የእለት ዜና

ፓስተር ዮናታን የገዛው ትምህርት ቤት የግለሰቦችን ቤት ለማስፋፊያ ማካተቱ ቅሬታ አስነሳ

ፓስተር ዮናታን አክሊሉ ገዝቶታል የተባለው ገርጂ ኮርያ ሆስፒታል አካባቢ የሚገኘው እንቡጥ ትምሕርት ቤት በአካባቢው የሚገኙትን የግለሰብ እና የቀበሌ ቤቶች ለማስፋፊያ ሊወስድ መሆኑ ቅሬታን አስነሳ፡፡

ፓስተር ዮናታን ትምህርት ቤቱ ከሚገኝበት ይዞታ በተጨማሪ የግለሰብ መኖሪያ ቤቶችን ያለነዋሪዎቹ ፍቃድ ልውሰድ ማለቱ የፈጠረባቸውን ቅሬታ ነዋሪዎቹ ለአዲስ ማለዳ አቅርበዋል፡፡

ዮናታን ገዝቶታል የተባለው ይህ ትምህርት ቤት በ60 ሚሊየን ብር የተሸጠ ሲሆን፣ ከዓመት በፊት ተዘግቶ በአሁኑ ሰዓት በኃይማኖት ተቋምነት እያገለገለ ይገኛል፡፡

የከተማ አስተዳደሩ ካቢኔ ሚያዝያ 5/2013 የማስፋፊያ ቦታውን ያለባለቤቶቹ ፍቃድ እንዲያስፋፋ መወሰኑን አዲስ ማለዳ ማወቅ ችላለች፡፡

ቅሬታ አቅራቢዎቹ ለገዢው አናስረክብም ያሉት በአዲስ አበባ ከተማ በቦሌ ክፍለ ከተማ በወረዳ 13 ክልል አለምነሕ ጋራዥ አካባቢ በአጠቃላይ 2900 ካ.ሜ የሚሸፍን ቦታ ሲሆን፣ ነዋሪዎቹም በቦታው ላይ ለረጅም ዓመታት የኖሩ ናቸው፡፡

ቅሬታ አቅራቢዎቹ ስለውሳኔው ባላወቁበት ሁኔታ የክፍለ ከተማው የመሬት ልማት ፅሕፈት ቤት እና የወረዳው ባለስልጣናት በገለጹላቸው መሰረት፣ ሰኔ 30/ 2013 ይዞታቸው ለኢትዮጵያ ወንጌላውያን አብያተ ክርስትያን ሕብረት አዲስ ኪዳን ካሕናት አለም አቀፍ ቤተክርስትያን በመሰጠቱ እንዲለቁ ስለተነገራቸው ነው ቅሬታውን ያነሱት፡፡

ከቦታው እንዲለቁ ከተነገራቸው መካከል ከ6 በላይ የግለሰብ ቤቶች፣ የመረዳጃ እድር፣ ለይዞታው የባለሀብትነት ማረጋገጫ ሰነድ ካርታ ያለው ትልቅ ጋራዥ እና በርካታ የቀበሌ ቤቶች ይገኙበታል፡፡

የግለሰብ ቤቶቹ የቅርብ ጊዜ የአየር ላይ ካርታ ያላቸው ሲሆን፣ የከተማ አስተዳደሩ ካቢኔ ማስፋፊያውን የፈቀደው በቀድሞው 80ዎቹ ላይ በነበረው የአየር ላይ ካርታ ነው፡፡

ይሕንን መሰረት በማድረግ እና የተለያዩ ጥያቄዎችን ይዘው ባሳለፍነው ሳምንት ለከተማ አስተዳደሩ ምክትል ከንቲባ አዳነች አቤቤ ጋር ቀርበው አቤቱታቸውን አሰምተው ነበር፡፡

በአዋጅ 1161/2012 መሬት ለሕዝብ ጥቅም ተብሎ ሊለቀቅ የሚችለው የልማት ስራው በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ መንገድ ማሕበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ልማትን ለማጎልበት በፀደቀ በመሬት አጠቃቀም እና ልማት እቅድ፣ በመሰረተ ልማት መሪ ፕላን መሰረት (Structural Plan) ለሕዝብ የተሻለ የጋራ ጥቅም እና እድገት ያመጣል ተብሎ የተወሰነ ከሆነ እንደሆነ መረጃዎች ያሳያሉ፡፡

ለከተማ አስተዳደሩ ካቀረቡ ቅሬታዎች መካከል፣ “ህጉ የሚለው የልማት ተነሺዎች አካባቢውን የማልማት አቅም ከሌላቸው ለሌላ ማስተላለፍ እንዳለባቸው ነው” የሚሉት ቅሬታ አቅራቢዎቹ፣ አካባቢውን ባላቸው አቅም እና ከተማዋ በሚያስፈልጋት የልማት ደረጃ ለማልማት እየተንቀሳቀሱ መሆኑን ለአዲስ ማለዳ አስረድተዋል፡፡

በተጨማሪም በደንብ ቁጥር 472/2012 አንቀጽ 3 እና 8 እንደሚለው የከተማ አስተዳደሩ የመሬት ልማት እና ማኔጅመንት ቢሮ የውሳኔ ሀሳቡን ከማቅረቡ በፊት በይዞታው ላይ መብት ያላቸው አካላት እንዲወያዩ ማድረግ ግዴታ መሆኑ እየታወቀ አለማወያየቱ ተገቢ እንዳልነበር ነው ያነሱት፡፡

ቅሬታ አቅራቢዎቹ አያይዘውም በአዋጅ ቁጥር 1161/2011 እና ደንብ ቁጥር 472/2012 የልማት ተነሽ ከይዞታው ላይ ከመነሳቱ በፊት ሊፈጸሙ ስለሚገባቸው ቅድመ ሁኔታዎች እና ስለካሳ አከፋፈል፣ እንዲሁም ምትክ ቦታ አሰጣጥ በቀድሞ ሕግ ውስጥ ያልነበሩ አዳዲስ ሀሳቦችን በማካተት የተነሺዎችን መብት ለማስከበር የሚቻልበትን ስርአት የዘረጉ ሕጎች መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡

ነገር ግን አዋጅ ቁጥር 1161/2011 በግልፅ አዋጅ ቁጥር 455/1997ን ሽሮታል፡፡ እንዲሁም ደንብ ቁጥር 472/2012 በግልፅ ደንብ ቁጥር 135/1999ን ሽሮታል፡፡

በመሆኑም የክፍለ ከተማው አስተዳደር አዲስ ለወጡት አዋጅ ቁጥር 1161/2011 እና ደንብ ቁጥር 472/2012 መመርያ እንዲወጣ በማድረግ ሊያስፈጽም ሲገባ በተሻረ መመርያ እያስተናገደን መሆኑ ፍትሀዊ አይደለም ብለዋል፡፡

የቅሬታ አቅራቢዎቹ ዋነኛ ጥያቄም ለካቢኔ የቀረበው የውሳኔ ሀሳብ አሁን በተግባር በይዞታው ላይ ያለውን እውነታ ያላገናዘበ ይልቁንም ካቢኔው ፍትሐዊ ያልሆነ ውሳኔ እንዲሰጥ ባደረገው መልኩ በተሳሳተ መረጃ ላይ የተመሰረተ ነው የሚል መሆኑን አዲስ ማለዳ ለማወቅ ችላለች፡፡

በቀን 15/2013 ቅሬታ አቅራቢዎቹ የመሬት ልማት ማኔጅመንት በመሄድ በምን መስፈረት ማስፋፊያውን እንደፈቀደ መጠየቃቸውም ታውቋል፡፡

አዲስ ማለዳ ትምህርት ቤቱን ለገዛው ፓስተር ዮናታን አክሊሉ እንዲሁም ባለቤቱ ጋር በተደጋጋሚ ስልክ ብትደውልም ምላሽ ማግኘት አልቻለችም፡፡

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

error: Content is protected !!