የእለት ዜና

በኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ የልብ የደም ስር እና የልብ በር ቀዶ ጥገና በአንድ ላይ ተካሄደ

በኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ 6 ሰዓታትን የፈጀ የልብ የደም ስር ነቅሎ መትከል እና የልብ በር ቀዶ ጥገና መካሄዱን የጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ሐኪም ገለጹ፡፡

ቀዶ ጥገናውን ለየት የሚያደርገው የልብ የደም ስር ነቅሎ መትከል እና የልብን በር ቀዶ ጥገና በአንድ ላይ መደረጉ መሆኑን በጥቁር አንበሳ የልብ ማዕከል የልብ ቀዶ ሐኪም ዶ/ር ፈቀደ አጉዋር ገለፁ።

ዶክተሩ እንዳሉት ከሆነ ሁለቱ ችግሮች በአንድ ላይ የመከሰታቸው ሁኔታ በጣም አነስተኛ ነው።

የ55 ዓመት እድሜ ያላቸው ታካሚ በግራ በኩል ያለው የልባቸው በር በከፍተኛ ሁኔታ በመጥበቡ እና ደም አላሳልፍ በማለቱ ህይወታቸው በአስጊ ሁኔታ ላይ እንደነበር አስረድተዋል።

አብዛኛው ጊዜ እድሜያው ከ50 ዓመት በላይ የሆኑ ሰዎች የልብ በር መጥበብ እና የልብ ደም ስሮች ሊዘጉ ይችላሉ፤ ይህም በስኳር፣ በደም ግፊት እና በተለያዩ ተያያዥ ጉዳዮች ሊከሰቱ ይችላል ብለዋል።

ቀዶ ጥገናው ሀላፊነት መውሰድ የሚፈልግና ምን ሊፈጠር እንደሚችል ለማወቅ የሚከብድ እንደነበር የገለፁት ዶክተር ፈቀደ በትላንትናው እለት ከቀኑ 8 ሰዓት ተጀምሮ ምሽት 2 ሰዓት ላይ በስኬት መጠናቀቁን ገልጸዋል።

የተዘጋው የልብ የደም ስር በመከፈቱ ደም በአግባቡ ሊተላለፍ ችሏል፤ ውጤቱም እጅግ የተሳካ እና በሀገራችን ለመጀመሪያ ጊዜ የተከናወነ ነው ማለታቸውን ኢቢሲ ዘግቧል።

ታማሚው በአሁኑ ጊዜ በጥሩ ሁኔታ ላይ እንደሚገኙም ገልፀው፤ ከቀዶ ጥገናው በኋላ ልብ እና ሳንባ ወደ ቀደመ ስራቸው መመለሱ ለእኛ ትልቅ ደስታን ፈጥሯል ሲሉም ዶክተሩ ተናግረዋል።

ታካሚው ውጭ ሄዶ ቢታከም እስክ 50 ሺህ የአሜሪካ ዶላር ድረስ ሊያስወጣ እንደሚችልም ነው ጨምረው የተናገሩት።

የልብ ቀዶ ጥገና ህክምና የተከናወነው ሆሌዜር የልብ ህክምና ማእከል ውስጥ መሆኑም ተገልጿል።

 

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

error: Content is protected !!