የእለት ዜና

ለ500 ሥራ ፈጣሪ ሴቶች የገበያ ትስስር የሚፈጥር ድረ-ገጽ ለማልማት ድጋፍ ሊደረግ ነው

ለ500 ሥራ ፈጣሪ ሴቶች ለሚያመርቱት ምርት የገበያ ትስስር የሚፈጥር ድረ-ገጽ ለማልማት ድጋፍ ሊደረግ መሆኑን የፌደራል የከተሞች የሥራ ዕድል ፈጠራና ምግብ ዋስትና ኤጀንሲ አስታወቀ።
የፌደራል የከተሞች የሥራ ዕድል ፈጠራና ምግብ ዋስትና ኤጀንሲ በንግድ፣ በአገልግሎትና በምርት ዘርፍ የተሰማሩት የሴት ሥራ ፈጣሪዎችን ገቢ የሚያሳድግና ተጨማሪ የገቢ ምንጭ ያስገኛል ተብሎ የታሰበውን ድረ-ገጽ ለማልማት የክህሎት ሥልጠና ከሚሰጠው አፍሪካ-118 ከተባለ ድርጅት ጋር የመግባቢያ ሰነድ ተፈራርሟል።

ኤጀንሲውን ወክለው ዋና ዳይሬክተር ገብረመስቀል ጫላ ስምምነቱን የፈረሙ ሲሆን፣ በአፍሪካ-118 በኩል ደግሞ የሰው ኃብትና ሥራ ሂደት ዳይሬክተር የሆኑት ምስጋናው አለሙ የስምምነት ፊርማውን ፈርመዋል።
አፍሪካ-118 ኬኒያ፣ኡጋንዳና ታንዛኒያን ጨምሮ በአምስት የአፍሪካ አገራት ላይ እንደሚሰራ የገለጹት የድርጅቱ የሰው ኃብትና ሥራ ሂደት ዳይሬክተር የሆኑት ምስጋናው፣ በፕሮጀክቱ የታቀፉ ደንበኞች በኦንላየን የግብይት ዘርፍ /e-commerce/ ተጠቃሚ እንዲሆኑ፣ ምርቶቻቸውን እንዲሸጡ እና ድረ-ገጽ እንዲኖራቸው በማድረግ ተደራሽነታቸውን ለማስፋት ያለመ ፕሮጀክት መሆኑን ገልጸዋል።

ይህ ፕሮጀክት በ Norwegian Agency Development Corporation ድጋፍ የሚካሄድ ሲሆን፣ የሙከራ ጊዜውም ሦስት ዓመት መሆኑ ታውቋል። በመግባቢያ ስምምንቱ መሰረት ፕሮጀክቱ ለ500 መቶ ሴት ሥራ ፈጣሪዎች ድረ- ገጽ በማልማት፣ የዲጂታል ክህሎት እና የፋይናንስ ሥልጠናዎችን ለመስጠት አቅዷል።

ሥልጠናው ከሚሰጣቸው ሴት ሥራ ፈጣሪዎች መካከል ኹለት መቶ ሃምሳዎቹ ከአዲስ አበባ የሚመረጡ ሲሆኑ፣ ቀሪዎቹ ኹለት መቶ ሃምሳ ሴቶች ደግሞ ከሌሎች ፕሮጀክቱ ከሚካሄድባቸው የክልል ከተሞች የሚመረጡ መሆኑን ኤጀንሲው በሰጠው መግለጫ ላይ አሳውቋል።
የፌደራል የከተሞች የሥራ ዕድል ፈጠራና ምግብ ዋስትና ኤጀንሲን ወክለው ስምምነቱን የተፈራረሙት የኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተር ገብረመስቀል፣ አፍሪካ-118 ከተቋማቸው ጋር ለመሥራት ስለመረጠ እና በሌሎች የአፍሪካ አገራት ያለውን ልምድ ለማካፈል ስለመጣ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

በዚህ ፕሮጀክት የታቀፉ ሴት ሥራ ፈጣሪዎች ገቢ እያደገ በመሆኑ እና የመበደር አቅማቸውም እየጨመረ በመምጣቱ ከባንክ ጋር የማገናኘት ሥራ እየተሠራ እንደሆነ በመግለጫው ላይ ተነስቷል።
ከአፍሪካ-118 የተደረገው ስምምነት ምርትና አገልግሎታቸውን በማስተዋወቅ ለአገር ውስጥና ለውጭ ደንበኞች ተደራሽ እንዲሆኑ በማደረግ ለሴት ሥራ ፈጣሪዎች የተሻለ የገበያ መንገድን እንደሚያመቻች ተገልጿል።
የሴት ሥራ ፈጣሪዎች ልማት ፕሮጀክት፣ በፌደራል የከተሞች የሥራ ዕድል ፈጠራና ምግብ ዋስትና ኤጀንሲ ስር የተደራጀ ሲሆን፣ በአስር ዋና ዋና ከተሞችና ከእነዚህ ከተሞች በቅርብ ርቀት በሚገኙ ሰማኒያ ዘጠኝ ከተሞች በአጠቃላይ ከ 42 ሺሕ በላይ የተመዘገቡ ሴት ሥራ ፈጣሪ ደንበኞች እንዳሉት ተመላክቷል።

በዚህ ፕሮጀክት ከሚሳተፉ ሴት ሥራ ፈጣሪዎች መካከል ከ 23 ሺሕ ለሚበልጡት ሥልጠና እንደተሰጠ የጠቀሰው የፌደራል የከተሞች የሥራ ዕድል ፈጠራና ምግብ ዋስትና ኤጀንሲ፣ ከ18 ሺሕ ለሚበልጡ ደግሞ ከ 5 ቢሊዮን ብር በላያ የብድር ተጠቃሚ ማድረግ እንደቻለ በመግለጫው ላይ አሳውቋል።

በተጨማሪም አፍሪካ-118 እስከ 2021 ማብቂያ ድረስ ለ አራት ሽሕ የፕሮጀክቱ ተጠቃሚ ሴት ሥራ ፈጣሪዎች የዲጅታል ክህሎት እና የፋይናንስ ሥልጠናዎችን ለመስጠት እቅድ መያዙም ስምምነቱ በተፈረመበት ወቅት ተገልጿል።


ቅጽ 3 ቁጥር 142 ሐምሌ 17 2013

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com