የእለት ዜና

ከደረጃ በታች የሆኑ 3 ሺህ 685 ነጥብ 2 ሜትሪክ ቶን የተለያዩ ገቢ ምርቶች ወደ ሀገር ውስጥ እንዳይገቡ ተደረገ

ከደረጃ በታች የሆኑ 3ሺህ 685 ነጥብ 2 ሜትሪክ ቶን የተለያዩ ገቢ ምርቶች ወደ ሀገር ውስጥ እንዳይገቡ መታገዳቸውን የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡

በተጠናቀቀው የ2013 በጀት አመት አስገዳጅ የኢትዮጵያ ደረጃ የወጣላቸው ምርቶችና አገልግሎቶች ጥራታቸው፣ ደህንነታቸውና ትክክለኛነታቸው ለማረጋገጥ በተደረገው የገቢና ወጪ እቃዎች ጥራት ቁጥጥር ስራ ብዛቱ 3 ሺህ 685 ነጥብ 2 ሜትሪክ ቶን የተለያዩ ገቢ ምርቶች እንዳይገቡ መታገዳቸው ተገልጿል።

ወደ አገር ውስጥ እንዳይገቡ ከታገዱት ምርቶች ውስጥም የኤሌክትሪክና የኮንስትራክሽን ዕቃዎች፣ የታሸጉ ምግቦች እንዲሁም የኬሚካል ምርቶች ከደረጃ በታች ሆነው በመገኘታቸው ወደ አገር ውስጥ እንዳይገቡ ታግደዋል፡፡

የሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የወጪና ገቢ ዕቃዎች ጥራት ቁጥጥር ዳይሬክቶሬት በበጀት አመቱ ለማከናወን ካቀደው የኢንስፔክሽን ሥራ 97 ነጥብ 7 በመቶ ያህሉን እንዳሳካም ገልጿል።

ዳይሬክቶሬቱ በ685 ሺህ 500 ሜትሪክ ቶን  የወጪ ምርቶች ላይ የኢንስፔክሸን ሥራ ለማከናወን አቅዶ በቁጥር በ620 ሺህ 760 ነጥብ 5 ሜትሪክ ቶን ምርቶች ላይ የኢንስፔክሽን ሥራ በማከናወን ፈቃድ መስጠቱን አስታውቋል፡፡

ዳይሬክቶሬቱ ወካይ ናሙናዎችን ለኢትዮጵያ ተስማምነት ምዘና ድርጅት በመላክ ከሚያደርገው የላብራቶሪ ፍተሻ እና የኢንስፔክሽን ስራዎች በተጨማሪ ወደ አገር ውስጥ የሚገቡ የውሃ ፓምፕና የሶላር ቴክኖሎጂ ምርቶችን በሦስተኛ ወገን አለም አቀፍ የጥራት ማረጋገጫ ሰርተፊኬት እያቀረቡ እንዲስተናገዱ ማድረጉንም ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ገልጿል፡፡

በአጠቃላይ በበጀት አመቱ በሁሉም ቅ/ጽ/ቤቶች የኢንስፔክሽን ስራዎችን በማከናወን የኢትዮጲያን ደረጃ ያሟሉ ምርቶች ወደ ሀገር ውስጥ እንዲገቡ ወይም ከሀገር እንዲወጡ ፍቃድ መሰጠቱን ከንግድና ኢንደስትሪ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያስረዳል፡፡

አስገዳጅ የኢትዮጵያ ደረጃን ያላሟሉ የገቢ ምርቶች ወደ አገር ውስጥ እንዳይገቡ በማድረግ የህብረተሰቡን ጤና እና የአካባቢን ደህንነትን እንዳይጎዱ መደረጉም በሪፖርቱ ላይ ተገልጿል፡፡

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

error: Content is protected !!