የእለት ዜና

የጾታ እኩልነትና ተሳትፎ ለዲሞክራሲ ግንባታ

ኢምፓቲ ፎር ላይፍ ኢነተግሬትድ ዴቨሎፕመንት አሶሴሽን(ኤሊዳ) የተቀናጀ የልማት ሥራን በመሥራት ሴቶችን፣ ልጃገረዶችን፣ ወጣቶችን እና ህጻናትን በትምህርት፣ በጤና እና በኢኮኖሚ በመደገፍ እንድሁም በዴሞክራሲ ባህል ግንባታ እና ዘላቂ ሰላም ላይ የሚሠራ እና ማኅበራዊ ኀላፊነታቸውን የሚወጡ ፣ ምርታማ እና አርቆ አሳቢ ዜጎችን ለማፍራት በማለም 2008 (እ.ኤ.አ)ሴቶች የተመሠረተ አገር በቀል የሲቪክ ማኅበረሰብ ድርጅት ነው፡፡

በዚህ ገፅ ላይ የተካተቱ የተለያዩ አካላት ሐሳቦች የኤሊዳንም ሆነ የድጋፍ ሰጪ ድርጂቱን አቋም ላያንጸባርቁ ይችላሉ፡፡

ዓለም ከተስማማባቸው ነገር ግን ተፈጻሚነት ላይ ካዘገመባቸው ጉዳዮች መካከል አንዱ በፖለቲካ ተሳትፎ እና የውሳኔ ሰጪነት ሚና ውስጥ የጾታ እኩልነት አንዱ ነው። እንደሚታወቀውም ጥቂት ለማይባሉ ዓመታት፣ የሴቶችና የወንዶች እኩል የፖለቲካ ተሳትፎን በሚመለከት ብዙ ትግሎች ተደርገዋል። ትግሎቹ ‹ሴቶች ይምረጡ› ከሚል ተነስተው የመመረጥ መብት እንዲኖራቸው መጠየቅ ላይ የጨረሱ ናቸው።
በአለም ዙሪያ ይህ መብት እየYተረጋገጠ ቢመጣም፣ አሁንም ብዙ የሚቀሩ ሥራዎች መኖራቸው ግልጽ ነው።

የተባበሩት መንግሥታት የልማት ፕሮግራም (UNDP) በድረ ገጹ ባስነበበው አንድ ጽሑፍ፤ ‹ይህ ጉዳይ በ21ኛው መቶ ክፍለ ዘመንም ለምን አጀንዳ ሆነ?› ሲል የሂደቱን አዝጋሚነት ይጠይቃል። በዚህም ላይ አስተያየቱን በማከል ዓለም ሴቶችን ትታ በግማሽ (ከግማሽ በታች) በሆነ ሕዝብ ለውጥ እንደማታመጣ ጠቅሶ ሴቶች አሁንም በውሳኔ ሰጪነት ሳይደርሱ የዳር ተመልካች ሆነው መታየታቸውን ይኮንናል። አሁንም በፖለቲካ የመምረጥና የመመረጥ ሂደት ውስጥ ለመሳተፍ መዋቅራዊ፣ ማኅበረ ኢኮኖሚያዊ፣ ተቋማዊና ባህላዊ መሰናክሎች አሉባቸው ሲል ይጠቅሳል።

በሂደት ውስጥ ግን በኢትዮጵያም ጭምር የታዩ የሴቶች በፖለቲካ የመምረጥና የመመረጥ ተሳትፎዎች ይበል የሚያሰኙ ናቸው። ምንም እንኳ ብዙ ቀሪ የቤት ሥራዎች እንዳሉ ግለጽ ቢሆንም፣ አሁንም የፖለቲካ ፓርቲዎች ሴቶችን በማሳተፍ ረገድ ‹ወገቤን!› ሲሉ ቢስተዋልም፤ ለውጦች ግን አሉ።

ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ 6ኛው አገራዊ ምርጫ ዋዜማ በቅድመ ምርጫ ሂደቱ ላይ ፓርቲዎች ሴቶችን በተመራጭነት እንዲያሳትፉ ሲል ከመጠየቅ አልፎ እንደውም ማበረታቻ እንደሚሰጥ ሲገለጽ ተስተውሏል። አንድ የፖለቲካ ፓርቲ መሪውን ሴት ያደረገ ሲሆን በቀረው ውስን ቁጥር ያላቸው ተመራጮችን ያካተቱ ፓርቲዎች ታይተዋል። ጨርሶም ይህ ነው የሚባል ድረሻ ላይ ሴቶችን ያላስቀመጡም ነበሩ።

በዚህ ወቅትም ‹‹የኢትዮጵያ ፖለቲካና ምርጫ እንኳን ለእናንተ ለሴቶቹ ለእኛም ለወንዶቹ ከብዷል።›› የሚሉ ጥቂት አልነበሩም። ይህንንም የተለያዩ ሲቪክ ማኅበራት ሲኮንኑና ሲወቅሱ፣ የሴቶች ተሳትፎ እንዲጨምር ሲገፋፉና ድምጽ ሲያሰሙም ተስተውሏል።

አሁን ላይ በጠቅላላው የምርጫ ሂደት እንዲሁም ውጤት የሴቶች ተሳትፎ እንዴት ነበርና ውጤታቸውስ እንዴት ሆነ የሚለው፣ የዘገባዎችን መጠናቀር የሚፈልግ ጉዳይ ነው። በቀጥይ 7ኛው አገራዊ ምርጫ ከአሁን የተሻለና የበረታ የሴቶችን ተሳትፎ እውን ለማድረግ ከወዲሁ የሚጠበቁ ሥራዎች እንዳሉ ግልጽ ነው።

ይልቁንም ኃላፊነት የተረከቡ፣ ወንበር ያገኙና ባለሥልጣን የሆኑ ሴቶች ትልቅ ኃላፊነት አለባቸው። የተባበሩት መንግሥታት የልማት ፕሮግራምም የሴቶች ወደ ሥልጣን መቅረብና በተለያዩ መንግሥታዊ ቢሮዎች ውስጥ በኃላፊነት መገኘት፣ ሌሎችን ሴቶችም እየቀሰቀሰ ነው ሲል ይፋ ማድረጉ ይታወሳል።

በአገራችን ከኹለትና ሦስት ዓመታት በፊት ሴት ካቢኔ አባላት ብዛት ከወንዶች ጋር ተመጣጣኝ ቁጥር እንደነበረው ይታወሳል። ሴት ሚኒስትሮች፣ አመራርና ውሳኔ ሰጪዎችንም በርከት ብለው ተመልክተናል። ይህን ዓይነት እድገትና ለውጥ በዓለማቀፍ ደረጃም እንደታየ የተባበሩት መንግሥታት ሴቶች ጉዳይ ‹ዩኤን ውመን› ያወጣው መረጃ ያመላክታል።

ድርጅቱ ሴቶች በፖለቲካና በአመራር ያላቸውን ተሳትፎ በሚመለከት ባወጣው የቁጥር መረጃ መሠረት፣ በፓርላማ ውስጥ ያለው የሴቶች ተሳትፎ በዓለማቀፍ ደረጃ በ1995 ከነበረው አንጻር 11.3 በመቶ አድጎ በ2019 በሁሉም ፓርላማዎች የሴቶች ተሳትፎ 24.3 በመቶ ደርሷል። እስከ 2019 ማብቂያ ድረስም በዓለማቀፍ ደረጃ 11 ሴቶች ፕሬዝዳንት፣ 12 ሴቶች ደግሞ ጠቅላይ ሚኒስትር ነበሩ።

በፓርላማ አባልነት ብዙ ሴቶችን በማካተት አፍሪካዊቷ ሩዋንዳ ከዓለም አገራት ሁሉ ቀዳሚ ናት። ለዚህም ያበቃት 61.3 በመቶ የፓርላማ ወንበር የያዙት ሴቶች በመሆናቸው ነው። በአንጻሩ አንድም እንኳ ሴቶችን ያላሳተፉ ፓርላማዎች ደግሞ አሉ።

በሚኒስቴርነት ደረጃ ሴቶች የሚሾሙባቸው ኃላፊነቶች መካከል በዋናነት አምስት ዘርፎች ይጠቀሳሉ። አንደኛው ማኅበራዊ ጉዳይ ነው። ቀጥሎ እንደ ቅደም ተከተላቸው የቤተሰብ (የሕጻናት፣ የወጣቶች፣ የአካል ጉዳተኞችና አዛውንቶች) ጉዳይ፣ የተፈጥሮ ጉዳይ፣ የሥራ ፈጠራ እንዲሁም ንግድና ኢንዱስትሪ ናቸው።

በዚሁ የተባበሩት መንግሥታት መረጃ መሠረት እስከ 2019 አጋማሽ ድረስ ከ50 በመቶ በላይ ሴቶችን በፓርላማ ውስጥ የሚያሳትፉ አገራት ሦስት ብቻ ነበሩ። እነዚህም ከሩዋንዳ ቀጥሎ ኩባ እና ቦሊቪያ ናቸው።


ቅጽ 3 ቁጥር 140 ሐምሌ 4 2013

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com