የእለት ዜና

የጥላቻ ንግግር የሚያደረጉ ግለሰቦችን ለፍርድ ማቅረብ አልተቻለም ተባለ

የጥላቻ ንግግር በማድረግ የተጠረጠሩ ግለሰቦችን ለፍርድ አቅርቦ ቅጣት እንዲያገኙ ለማድረግ መቸገሩን የፌዴራል ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ገለጸ።
የጥላቻ ንግግሮችን የሚናገሩ፣ የሚጽፉ እና የሚያሰራጩ ግለሰቦችን ለመቆጣጠር ያስችል ዘንድ በርካታ የሕግ ሥራዎች ተግባራዊ ቢደረጉም፣ የወንጀሉ አሳሳቢነት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየከፋ መምጣቱን የፌዴራል ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ የፕሬስ ሴክሬታሪያት ኃላፊ አወል ሱልጣን ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።

ይህ የሆነውም የጥላቻ ንግግረ በማድረግ የተጠረጠሩ ግለሰቦችን ችሎት አቅርቦ ማስቀጣት ስላልተቻለ እንደሆነ አስረድተዋል።
ለዚህም ዋነኛ ምክንያት የጥላቻ ንግግርን በሚመለከት አዋጅ ላይ የወጡ ሕጎች ምን ያህል ለማሕበረሰቡ ግልጽ እና ፋይዳቸው የጎላ ነው የሚሉት ጥያቄዎች ባለመመለሳቸው እንደሆነም አንስተዋል።
አክለውም በተለይ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በኢትዮጵያ በአይነትም፣ በስፋትም የጥላቻ ንግግር እየጨመረ ይገኛል ብለዋል። ለዚህ ደግሞ የሚጠቀሰው አንዱ ምክንያት፣ የማኅበራዊ የመገናኛ ብዙኃን አውታሮች በጊዜ እና በፍጥነት ይዘታቸውን ባለማረማቸው ነው ተብሏል።
የጥላቻ ንግግር ሰዎች በማንነታቸው ወይንም በብሔር፣ በጾታ እና በኃይማኖት እንዲገለሉ፣ እንዲጠሉ እና ጥቃት እንዲደርስባቸው የሚያደርግ መሆኑን አጽንኦት ሰጥተወበታል።
በዚህም ረገድ የጥላቻ ንግግር ከስሜት የሚመነጭ ጽንሰ ሐሳብ ነው ያሉት ኃላፊው፣ በዚህም ለጉዳዩ ብያኔ ለመስጠት አስቸጋሪ ነው ሲሉም አመልክተዋል።

ሐሳብን በነጻነት የመግለጽ መብት በሕገ-መንግሥቱ ብቻ ሳይሆን ሕገ-መንግሥቱን ለመተርጐም እንደ አጋዥ ተደርገው በሚቆጠሩና የአገሪቱ የሕግ ስርዓት አካል በሆኑት ዓለም ዐቀፍ የሰብዓዊ መብት ስምምነቶችም የተካተተ ነው።
በኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት እውቅና ከተሰጣቸው መብቶች አንዱ ሐሳብን በነጻነት የመግለጽ መብት መሆኑን የጠቀሱት የፕሬስ ሴክሬታሪያት ኃላፊው፣ ይህን መብት ለወንጀል የሚጠቀሙ ሰዎች ግን ተበራክተዋል ብለዋል።
የጥላቻ ንግግር የሰውን ልጅ ክብር የሚጎዳ፣ በተለይም ልዩ መገለጫ በመለጠፍ ፣ለምሳሌ የቆዳ ቀለሙ፣ ብሔሩ እና ኃይማኖቱን መሰረት በማድረግ፣ ከማሕበረሱ የማግለያ እና የመነጠያ መንገድ ነው።
በተለይም የጥላቻ ንግግር እና ሐሰተኛ መረጃዎች በጽሑፍ፣ በምስል ወይም በድምጽ ሲነገሩ በሕብረተሰቡ ዘንድ ያልተገባ መልዕክትን እንደሚያስተላልፉ ይነገራል።
የመጀመሪያው የጥላቻ ንግግር ተጠቂውን ግለሰብ ወይንም ቡድን ከሰውነት በማውረድ ብሎም በራስ መተማመንን በማጉደል የሚፈጸም ነው።

ከዚህ ባሻገር የጥላቻ ንግግር የራስን ሰው ወይንም ቡድን በስጋት ውስጥ እንዳለ በመቁጠር ሌሎች ሰዎች የጥላቻ ንግግሩን እንዲቀላቀሉት እና እንዲዘምቱበት የሚያደርግ በመሆኑ እንደሚያስቀጣ አዋጁ ላይ ተቀምጧል።
ለዚህም መሰረት እንዲሆን የፌዴራል ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ግንዛቤን ለመፍጠር እየሠራ እና አዋጁን ተግባራዊ በማያደርጉ ግለሰቦች ላይ እርምጃዎችን ለመውሰድ እየተገደደ መምጣቱን አስታውቀዋል።
ማንኛውም ዜጋ ሐሳብን በነጻነት የመግለጽ መብት እንዳለው ሁሉ፣ በሕጉ የተደነገጉ ግዴታዎችን በማገናዘብ ዜጎች ከወንጀል እራሳቸውን እንዲያርቁ እና ይህን ተግባር የሚፈጽሙ ግለሰቦችን በመጠቆም የዜግነት ግዴታዎችን እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል።


ቅጽ 3 ቁጥር 142 ሐምሌ 17 2013

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

error: Content is protected !!