የእለት ዜና

የጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዝ ልማት ባንክ ሊቋቋም መሆኑ ተገለጸ

የጥቃቅን፣ አነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች ልማት ባንክ ለማቋቋም የዳሰሳ ጥናት ማካሄዱን የፌዴራል የከተሞች የሥራ ዕድል ፈጠራና ምግብ ዋስትና ኤጄንሲ ለአዲስ ማለዳ አስታወቀ።
የጥቃቅን፣ አነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዝ ልማት ባንክ ለማቋቋም የተዘጋጀው የጥናት ሰነድ ለባለድርሻ ተቋማት ቀርቦ ውይይት እየተደረገበት ሲሆን፣ በዳሰሳ ጥናቱ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ፣ የፌደራል ሥራ ዕድል ፈጠራ ኮሚሽንና የክልሎች ብድርና ቁጠባ ተቋማት ተገኝተው ባንኩን ለማቋቋም የሚያስችል ሐሳብ አጋርተዋል ተብሏል።

ኤጀንሲው የጥቃቅን፣ አነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዝ ባንክ ለማቋቋም ያዘጋጀውን የጥናት ሰነድ ለውሳኔ ሐሳብ ለብሔራዊ ባንክ ለማቅረብ የአዋጭነት ጥናት እያስጠና መሆኑን የኤጀንሲው የኮሚዩኒኬሽን ባለሙያ በኃይሉ ንጉሴ ጠቁመዋል። ኤጀንሲው የጀመረው የጥቃቅንና አነስተኛ ባንክ የማቋቋም ሒደት በባለድርሻ ተቋማት ተቀባይነት ማግኘቱን ተከትሎ ነው የሚቋቋመውን ባንክ አዋጭነት እያስጠና የሚገኘው፣ ሲሉ በኃይሉ ገልጸዋል።

የጥቃቅን፣ አነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዝ ልማት ባንክ ለማቋቋም የተጀመረው ሥራ በዋናነት በዘርፉ የሚታየውን የገንዘብ አቅርቦት እጥረት ለመፍታት ያለመ ነው ተብሏል። በኢትዮጵያ የምጣኔ-ሐብት ዕድገት ውስጥ ጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕይዞች የሥራ ዕድል ለመፍጠርና ድህነትን ለመቀነስ በሚደረገው ጥረት ፋይዳቸው የጎላ ቢሆንም፣ ኢንተርፕራይዞቹ ሙሉ አቅማቸውን ተጠቅመው በዘላቂነት እንዳያድጉ ከሚያደርጓቸው ችግሮች መካከል የገንዘብ እጥረት አንዱ መሆኑ በጥናቱ ተለይቷል።

ኤጀንሲው ባስጠናው ጥናት በኢትዮጵያ የጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች ልማትን ለማሥፋፋት በገንዘብ ድጋፍ በኩል የሚያጋጥሙ ማነቆዎችን ለመቅረፍ፣ የጥቃቅን፣ አነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች ልማት ባንክ ለማቋቋም መታሰቡ ተመላክቷል።
ኤጀንሲው ባካሄደው የፍላጎት ጥናት፣ አነስተኛ ፋይናንስ አቅራቢ ተቋማት የዲጂታል-ባንኪንግ ቴክኖሎጂዎችን የማይጠቀሙ፣ የቁጠባና ብድር አገልግልቶች በስፋት ተደራሽ የማያደርጉ፣ በቢሮክራሲ የታጠረ አሰራራቸው ለብልሹ አሰራር የሚዳርግ መሆኑ፣ በአነስተኛ ፋይናንስ ተቋማት የሚቀርበው የብድር ጣራ፣ የወለድ ምጣኔና የዋስትና አማራጮች ከሌሎች የግልና የመንግሥት ባንኮች አንፃር በንጽጽር ሲታይ ከፍተኛ ልዩነት መኖሩና የአንቀሳቃሾችን የፋይናንስ ፍላጎት ያላሟላ መሆኑ በጥናቱ ተረጋግጧል።

በመሆኑም የጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች ለአገሪቱ የኢኮኖሚ ዕድገት የሚያበረክቱትን ከፍተኛ አስተዋጾ ግምት ውስጥ በማስገባት፣ ኹለም የፋይናንስ ተቋማት፣ የልማት ድርጅቶች፣ የዘርፉ ልማት አንቀሳቃሾችና ባለድርሻ አካላት፣ እንዲሁም ፈላጎት ያላቸው የሕብረተሰብ ክፍሎች የጥቃቅን፣ አነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች ልማት ባንክ ሲቋቋም፣ አክሲዮን በመሸጥ የባንክ ባለቤት እንዲሆኑ ለማድረግ ዕቅድ ተይዟል።

በዚሁ መሰረት የቁጠባና ብድር፣ የሐዋላ፣ የማይክሮ ኢንሹራንስ፣ የሦስተኛ ወገን ገንዘብ ማስተዳደርና አጠቃላይ የባንክ አገልግሎቶችን በተቀላጠፈ ሁኔታ እንዲያገኙ፣ በመንግሥት አስፈፃሚ አካላት አማካይነት የዘርፉን ልማት የሚያፋጥኑ የፋይናንስ ፖሊሲ፣ ስትራቴጂና የሕግ ማዕቀፎችን በመቅረጽ የጥቃቅን፣ አነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች ልማት ባንክ በአክሲዮን ማኅበር ማቋቋም እንደሚገባ በጥናቱ ውጤት ላይ ተጠቁሟል።

የሚቋቋመው የጥቃቅን፣ አነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዝ ልማት ባንክ በዋናነት በኢንተርፕራይዞች ባለድርሻነት የሚመራ ሆኖ፣ በዘርፉ የሚታየውን የገንዝብ አቅርቦት ችግር እንደሚፈታ ይጠበቃል። እስካሁን በዘርፉ ላይ ከሚታዩ ቀዳሚ ችግሮች የገንዘብ አቅርቦት እጥረትና የሚቀርበው የገንዝብ ብድር የወለድ ምጣኔ እንደሆነ ተመላክቷል።

የጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዝ አንቀሳቃሾች ለሥራ መነሻ የሚሆን የካፒታል ምንጭ የሚያገኙት ከቤተሠብ ዕርዳታ 44 በመቶ፣ በራስ ገንዘብ 41 በመቶ እና ከብድር 16 በመቶ መሆኑን ኤጀንሲው ባካሄደው ጥናት ገልጿል።
በአነስተኛ ፋይናንስ አቅራቢ ተቋማት የቁጠባና ብድር አገልግሎት በስፋት ተደራሽ አለመደረጉና የአገልግሎት አሰጣጥ ሥርዓቱ የሚያበረታታ አለመሆኑ፣ ብድር የወሰዱ ኢንተርፕራይዞች የወሰዱትን ገንዘብ ውጤታማ በሆነ መንገድ መጠቀም እንይችሉ አድርጓል ሲል ጥናቱ ገልጿል።


ቅጽ 3 ቁጥር 142 ሐምሌ 17 2013

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

error: Content is protected !!