢትዮጵያ ስትራቴጂ ብላ እየሠራች ያለችው ‹ግድቡን እሞላለሁ፣ በተጨማሪም እደራደራለሁ› ስለሆነ በጣም የሚያኮራ ነው ይላሉ ዑመር።
ይህን ማድረጓ ደግሞ ግብጾችን በጣም አስደንግጧቸዋል። ከዛ ምን ብለው መግለጽ ጀመሩ ኢትዮጵያ እየሞላች ያለቸው 4.9 እና 13.5 ሜትሪክ ኪዩብ ውኃ ስለሆነ ግብጽ ላይ ምንም የምታመጣው ተጽዕኖ የለም በማለት ሕዝቦቻቸውን ሲያረጋጉ ተሰምተዋል። ከዚህ በተጨማሪ አሁን ባለው ውኃ መሰረት ግማሹን የሚያህል እንኳን ስላልወሰደች አትቸገሩ እያሉ ነው።

አሁን የሚታየው ነገር ደግሞ በግብጹ ፕሬዝዳንት አብዱልፈታህ አልሲሲ ላይ ሕዝቡ እንደተነሳበት እንደሆነ ነው። የግብጽ ሕዝብ እያለ ያለው እና መሪዎቹን እየተቃወመ የሚገኘው የጸጥታው ምክርቤት ስትገቡ ሐሳባችሁ ያሸንፋል ብለን ጠብቀን ነበር። ነገር ግን ለግብጽና ለሱዳን ሽንፈት ለኢትዮጵያ ደግሞ ትልቅ ድልና አሸናፊነትን አረጋግጣችሁ ነው የመጣችሁት በማለት ቅሬታውን እያሰማ ይገኛል።

ይህንን ሽንፈት ተመርኩዘው አሁን በሕይወት የሌለው የቀድሞው የግብጽ ፕሬዘዳንት የመሐመድ ሙርሲ ተከታዮች ደግሞ የውስጥ ጫና እያደረጉባቸው ይገኛሉ። ይህንን የውስጥ ችግር ለመፍታት ደግሞ የዐረብ ሊግ ጣልቃ እየገባ ይገኛል።
እንደ ዑመር ገለጻ ከሆነ፣ ሱዳን ከዚህ በኋላ የግድቡ ችግር ትሆናለች ተብሎ አይታሰብም። ምክንያቱም አሁን ባለው ሁኔታ ቀድሞ ችግር ውስጥ የሚወድቁት እነሱ ስለሆኑ ማለት ነው። ሰሞኑን ግን እየታየ ያለው ምንድነው ከተባለ፣ ሱዳን እና ኢትዮጵያ ድንበር በሚዋሰኑበት አካባቢ ወታደሮችን የመጨመርና ጦራቸውን በአካባቢው ላይ የማቆየት ሁኔታ አለ።

ሱዳኖች ኢትዮጵያውያን የኖሩበት ቦታ ላይ ወረራ አድርገዋል። አገሪቷ ሰላሟን ለማስጠበቅ በተንቀሳቀሰችበት ወቅት ነው ሱዳኖች ያንን ቦታ የተቆጣጠሩት። ይህን ቦታ በቁጥጥራቸው ስር መሆኑን ለማጠናከር ሥራ እየሠሩ ነው። የኢትዮጵያ አብዛኛው የጦር ሠራዊት ድንበር አካባቢ ያለ እና ግድቡን በመጠበቅ ላይ የሚገኝ ነው።

ኢትዮጵያ ከድንበሩ ጋር በተያያዘ ያስቀመጠችው መስፈርት አለ። ይህም ሱዳን ቀድማ ወደነበረችበት ቦታ ትመለስና እንደራደራለን የሚል ነው። ይህንን ወረራ ደግሞ ሱዳኖች እያጠናከሩት ይገኛሉ። ይህን የማጠናከር ሥራ ላይ ደግሞ የግብጽ ሴራ ይኖርበታል ብዬ አስባለው የሚሉት ዑመር፣ ምክንያቱም ግድቡ ላይ ጫና ማሳደር ስላቃታቸው ኢትዮጵያን በጦርነት ወከባ ውስጥ ለመክተት የተያያዙት ይመስላል ይላሉ።

ኢትዮጵያ 100 ትናንሽና መካከለኛ ግድቦች እንገነባለን ስትል፣ በተቃራኒው ግብጾች ደግሞ ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ ችግሮችን እየቀሰቀስን ግንባታውን እናደናቅፋለን ሲሉ ተደምጠዋል።
ይህ አሁን አገሪቱ የገባችበት ጦርነት እንዲባባስ ያደረገበት ሁኔታ ይኖራል ተብሎ ቢታሰብም፣ ኢትዮጵያ ፈተናዎችን በሚገባ እያለፈች ትገኛለች። ሕዝቡም ከመንግሥት ጎን እንደሆነ ባካሄደው ሰልፍ ድጋፉን የገለጸበትን ሁኔታ ማውሳት ይቻላል ብለዋል ዑመር።
የኢትዮጵያ ሕዝብ በሚካሄዱት የድል ጉዞዎች ሁሌም ከመንግሥት ጎን እንደሚቆም ይናገራሉ። አዲስ ማለዳ ተዘዋውራ ያነጋገረቻቸው አንዳንድ የአዲስ አበባ ነዋሪዎችም ቢሆኑ ይህንን አረጋግጠዋል።

የቀድሞው የመከላከያ ሠራዊት አባል እና በአሁኑ ሰዓት የታክሲ ሹፌር የሆኑት ሻለቃ ጌትነት ገ/እግዚአበሄር በአሁኑ ሰዓት ያለው የግድቡ ሁኔታ በጣም የሚያስደስት እና የሚያኮራ ነው ይላሉ። ‹‹የአብዛኛው ኢትዮጵያዊ ህልውና በመሆኑ በጣም ደስተኛ ነኝ›› ብለዋል።
ዓባይ ለኛም ለአገራችንም ዕድገት መሰረታዊ ጉዳይ ሲሆን፣ የአገሪቱ ገበሬ ወደ ልማት መሰመራት የሚችለውና ከኩራዝ መብራት ተላቆ ወደ ዘመናዊ ሕይዎት የሚሻገረው በዚህ የሕዳሴ ግድብ ልማት እንደሆነ አምናለሁ ሲሉ ተደምጠዋል።
‹‹የግብጽ እና ሱዳን ጉዳይ በሚመለከት እኔ ረጅም ጊዜ በጦርነት ስላሳለፍኩ የውጭ ወራሪ ኃይልን ለመመከት ዝግጁ ነበርኩኝ። ጦርነትም ተፈጥሮ ቢሆን ኖሮ ምንም ፍራቻ የለኝም፤ እንደምናሸንፍም እርግጠኛ ነበርኩኝ። በዚያድባሬ እና በሌሎች ከባባድ ጦርነቶች ላይ ተሳትፌ ነበር። ስለዚህ ቆራጥነት ውስጤ ነበር። ቢሆንም ግን በሰላም በመጠናቀቁ ደስተኛ ነኝ›› ይላሉ ሻለቃ ጌትነት።
በአጠቃላይ ረጅም ጊዜ ቢወስድም የግድቡ መሞላት እጅግ ትልቅ ደስታን ፈጥሯል።

ኢትዮጵያ ደግሞ ይህንን ሁሉ ችግሮችና ፈተና አልፋ፣ ለኹለተኛ ጊዜ ግድቧን መሙላት መቻሏ ትልቅ ስኬት ሲሆን፣ እንደ አንድ ኢትዮጵያዊ ደግሞ ያለኝን አቅም በሙሉ ተጠቅሜ እስከመጨረሻው ግድቡን ለማሳካት ዝግጁ ነኝ ብለዋል።
ይህ ግድብ እንዳይሳካ የሚያደርግ ማንኛውም የውስጥም ይሁን የውጭ ኃይል አቅም ማዳከም ይገባናል።

ግብጾች ኢትዮጵያውያን እንዲጠቀሙ አይፈልጉም የሚሉት ደግሞ የበደብረብርሀን ሰሜን ሸዋ ፖሊስ መምሪያ አባል የሆኑት ኮማንደር እሸቱ ጌታቸው ናቸው።
ግድቡ ተጠናቆ ማየት የኹሉም ኢትዮጵያዊ ፍላጎት ነው። ዋና ነዳጃችን የሆነው የዓባይ ግድብ የኃይል ማመንጫ ከተጠናቀቀ የአገሪቱን ከፍተኛ የሥራ አጥነት ቁጥር ይቀንሳል፣ የተለያዩ ኢንዱስትሪዎችና ፋብሪካዎች እንዲስፋፉ ያደርጋል ሲሉ እሸቱ ገልጸዋል።
እኛ መኖር ነው የምንፈልገው። ልጆቻችን በተመቻቸ የኑሮ ሁኔታ እንዲያድጉ ነው የምንሻው የሚሉት ደግሞ ኮንትራክተር ፍቃዱ ጀማል ናቸው። ‹‹እነሱ እኮ ጠግበው ቲማቲም፣ እንቁላል እና ኬክ በመወራወር እየተጫወቱበት ነው። እኛ በወንዛችን ባለመጠቀማችን ሽሮ አሮብን በልተን እንኳን እያደርን አይደለም። አገራችን በሚፈልቅ ውኃ ተጠቅመን በመስኖም ማልማት እንችላለን። እንደ አገር ማደግ መበልጸግ እንፈልጋለን። አገራችን የምትለማ ከሆነ የሰው አገር መሰደድ ይቀራል። በአገራችን ሰርተን እንበላለን፣ ሥራ አጥነት ይቀርፍልናል። ይህ የዓባይ ግድብ ሙሌት በመጠናቀቁ እኮ እንኳን እኛን የሞተ ሰው ይደሰታል። ደስታዬ ወደር የለውም›› ሲሉ ተደምጠዋል።


ቅጽ 3 ቁጥር 142 ሐምሌ 17 2013

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

error: Content is protected !!