የእለት ዜና

ለተሰንበት ጊደይ የ10 ሺህ ሜትር ክብረ ወሰን ጸደቀ

ከአንድ ወር በፊት በሁለት ቀናት ልዩነት ውስጥ ከ15 ሰከንዶች በላይ ተሻሽሎ በኢትዮጵያዊቷ ለተሰንበት ጊደይ እጅ የገባው የ10 ሺህ ሜትር ክብረ ወሰን መፅደቁ ተገለፀ።

የዓለም አትሌቲክስ የበላይ አካል ታላቁ የኦሊምፒክ ውድድር በቶኪዮ ከተጀመረ ከቀናት በኋላ እንዳሳወቀው፤ ከአራት ዓመት በፊት በሪዮ ኦሊምፒክ ላይ በኢትዮጵያዊቷ አልማዝ አያና ተይዞ የነበረው የ10 ሺህ ሜትር ክብረ ወሰን በሁለት አትሌቶች በተከታታይ መሰበሩን አጽድቋል።

የውድድሩ ክብረ ወሰን በቀዳሚነት በትውልደ ኢትዮጵያዊቷ የኔዘርላንድስ ዜጋ ሲፋን ሐሰን፤ ሄንግሎ ላይ ሰኔ 29/2013 ዓ. ም 29:06.82 በመሮጥ ከቀድሞው ሰዓት ላይ 10 ሰከንዶችን ያህል በማሻሻል ክብረ ወሰኑን በእጇ አስገብታ ነበር።

ነገር ግን የሲፋን ክብረ ወሰን ከሁለት ቀናት በላይ ሳይቆይ ለተሰንበት ጊደይ እዚያው ሄንግሎ ውስጥ 29:01.03 በመሮጥ በአምስት ሰከንዶች አሻሽላው ክብረ ወሰኑን ተቆጣጥራዋለች።

የዓለም አትሌቲክስ ተቋምም የሁለቱን ተከታታይ ክብረ ወሰኖች በይፋ ሳያጸድቀው ቆይቶ አሁን የርቀቱ ክብረ ወሰን ሆኖ መጽደቁን ዛሬ በድረ ገጹ ላይ ባወጣው መግለጫ አሳውቋል።

ለተሰንበት ባለፈው ዓመት ላይ 14:06.62 የሆነ ሰዓት በማስመዝገብ የዓለም የ5000 ሜትር ሩጫ ክብረ ወሰንን የሰበረች ሲሆን፤ በቀጣይም ሰዓቱን ከዚህም በላይ ለማሻሻል እንደምትሞክር ተናግራ ነበር።

ለተሰንበትና ሲፋን ጃፓን ላይ እየተካሄደ ባለው ኦሎምፒክ ላይ የሚሳተፉ ሲሆን፤ በ10,000 ሜትር ውድድርም የኦሎምፒክ የወርቅ ሜዳሊያ ለማጥለቅ እንዲሁም ክብረ ወሰኑን ለማሻሻል ይፋለማሉ።

ለተሰንበት በቶኪዮው ኦሊምፒክ ላይ በ10,000 ሜትር የምትወዳደር ሲሆን ሲፋን ግን ከ10,000 ሜትር በተጨማሪ በ1,500 እና 5,000 ሜትር እንደምትወዳደር መገለፁን ቢቢሲ ዘግቧል።

የዓለም አትሌቲክስ ከለተሰንበት እና ከሲፋን ክብረ ወሰኖች በተጨማሪ በተለያዩ የአትሌቲክስ ውድድሮች ክብረ ወሰን ያሻሻሉትን የኬሊ ሆጅኪንሰንን፣ የግራንት ሆሎዌይን እና የካርስቲን ዋርሆልምን ክብረወሰኖች ማጽደቁን ይፋ ማድረጉም ተገልጿል፡፡

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com