የእለት ዜና

ወጣቶች ላይ ያተኮረው የሠላም ውይይት

የሠላምና ልማት ማዕከል ለትርፍ ያልተቋቋም፣ መንግሥታዊ ያልሆነ አገር በቀል ድርጅት ሲሆን፣ ከማንኛውም የፖለቲካም ሆነ የሌላ ወገንተኝነት የጸዳ፣ በአገሪቱ የሠላም ባህል እንዲስፋፋ፣ በውይይት እና በንግግር የሚያምን ማሕበረሰብን ለመፍጠር የሚሰራ ተቋም ነው።
ተቋሙ ከተመሰረተበት 1982 ዓ/ም አነስቶ በተለያዩ የሠላም ግንባታ ሥራዎች ላይ ተሰማርቶ በመንቀሳቀስ ላይ ይገኛል። በተለይም ደግሞ ግጭትን ለመፍታት እና የሠላም ባህልን ለመገንባት የሚያስችሉ አገር በቀል እውቀቶችን በማዳበር በተለያዩ አካባቢዎች የሚከሰቱ አለመግባባቶች በውይይት እንዲፈቱ ሲያደርግ ቆይቷል። በተለይም ደግሞ በቦታ እና በሁኔታ አለመመቸት ምክንያት ለብዙ ተቋማት ለመድረስ አመቺ አይደሉም የሚባሉ የአገራችን አካባቢዎች ጭምር ሳይቀር በመግባት ከታችኛው የማሕበረሰብ አደረጃጀቶች ጋር ሰፊ የሠላም ግንባታ ሥራዎችን በማከናወን ላይ ይገኛል። ተቋሙም በተሰማራበት የሥራ ዘርፍ ምንም እንኳ እንደአገር ያለብን ችግር ዘርፈ ብዙ እና ሰፊ ቢሆንም የአቅሙን በማበርከት ላይ ከመሆኑም በላይ አመርቂ የሚባሉ ውጤቶችን በማስመዝገብ ላይ ይገኛል። ተቋሙም አሁን ያሉ ፕሮጅክቶችን በማስፋት እና ወደተጨማሪ ቦታዎች በመንቀሳቀስ፣ እንዲሁም የተለያዩ ማሕረሰብ አቀፍ የሆኑ የሰላም ጥረቶችን በመደገፍ እንዲሁም አቅማቸውን ጭምር በመገንባት ለችግሮች ተመጣጣኝ የሆነ ምላሽ ለመስጠት የበኩሉን አስተዋፅኦ በማበርከት የሚቀጥል ይሆናል።
ሠላምና ልማት ማዕከል

በኢትዮጵያ ባለፉት አራት አመታት ውስጥ ከተከሰቱ ግጭቶች መካከል በአዲስ አበባ ከተማ በኮልፌ ቀራኒዮ ወረዳ 10 ወጣቶችና በቡራዩ ከተማ ወጣቶች መካከል የዛሬ 3 አመት ገደማ የተከሰተው አንዱ ነው። ለውጥ መጣ ተብሎ በርካታ እስረኞች በተፈቱበት፣ እንዲሁም የተሰደዱት የፖለቲካ ፓርቲዋችና መሪዎቻቸው ከውጭ አገራት በሚገቡበት ወቅት አቀባበል የተደረገበት ሂደት ነበር ወጣቶቹን ለግጭት የዳረገው። ለበርካቶች ጉዳት ምክንያት የነበረው የእርስበርሱ ግጭት ለብዙዎችም መታሰር ምክንያት ሆኖም ነበር።

ለግጭቱ መነሻው ይህ ነው እየተባለ የተለያየ ምክንያት ሲሰጥ ቢቆይም፣ የተለያዩ ኃይማኖታዊና ባህላዊ በዓላት ሲከበሩ ችግሮቹ እያገረሹ ጸቡ አስቸጋሪ ሁኔታ ላይ ደርሶ ነበር። የነበረውን የቅራኔ መንፈስ ለመቀየርና በመካከላቸው የሠላምና አብሮ በፍቅር የመኖር ውይይት እንዲደረግ ጥረት ካደረጉት አካላት መካከል ሠላምና ልማት ማዕከል በግንባር ቀደምትነት ይጠቀሳል። የውይይቱ ዋና ዓላማ በአዲስ አበባ ኮልፌ ቀራንዬ ክፋለ ከተማ እና በአጐራባቹ ኦሮሚያ ልዩ ዞን ቡራዩ በሚኖሩ ወጣቶች መካከል ተፈጥሮ የነበረው ግጭት እንዳይደገም፣ ለወደፊቱም እርስበርሳቸው ከመጋጨት ይልቅ ችግሮችን ተቀራርበው እንዲፈቱ ብሎም እኛና እነሱ የሚል አስተሳሰብን እንዲያስቀሩ ለማድረግ ታስቦ ነበር።

በኮልፌ ወረዳ 10 እና የቡራዩ ወጣቶች ዘንድ የሠላም ግንባታ ጥረቱ ከመጀመሩ በፊት የሚመለከታቸው የመንግሥት አካላት እንዲያውቁት ስለጉዳዩ በማነጋገር ለስኬቱ ድጋፍ እንዲያደርጉ እና በሂደቱም እንዲሳተፉ ተደርጓል። በኹለቱ አካባቢዎች በኮልፌና በቡራዩ የሚገኙ ወጣቶችን በቀጥታ ለማገናኘት ከመሞከሩ በፊት ማዕከሉ ከዚህ በፊት በተመሳሳይ ሁኔታዎች ውስጥ ያገኛቸውን ልምዶች በመጠቀም ዝግጅቱን አጠናቆ ወደ ማቀራረብ ሂደቱ ገብቷል። በኹለቱ አካባቢ ነዋሪ ወጣቶች መካካል ያለውን ውሱን አለመግባባት ለመቅረፍ እና ችግሮቻቸውን በዘላቂነት በውይይት እና በመቀራረብ መንፈስ እንዲፈቱ ለማስቻል የውይይት መድረኮችን በማሰናዳት ወጣቶቹ ተቀራርበው እንዲወያዩ ተደርጓል።

በኹለቱም አካባቢዎች የተዘጋጁት መድረኮች ላይ ተፅዕኖ ፈጣሪ ናቸው የተባሉ 40 (አርባ) ወጣቶች በየፊናቸው በመካከላቸው የልዩነት መንስኤ ናቸው ባሏቸው ጉዳች ላይ ዝርዝር ውይይት አድርገው ከተነሱ ዝርዝር ምክንያቶች ውስጥ በየፊናቸው አምስት አምስት የልዩነት መንስኤዎች አንጥረው በማውጣት ለጋራ ውይይት አሰናድተዋል። በእነዚህ ሂደቶች እንደታዛቢ ሂደቱን ከመምራት ውጭ የሠላምና ልማት ማዕከል ተሳታፊ ያልነበር ሲሆን፣ እስከመጨረሻውም በዚሁ መልክ መድረኩን በማመቻቸት፣ ውይይትን የመምራት ክህሎት (Dialogue Facilitation Skills) ስልጠና በማዕከሉ አማካይነት የወሰዱ ወጣቶች እንዲመሩት ተደርጓል። ከዚህ ቀደም በሌሎች የማዕከሉ ተግባራት ላይ ተሳታፊ የነበሩ የአካባቢ ወጣቶች ተመልምለው ስልጠና የወሰዱ ሲሆን፤ በስልጠናው መሰረትም ለግጭት የማይዳርግ፣ ስርአቱን የጠበቀ አካሄድ እንዲከተሉ ለማድረግ ተችሏል። በሂደቱም ከኹለቱም አካባቢ በወጣቶች እና ጸጥታ ዙሪያ ሥራዎችን የሚያከናውኑ መንግሥታዊ ተቋማት ተወካዮች ተገኝተው እንዲታዘቡ እና በመንግሥት በኩል መወሰድ ያለባቸውን የእርምት እርምጃዎች በአግባቡ እንዲያጤኑ እድል ተፈጥሮላቸዋል።

ማዕከሉ በያዝነው ሐምሌ 2013 ዓ.ም. ሊያከናውን ካቀዳቸው ስድስት የወጣቶች ማሕበረሰብ የተናጠል እና የጋራ ውይይቶች ውስጥ ሁሉንም በተሳካ ሁኔታ ያከናወነ ሲሆን፣ በመድረኩም በወጣቶች መካከል መልካም ሊባሉ የሚችሉ ውጤቶች ተገኝተዋል። በመድረኮቹም ላይ ወጣቶች የየአካባቢያቸውን ወጣቶች በመወከል በሃቅ ላይ የተመሰረተ እና ከማንም ወገን ጣልቃ ገብነት ነጻ የሆነ ውይይት እንዲያደርጉ ሆኗል። በተለይም ደግሞ በዋነኝት ከኹለቱ አካባቢ ወጣቶች የሚመነጩና ወጣቶቹ በራሳቸው መፍትሔ ሊያገኙላቸው የሚችሉ ችግሮች ላይ አተኩረው እንዲወያዩ ከመድረኩ በተሰጠው አቅጣጫ መሰረት ወጣቶች የሞሏቸውን ዝርዝር ችግሮች አውጥተው ተወያይተዋል። በመጨረሻም የኹለቱ አካባቢ ወጣቶች በየፊናቸው ባደረጉት ውይይት ማብቂያ ላይ በሙሉ ቀን ውይይት ለይተው ካስቀመጧቸው ሐሳቦች ከእያንዳንዱ ውይይት አምስት አምስት ነጥቦች ተለይተው ለጋራ ውይይት እንዲቀርቡ ተደርጓል። በየአካባቢው በተደረጉ የተናጠል ውይይቶች ላይ ተሳታፊ ከነበሩ 40 ተሳታፊዎች ውስጥ 15ቱ በተሳታፊዎች እና በመድረኩ አወያይ ወጣቶች አማካይነት ተለይተው አካባቢያቸውን በቀጣይ የጋራ መድረክ እንዲወክሉ ተደርገዋል። በዚህም መሰረት የጋራ የውይይት መድረኮቹ በድምሩ 30 ወጣቶች የተሳተፉባቸው ሲሆን፣ በኹለቱም በኩል በየአካባቢያቸው በተደረጉ የተናጠል ውይይቶች ላይ የተነሱ ሃሳቦች ቀርበው በጋራ ውይይት ተደርጎባቸዋል።

ወጣቶቹ በጋራ መድረካቸው ላይ በቀጥታ ወደ ውይይቱ ቢገቡ በመካከላቸው ያለው የውጥረት ስሜት ወደ መካረር ገብቶ ችግሮችን ከመፍታት ይልቅ ችግሮችን የማባባስ ውጤት ሊያስከትል ስለሚችል በቅድሚያ መተማመናቸውን ለመጨመር የሚያስችል እና ኅብረታቸውን ሊያጠነክር የሚችል የተለያዩ እንቅስቃሴዎችን ማድረግ አስፈላጊ ነበር። ስለሆነም በሠላም እና ልማት ማዕከል ባለሙያዎች በኩል የተዘጋጁ እንቅስቃሴ እና ጨዋታዎች በጋራ እንዲያከናውኑ በማድረግ የውይይት መድረኩ ከመጀመሩ አስቀድሞ በተወያይ ወገኖች መካከል መልካም የትውውቅ እና የመግባባት መንፈስ እንዲፈጠር ለማድረግ ተችሏል። ተወያይ ወገኖችም በመካከላቸው ቀለል ያለ እና ለውይይት የሚጋብዝ አብሮነት የተፈጠረ ስለመሆኑ በአንደበታቸው መስክረዋል። ብዙዎቹም ወደውይይቱ ሲመጡ የነበራቸው የውጥረት መንፈስ እንደለቀቃቸው እና እንቅስቃሴው ለመወያየት የሚያስችል ጥሩ መንፈስ እንደፈጠረላቸው ተናግረዋል። በተለይም ደግሞ ለጨዋታው ተብለው የተፈጠሩት ሦስት ቡድኖች በእያንዳንዳቸው ውስጥ ከኹለቱም አካባቢ የመጡ ወጣቶች የተካተቱበት በመሆኑ እና ወጣቶቹም ከመጡበት አካባቢ ከመጡ ወጣቶች ይልቅ ለተመደቡበት ቡድን የተሻለ ወገንተኝነት እንዲኖራቸው የሚያደርግ ጨዋታ በመሆኑ በፉክክር ስሜት ውስጥ ሆነው አዲስ ከተዋወቋቸው ወጣቶች ጋር የተሻለ ለመቀራረብ ዕድል ፈጥሮላቸዋል። በሂደቱም ሰዎች በብሔር፣ በኃይማኖት አልያም በሌላ እየተቧደኑ ከመለያየት እና ከመጋጨት በላይ ለአንድ ዓላማ በኅብረት ቢቆሙ ምን ያክል ውጤታማ ለመሆን እንደሚችሉ ተገንዝበዋል።

በውይይት ላይ ለመሳተፍ ከኹለቱ አካባቢ የመጡ ወጣቶች አስተማሪ ያሏቸውን ታሪኮችና ምሳሌዎች በማቅረብ የተፈጠረውን መልካም የውይይት መንፈስ በተሻለ መልኩ ለማጠናከር ችለዋል። በሂደቱም ላይ በኹለቱም ጎራ ጸብ አጫሪዎች እንደነበሩ ያመኑት ተሳታፊዎች፣ ይሁንና ወጣቱ ለኹሉም ጥፋት ተጠያቂ መሆኑ ተገቢ አይደለም ብለዋል። በተለይም ደግሞ በአንድ አንድ ሁኔታዎች ትልልቅ ሰዎች በፈጸሟቸው ጥፋቶች ሳይቀር ወጣቶችን እንደ ጥፋተኛ የመቁጠር አዝማሚያ ተገቢ አለመሆኑ በመድረኩ ተነስቷል። በውይይት ሂደቱም የሠላምና ልማት ማዕከል ባለሙያዎች እና የፕሮግራም ኃላፊዎች ጣልቃ እየገቡ አንዳንድ ሐሳቦችን እና ማስተካከያዎችን እንዳስፈላጊነቱ ይሰጡ ነበር።

የቡራዩና ኮልፌ ወጣት ተወካዮች የተመረጡትን አምስት ነጥቦች በመድረኩ ላይ ካቀረቡ በኃላ በኹለቱም ወገኖች ውይይት ከመደረጉም በላይ ፣በተመረጡ ሦስት ነጥቦች ላይ በሠላምና በፍቅር ለመኖር እንድንችል ምን እናድርግ የሚል የመፍትሔ ሐሳብ ላይ ምክክር እንዲያደርጉ ተደርጓል። ምንም እንኳ ችግሩን እንደችግር ማንሳቱ ለውይይት የሚጋብዝ እና መልካም ቢሆንም፣ በችግሮቹ ላይ ተወያቶ መፍትሔ ላይ መድረስ ካልተቻለ ችግሩን ጭሮ ከማባባስ የሚለይ ስላልሆነ ወጣቶቹ ባወያዮቻቸው በኩል ስለመፍትሔው ጭምር እንዲነጋገሩ እድል ተመቻችቶላቸዋል።

በቡራዩም ሆነ አዲስ አበባ፣ ከየትኛውም አካባቢ የመጣ የየትኛውም ብሔር ተወላጅና የኹሉም ኃይማኖት ተከታይ የሚኖሩበት እንደመሆኑ፣ የተፈጠረው አይነት ክስተት መሆን እንዳልነበረበት ተነግሯል። አርቆ ባለማሰብና ግለቱን ተከትለው ግጭቱ ላይ ተሳታፊ የነበሩ ሳያውቁ ላደረጉትም ሆነ ተገፋፍተው ስለፈጸሙት ተግባር ይቅርታ ሊደረግላቸው እንደሚገባም መተማመን ላይ ተደርሷል። በተወሰኑ ሁኔታዎች በተለይም ደግሞ የኹለቱንም ወገን የወጣት ተወካዮች ወደስሜት ሊገፋፉ የሚችሉ ችግሮች ሲፈጠሩ በምክንያታዊነት ለመወያየት በተቸገሩባቸው አጋጣሚዎች የውይይቱ መንፈስ እንዳይረበሽ በማሰብ አወያዮች ተሳታፊዎችን በአነስተኛ ቡድን በመቀናነስ ውይይት አድርገው በልዩነት ሐሳቡ ላይ ስምምነት ላይ ደርሰው እንዲመጡ ሲያደርጉም ታይተዋል።

ወጣቶቹ ለየብቻቸው ያለማንም ታዛቢ እንደልባቸው ሳይፈሩ እና ሳይሸማቀቁ እንዲነጋገሩ ከተደረገ በኋላ የመዝጊያው ውይይት ተካሂዷል። ሌላውን ወገን ያስቀየመ ተግባር እንዲቆም፣ ራሳቸው በግላቸው ከጥላቻና ካልተገባ ድርጊት እንደሚያርቁና ሌላውንም ለመቀየር እንደሚሰሩ ቃል የገቡት ተሳታፊዎቹ፣ መግባባት ላይ ለመድረስ ጊዜ አልፈጀባቸውም ነበር። ከተነሱት ነጥቦች መካከል የተወሰኑት ሆን ተብለው ለማስቀየም የማይፈጸሙ እንደሆኑ በቀላሉ መግባባት ላይ የተደረሰ ሲሆን፣ የተወሰኑት ደግሞ የመንግሥት አካላት የሚጠበቅባቸውን ሥራ ባለመሥራታቸው፣ እንዲሁም የተለያዩ የፖለቲካ ኃይሎች የራሳቸው እኩይ የፖለቲካ አመለካከት በወጣቱ ላይ በመጫናቸው የተፈጠሩ እንደሆኑ ታምኖበታል። የመንግስት ተወካዮች ማስተካከያ እንዲደረግ ስለተባሉ ጉዳዮች ትኩረት ሰጥተው እልባት እንዲበጅ ጥረት እንዲያደርጉ ሐሳብ ቀርቧል።

በአጠቃላይ፣ የኹለቱን አካባቢ ወጣቶች ለማቀራረብ 6 መድረኮች ተዘጋጅተው የነበረ ሲሆን፣ ችግር ብለው ካቀረቧቸው ጭብጦች በተጨማሪ ይበልጥ ሊያቀራርባቸው በሚችሉ ጉዳዮች ላይ ተወያይተዋል። በጋራና በተናጥል በመወያየት እርቅ ሊወርድ የሚችልበትንና ዳግመኛ ግጭት የማይፈጠርበትን ሁኔታ ለማመቻቸት ሠላምና ልማት ማዕከል ለወደፊቱም አብሮ እንደሚሰራ ተናግሯል። የማዕከሉ ሥራ በዚህ ብቻ የሚወሰን ባይሆንም፣ እንደ አንገብጋቢነቱ የቡራዩውና የኮልፌው ቅድሚያ እንደተሰጠው ማዕከሉ አሳውቋል። በመጨረሻም በውይይት ተሳታፊ የነበሩ ወጣቶች በተለያዩ የበጎ ፈቃድ መረሃ-ግብሮች ላይ ለመሳተፍ እንዲችሉ እና ሠላማቸውን በጋራ ለመጠበቅ ያስችላቸው ዘንድ ጥምር ኮሚቴ አዋቅረዋል።


ቅጽ 3 ቁጥር 141 ሐምሌ 10 2013

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com