የእለት ዜና

የሴት መራጮች ውሎ

ኢምፓቲ ፎር ላይፍ ኢነተግሬትድ ዴቨሎፕመንት አሶሴሽን(ኤሊዳ) የተቀናጀ የልማት ሥራን በመሥራት ሴቶችን፣ ልጃገረዶችን፣ ወጣቶችን እና ህጻናትን በትምህርት፣ በጤና እና በኢኮኖሚ በመደገፍ እንድሁም በዴሞክራሲ ባህል ግንባታ እና ዘላቂ ሰላም ላይ የሚሠራ እና ማኅበራዊ ኀላፊነታቸውን የሚወጡ ፣ ምርታማ እና አርቆ አሳቢ ዜጎችን ለማፍራት በማለም 2008 (እ.ኤ.አ)ሴቶች የተመሠረተ አገር በቀል የሲቪክ ማኅበረሰብ ድርጅት ነው፡፡

በዚህ ገፅ ላይ የተካተቱ የተለያዩ አካላት ሐሳቦች የኤሊዳንም ሆነ የድጋፍ ሰጪ ድርጂቱን አቋም ላያንጸባርቁ ይችላሉ፡፡

በ2013 የኢትዮጵያ አገራዊ ምርጫ የመራጭ ሴቶች ቁጥር ከፍ ብሎ መታየቱን በርካታ ታዛቢዎች ጠቁመዋል። በየምርጫ ጣቢያው ከታዩ ረጃጅም ሰልፎች ላይ በርካታ ነጠላ የለበሱ፣ ልጆቻቸውን ያዘሉና ያስከተሉ እናቶችና አያቶች፣ በጋራና በተናጠል የተሰለፉ ወጣት ሴቶች ደከመንና ሰለቸን ሳይሉ፣ ዝናብና ፀሐይ ሳይበግራቸው ድምጻቸውን ሲሰጡ ተስተውለዋል፡፡ ማንበብም ሆነ መጻፍ አለመቻላቸው ያልገደባቸውን ጨምሮ ዱላና መቋሚያቸውን ተደግፈው፣ ነፍሰጡር መሆናቸውን ሰበብ ሳያደርጉ እጅግ ብዙ ኢትዮጵያዊያት በሰኔ 14/2013 ውሎአቸውን በየምርጫ ጣቢያው አድርገዋል።

በአገሪቱ ወቅታዊ ሁኔታ ግራ የተጋቡ፣ የልጆቻቸውና የቤተሰባቸው እጣ ፋንታ መስቀለኛ መንገድ ላይ መሆኑን የተገነዘቡ ሴቶች፣ ተስፋቸውን ሰላማዊና ዴሞክሪያሲዊ ምርጫ ላይ ጥለዋል። ‹የሰላም መጉደልና ያልተረገጋ የፖለቲካ ሁኔታ የሚያስከተለውን ችግር በተግባር እያየነው ነው፡፡ ዴሞክራሲያዊ ስርአትን ማበረታታትና፣ ሰላማዊ የሥልጣን ሽግግር ምን ማለት እንደሆነ ለልጆቻችን በተግባር ማሳየት ይኖርብናል። ለሰዓታት የተሰለፍኩትና የመረጥኩትም ለዚሁ ነው።›› ያለችን የሦስት ልጆች እናትና የባንክ ሠራተኛ የሆነችው የአዲስ አባባ ነዋሪዋ ሰላማዊት ደረጄ ነች፡፡

የኢትዮጵያ የህግ ባለሞያ ሴቶች ማህበር ባወጣው ሪፖርት መሰረት፣ ሴቶች በከፍተኛ ቁጥር በታዩበት በ2013 ምርጫ በአንዳንድ ቦታዎች ጥቃትና የሴቶችን የመምረጥ መብት የሚያስተጓጉሉ ድርጊቶች ታይተዋል፡፡ ይህ ግን፣ ሴት መራጮችን እስከምሽቱ ሶስት ሰአት ደረስ በተደረገው ምርጫ ከመሰለፍና ከመምረጥ አላገዳቸውም፡፡

‹‹ሰልፉ ረጅም ስለነበርና ጣቢያውም በጊዜ ሥራ ስላልጀመረ ወደ ሥራዬ መመለስ ነበረበኝ። ሰዓቱ መራዘሙን ስሰማ ሱቄን በሰዓቱ ዘግቼ ለመምረጥ መጣሁ። ካርዴ ባለመባከኑ ደስ ብሎኛል። ውጤቱ ምንም ይሁን ምን ስርአት የምናከብርና በሕግና በዴሞክራሲ የምናምን ሰዎች መሆናችንን ለዓለም ለማሳየት ምርጫው ጥሩ አጋጣሚ ይመስለኛል።›› ያለችን ደግሞ የሀያ ሦስት ዓመቷ ወጣት የደሴ ከተማ ነዋሪዋ ሶፊያ አሕመድ ነች።

‹‹ማንበብም ሆነ መጻፍ አልችልም። እድሜዬን ያሳለፍኩት ልጆቼን በማስተማርና ቤተሰቤን በመንከባከብ ነው። ባለቤቴን በሞት ያጣሁት ልጆቻችን ገና ትንሽ ሳሉ ነበርና እነርሱን ከቁምነገር ለማድረስ ስባትል ለመማር ጊዜ አላገኘሁም ነበር። ያኔ ያሳስበኝ የነበረው አለመማሬ ሳይሆን የልጆቼ ነገር ነው። ዛሬ ልጆቼ ከቁምነገር ደርሰዋል፤ የልጅ ልጅም ዐይቻለሁ። አሁን ደግሞ የሚያሳስበኝ የአገር ሰላም ነው፤ የልጅ ልጆቼ በሰላም የሚኖሩባት አገር እንድትኖርላቸው እፈልጋለሁ። ባልማርም፣ በጣት አሻራዬም ቢሆን በመራጭነት ተሳትፌአለሁ። ለዛሬ ባይሆን ለነገ የአገር ሰላምና እንደሚባለው ለዴሞክራሲ የኔም ድምጽ ድርሻ እንዳለው ስለማምን ነው የመረጥኩት።››

ይህን ያሉት የአራት ልጆች እናትና የ57 ዓመቷ ባልቴት አሰለፈች ቦንሳ የምርጫ ካርድ ባወጡበት የምርጫ ጣቢያ ድምጻቸውን ለመስጠት ማልደው ነው የተሰለፉት። በነበሩበት የምርጫ ጣቢያ የተወሰኑ መስተጓጎሎች ተፈጥረው የምርጫ ሂደቱ ጥቂት ዘግይቶ በመጀመሩ አልሰለቹም፣ ቤታቸው ተመልሰው መድኃኒት ውጠው መመለስ ግድ ያላቸው ቢሆንም አላስመረራቸውም።

የሚመርጡትን እጩ ግለሰብ እንዲሁም ፓርቲ ለመለየት አልተቸገሩም ወይ ብለን ጠይቀናቸዋል። ‹‹ፎቶ ተለጥፎ ዐይቻለሁ። ቀድሞ በቅስቀሳ የተወሰኑትን አውቅ ስለነበር የምመርጠውን ለመለየት አልተቸገርኩም። ልንመርጥ ስንገባም ገለጻ ተደርጎልን ነበርና ተረድቻለሁ።›› ይላሉ፤ አሰለፈች።

እንደ እርሳቸው መጻፍም ሆነ ማንበብ የማይችሉ፣ ነገር ግን ምስሎችን እና የምርጫ ምልክቶችን በማየት የመረጡ የሚያውቋቸው ሰዎች እንዳሉ ጠቅሰዋል። ‹‹አለመማሬ ከመምረጥ አልከለከለኝም። መጻፍና ማንበብ ባልችልም በአገሬ ጉዳይ ላይ እንድሳተፍ እድል እስከተሰጠኝ ድረስ የማልጠቀምበት ምክንያት የለም። መሃይም ናት አታውቅም ቢሉኝ ግድ የለኝም። ለዛም ብዬ አልሸሽም።›› ሲሉም ደፈር ብለው ይናገራሉ።

እንደ አሰለፈች ዓይነት ማንበብም ሆነ መጻፍ የማይችሉ ነገር ግን ከምርጫ ቦታ ድምጻቸውን ለመስጠት የተገኙ እናቶች ጥቂት አይደሉም። አንዳንድ ጣቢያዎች ላይ በዚህ ምክንያት ዘርዝሮ ለማስረዳት ከጊዜ አንጻርም ሆነ ለምርጫ ተዓማኒነት ፈታኝ በመሆኑ፣ የተቸገሩም አልጠፉ። እንዲያም ሆኖ ግን ብዙዎቹ በትጋትና የድምጻቸውን ዋጋ በማመን በመራጭነት ተሳትፈዋል።

በምርጫ ክልሉ በታዛቢነት ከተሳተፉ መካከል ሥማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ አንድ ግለሰብ በጉዳዩ ላይ ሐሳብ አካፍለዋል። በተለይም የሴቶችን ተሳትፎ በመጥቀስ፣ ‹‹መጻፍም ሆነ ማንበብን ተቸግረው ካየናቸው ውስጥ ሴቶች ይበዛሉ። እነርሱም ግን ከመጠየቅ ወደኋላ አላሉም። ድምጻቸው እንዳይባክንም ተጠንቅቀው ሲጠይቁ ዐይቻለሁ።›› ሲሉ አብራርተዋል። አያይዘውም ‹‹ይህ ዛሬ ላይ ላይታወቀን ይችላል። ስርዓቱን በዚህ ማስቀጠል ከተቻለ ግን በቀጣዩ አገራዊ ምርጫ ጉልህ ለውጦችን እናያለን፣ ተጨባጭ የፖለቲካ ውጤትም እንመለከታለን፣ የሴቶች ተሳትፎም ከዚህ የላቀ ይሆናል ብዬ አምናለሁ።›› ብለዋል።


ቅጽ 3 ቁጥር 139 ሠኔ 26 2013

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com