የእለት ዜና

የምርጫ ቅስቀሳና ሴት ተመራጮች

ኢምፓቲ ፎር ላይፍ ኢነተግሬትድ ዴቨሎፕመንት አሶሴሽን(ኤሊዳ) የተቀናጀ የልማት ሥራን በመሥራት ሴቶችን፣ ልጃገረዶችን፣ ወጣቶችን እና ህጻናትን በትምህርት፣ በጤና እና በኢኮኖሚ በመደገፍ እንድሁም በዴሞክራሲ ባህል ግንባታ እና ዘላቂ ሰላም ላይ የሚሠራ እና ማኅበራዊ ኀላፊነታቸውን የሚወጡ ፣ ምርታማ እና አርቆ አሳቢ ዜጎችን ለማፍራት በማለም 2008 (እ.ኤ.አ)ሴቶች የተመሠረተ አገር በቀል የሲቪክ ማኅበረሰብ ድርጅት ነው፡፡

በዚህ ገፅ ላይ የተካተቱ የተለያዩ አካላት ሐሳቦች የኤሊዳንም ሆነ የድጋፍ ሰጪ ድርጂቱን አቋም ላያንጸባርቁ ይችላሉ፡፡

ከምርጫ ቅድመ ሂደቶች መካከል አንደኛው ነው፤ የምርጫ ቅስቀሳ ዘመቻ። የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ የፓርቲ እንዲሁም የግል እጩዎች ራሳቸውን የሚያስተዋውቁበት፣ የመራጩን ቀልብ እና ልቦና ለመግዛት የሚያደርጉት ተግባር ነው። የምርጫ ቅስቀሳ አማራጭ ፖሊሲዎችንና የመፍተሄ አቅርቦ መራጭን ለማመረክና የፖለቲካ ሀሳብን ለመሸጥ የሚደረግ ጠንካራ እንቅስቃሴ ሲሆን፤ ይህም የምርጫው ወሳኝ ክፍል መካከል አንደኛው ነው። በዲሞክራሲ ምህዳር ፖለቲከኞች ራሳቸውን ከሕዝብ የሚያስተዋውቁበትና ሊሠሩ ያቀዱትን የሚስረዱበት እድል በመሆኑ በምርጫ ሂደት ዋነኛ ክፍል እንደሆነ ይነገርለታል።

ለምርጫ ቅስቀሳ በቅድሚያ ቢያንስ ከአንድ ዓመት በፊት ሊሠሩ የሚገቡ ሥራዎች እንዳሉ ኢሕአፓ መሪ የሆኑት ቆንጂት ብርሃን ይናገራሉ። ቅስቀሳውም እንዲሁ በሐሳብ ታስቦ በቃል የሚፈጸም ሳይሆን፣ በጽሑፍ ሊሰፍርና በሚገባ ሊታቀድ የሚገባ እንደሆነ ሳያነሱ አልቀሩም። የምርጫ ቅስቀሳ ከፍተኛ የገንዘብ የጊዜና የጉልበት ወጪን የሚጠይቅ፣ የተደራጀና በእቅድ የሚመራ መሆን አለበት። ውጤታማ ለመሆንም ተሳታፊዎቹ ተናግሮ ማሳመንን ጨምሮ የተለያዩ ክህሎቶችን ያዳበሩ መሆን ይኖርባቸዋል። እንዲሁም ዘመናዊውን ማህበራዊ ሚዲያ ጨምሮ፣ የተለያዩ የመገናኛ ብዙሀንን በአግባቡ የመጠቀምን ልምድና ችሎታ ፖለቲከኞች ሊያተኩሩበት የሚገባ የዘመቻው አካል ነው።

በተለይም የሴት እጩዎች ቁጥር ጎላ ብሎ በታየበት የ2013 ምርጫ፣ የቅስቀሳ ዘመቻው ከሴቶች ተሳትፎ አንጻር ውጤትም ፈተናም የታየበት እንደነበር ተወዳዳሪዎች ይገልጻሉ። በ2013 በተካሄደው 6ኛው አገራዊ ምርጫ በኮቪድ 19 ምክንያት መራዘሙ የምርጫ ቅስቀሳ ዘመቻን በጥሩ ሁኔታ አቅዶ ለመከወን እንዳገዛቸው የሚናሩት የኢዜማዋ ካውሰር ኢድሪስ, ያም ሆኖ የተለያዩ ፈተናዎች እንደነበሩ አልሸሸጉም። በተለይም ከሴት ተመራጮች ጋር በተያያዘ ገና ለእጩነት ከሚቀርቡበት ጊዜ ጀምሮ እስከ ቅስቀሳ ሥራዎች ድረስ አስቸጋሪ ሁኔታዎችና አጋጣሚዎች ነበሩ ይላሉ።

በራስ መተማመን ያላቸው፣ ብቁ እና ንቁ የሆኑ ሴት ፖለቲከኞች ወይም ተመራጮችን ለማፍራትና ስኬታማ የምርጫ ቅስቀሳም ለማድረግ ከኮታ ይልቅ አቅም ያላቸውን ሴቶች ወደ ሥራ ማምጣት ላይ መሠራት አለበት ባይ ናቸው ካውሰር እንድሪስ። ይህም በሂደት የማኅበረሰቡን ዕይታ ስለሚለውጥ ሴቶችን በብዛትና በብቃት በፖለቲካው ላይ ለማሳተፍ ጥሩ መንገድ ነው ሲሉ ተናግረዋል።

ከ30 ዓመታት በላይ በፖለቲካው ውስጥ እንዲሁም በፖለቲካው ዙሪያ ተሳትፎ የነበራቸው ቆንጂት፣ በኢትዮጵያ ከውይይትና ምክክሮች ይልቅ በትንንሽ ጉዳዮች እሰጥ አገባ በብዛት ይስተዋላል ይላሉ። ፖለቲካውም ከአገር ጉዳይ ወጥቶ ግለሰብ ወይም ጥቂት ሰዎች ላይ ማተኮሩ፣ ከሐሳብ ይልቅ ሰዎች ላይ ትኩረት እንዲሰጥ አድርጓል። በዚህም የተነሳ የምርጫ ቅስቀሳ ፈታኝና አስቸጋሪ መሆኑ እንደማይቀር አውስተዋል። ይህ ደግሞ ካለው የማኅበረሰብ እሳቤና ዕይታ አንጻር በሴቶች ላይ የከፋ ጫና እንዳለው አስረድተዋል።

በእርግጥ የኢትዮጵያ የፖለቲካ ስርዓት አካሄድ በየዘመኑ አስቸጋሪና ፈታኝ እንደሆነ የሚናገሩ ጥቂት አይደሉም። ቆንጂት ብርሃንም በዚህ ሀሳብ ይስማማሉ። ይህም የጾታ ጉዳይ ሳይሆን ራሱ የፖለቲካ ስርዓቱ ያለበት ችግር መሆኑን ጠቅሰው፣ እንዲያም ሆኖ ጫናው በሴቶች ላይ ይበረታል ብለዋል።

ለዚህና ከላይ ለተጠቀሱት ሴቶች በምርጫ ቅስቀሳ ወቅት ለገጠማቸው እንዲሁም በጠቅላላው በምርጫ በመሳተፍ ሂደት ውስጥ ካሳለፉት ፈተና አንጻር፣ በቀጣይ ሊያስተካክለው ይችላል ያሉትን የመፍትሔ ሐሳብም አቅርበዋል። ይልቁንም ሴቶችን ከኢኮኖሚ ጥገኝነት ማውጣት፣ የሴቶችን ጨምሮ የማኅበረሰብን አመለካከት መለወጥና ማስተካከል፣ እንዲሁም ከምርጫው ቀደም ብሎ መዘጋጀትና መሥራት በዋናነት ትኩረት ያሻቸዋል ብለዋል።
በአንጻሩ ሴቶች ንቁ ተሳታፊ እንዲሆኑ ቅስቀሳ በሚደረግበት ጊዜ፣ ጥያቄው የሚቀርብላቸው ሴቶች ‹እንኳን እኛም ልንገባ፣ ፖለቲካው ውስጥ ለሉ ሴቶችም እናዝናለን!› የሚል ምላሽ ሰጥተዋል፤ ይሰጣሉ።

በምርጫ ቅስቀሳ ወቅት የሚተላለፈውን መልዕክት ትተው በሴት እጩዎች መልክና አቋም ዙሪያ ሐሳብ የሚሰጡም ጥቂት አልነበሩም። በተለይም በማኅበራዊ ድረ ገጾች በሚቀርቡ የሴቶች እጩዎች የምርጫ ቅስቀሳ ምስሎች ስር የሚሰጡ አስተያየቶች ለዚህ ማሳያ ሆነው የሚጠቀሱ ናቸው።

ግሩም ተሰማ የብልጽግና ፓርቲ ታዛቢ ሆነው በምርጫው ተሳትፎ አድርገዋል። የሴቶችን የምርጫ ቅስቀሳ በሚመለከት በቅርበት የታዘቡትንና በቅርብ የሰሙትን አካፍለውናል። ራሳቸው በመረጡበት የምርጫ ጣቢያና በአካባቢው ከገጠማቸው በመነሳት ሲያስረዱ፣ ሴቶች እጩዎች በቅስቀሳ ወቅት ረዳትና አድማቂ እንጂ እጩ ተወዳዳሪ የማይመስሏቸው ጥቂት እንዳልነበሩ መታዘባቸውን ጠቅሰዋል።

የምርጫ ቅስቀሳ አደባባይ ተወጥቶ በሕዝብ ፊት የሚደረግና በራስ መተማመንን የሚጠይቅ መሆኑን አንስተዋል። ‹‹ሴቶች ይህን አሟልተው በራስ መተማመን ይዘው ከበረቱ ይህኛው ምርጫ ትልቅ ትምህርት እንደሚሆንና በቀጣይ የተሻለ ለውጥ ለማምጣት ይረዳል›› ሲሉም ነው የተናገሩት።


ቅጽ 3 ቁጥር 141 ሐምሌ 10 2013

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com