የእለት ዜና

‘በሳውዲ አረቢያ ላሉ ወገኖቻችን ድምፅ እንሁን’ በሚል ርዕስ የበይነ መረብ ውይይት ተካሄደ

በኢትጵያዊያን ዜጎች ላይ እየተፈጠሩ ያሉ ጫናዎችን የሚያወግዙ ሰልፎች በአሜሪካ ዋሽንግተን ዲሲና በአዲስ አበባ ከተሞች ለማካሄድ ታቅዷል።

‘በሳውዲ አረቢያ ላሉ ወገኖቻችን ድምፅ እንሁን’ በሚል ርዕስ በኢትዮጵያ ዳያስፖራ ኤጀንሲና በኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ የወጣቶች ሕብረት ትብብር የበይነ መረብ ውይይት መካሄዱ ተገለፀ፡፡

ውይይቱ በሃይማኖት አባቶች ቡራኬ የተጀመረ ሲሆን፣ የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር ወ/ሮ ሰላማዊትም በክብር እንግድነት ተገኝተው መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡

ዋና ዳይሬክተሯ በመልዕክታቸው ዜጎች በየትም ሃገር ቢኖሩ መብትና ጥቅማቸው ተጠብቀ መኖር እንዲችሉ ኤጀንሲው ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በትብብር እንደሚሰራ አንስተው፣ በሳውዲ አረቢያ የሚኖሩና በችግር ውስጥ ያሉ ዜጎችም ወደ ሃገራቸው እንዲመለሱ ኤጀንሲው ላለፉት ስድስት ወራት በርካታ ተግባራትን ሲያከናውን መቆየቱን ገልጸዋል፡፡

በተከናወነው ስኬታማ ቅንጅታዊ ስራ አማካኝነትም አስቀድሞ ከሳውዲ መንግስት ጋር በተደረሰው ስምምንት መሰረት ከ40ሺ በላይ በችግር ላይ የነበሩ ኢትዮጵያውያንን ወደ ሃገራቸው መመለስ እንደተቻለም ዳይሬክተሯ አስረድተዋል፡፡

ሆኖም አሁንም በርካታ ቁጥር ያላቸው ዜጎች ለእንግልት የሚዳረጉበት ሁኔታ መኖሩን መረጃዎች እንደሚያሳዩ ገልጸው፣ ለችግሩ ዘላቂ መፍትሔ ማበጀት እንዲቻል በመንግስት በኩል የተጀመሩ የስራ ስምምንት ውሎች ሙሉ በሙሉ ወደ ስራ እንዲገቡና ወደ ውጭ የሚደረጉ የስራ ጉዞዎችም ህጋዊ እንዲሆኑ ማድረግ እንደሚገባ ጠቅሰዋል፡፡

በሳውዲ አረቢያ የኢፌዴሪ ባለ ሙሉ ስልጣን አምባሳደር አምባሳደር ሌንጮ ባቲም በበኩላቸው በሚሲዮኑ በኩል የዜጎችን መብትና ጥቅም ለማስከበር በርካታ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑን አንስተው፣ ከችግሩ ስፋትና ውስብስብነት አንጻር ግን አሁንም ብዙ መስራት እንደሚጠበቅባቸው ገልጸዋል፡፡ በዋሽንግተን የኢፌዴሪ ባለሙሉ ስልጣን አምባሳደር አምባሳደር ፍጹም አረጋም በአሜሪካ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያንን በማስተባበር በሳውዲ አረቢያ የሚኖሩ ዜጎቻችን ላይ የሚደርሰውን እንግልት ለመቀነስ ድጋፍ መደረጉን አንስተው፣ ይኸው ድጋፍ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጸዋል፡፡

በመድረኩ ላይ የተሳተፉ ዜጎችም እየደረሰባቸው ያለው እንግልት እንዲቀንስ ሳውዲ አረቢያ በሚገኙ የኢፌዴሪ ሚሲዮኖችና በመንግስት በኩል መከናወን አለባቸው ባሏቸው ጉዳዮች ላይ ጥያቄና አስተያየቶችን አቅርበው ምላሽ ተሰጥቶባቸዋል፡፡

በመድረኩ ማጠቃለያ ላይ በሳውዲ አረቢያ በዜጎቻችን ላይ እየተፈጠሩ ያሉ ጫናዎችን የሚያወግዙ ሰልፎች በአሜሪካ ዋሽንግተን ዲሲና በአዲስ አበባ ከተሞች ለማካሄድ መታቀዱን የኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ የወጣቶች ሕብረት መስራችና የመድረኩ አስተባባሪ ወጣት ቢኒያም ጌታቸው መግለፃቸውን ከኢትዮጵያ ዲያስፖራ ኤጀንሲ ያገኘነው መረጃ ያስረዳል፡፡

 

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

error: Content is protected !!