የእለት ዜና

ምርጫን የታዘቡ ሴቶች

Views: 96

ኢምፓቲ ፎር ላይፍ ኢነተግሬትድ ዴቨሎፕመንት አሶሴሽን(ኤሊዳ) የተቀናጀ የልማት ሥራን በመሥራት ሴቶችን፣ ልጃገረዶችን፣ ወጣቶችን እና ህጻናትን በትምህርት፣ በጤና እና በኢኮኖሚ በመደገፍ እንድሁም በዴሞክራሲ ባህል ግንባታ እና ዘላቂ ሰላም ላይ የሚሠራ እና ማኅበራዊ ኀላፊነታቸውን የሚወጡ ፣ ምርታማ እና አርቆ አሳቢ ዜጎችን ለማፍራት በማለም 2008 (እ.ኤ.አ)ሴቶች የተመሠረተ አገር በቀል የሲቪክ ማኅበረሰብ ድርጅት ነው፡፡

በዚህ ገፅ ላይ የተካተቱ የተለያዩ አካላት ሐሳቦች የኤሊዳንም ሆነ የድጋፍ ሰጪ ድርጂቱን አቋም ላያንጸባርቁ ይችላሉ፡፡

6ኛው አገራዊ ምርጫ የሴቶች ተሳትፎ በብዛት የተስተዋለበት እንደሆነ ብዙዎቻችን መታዘብ የቻልነው እውነት ነው። ምንም እንኳ ይህ ይበቃል ወይም ‹በቂ ነው፣ የሴቶች የእኩል የፖለቲካ ተሳትፎ ጥረት ተሳክቷል› ለማለት የሚያስች ባይሆንም፣ እያንዳንዱ ወደፊት የሆነ እርምጃ ሊበረታታ እንደሚገባ እሙን ነው።

የቅድመ ምርጫ ሂደት ላይ የፖለቲካ ፓርቲዎች የሴቶችን ተሳትፎ እንዲያሳድጉ ለማድረግ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ጥረት ማድረጉ የቅርብ ትውስታ ነው። የፖለቲካ ፓርቲዎች በተወሰነ መጠንም ቢሆን እንኳ ሴቶችን እንዲያሳትፉ ግድ ለማለት የተደረገው ጥረት ባይሳካም፣ ሴቶችን በብዛት ተሳታፊ ለሚያደርጉ የተለየ ማበረታቻ እስከመስጠት ደርሷል።

በተጓዳኝ ግን በቦርዱ የሴት ባለሞያዎችና ሠራተኞች፣ በምርጫ ወቅት የተሳተፉ የሴት ታዛቢዎች እንዲሁም የሴት መራጮች ቁጥር ያንን ሁሉ ያካካሰው ይመስላል። ለአሁን ብቻ ሳይሆን በቀጣይ ምርጫ ቦርድን ጨምሮ የሲቪል ማኅበራት እና የፖለቲካ ፓርቲዎች ምን መሥራት እንዳለባቸው አቅጣጫ ጠቋሚ ነው። ከዛም በላይ ሴቶች ራሳቸው ተነሳሽነትን እንዲያሳዩ ይረዳል።

ዛሬ ጥቂት ስለ ታዛቢዎች ልናነሳ ነው። በምርጫ ወቅት ትልቅ ድርሻ እና ተሳትፎ ካደረጉት መካከል የምርጫ ታዛቢዎች ይጠቀሳሉ። በ6ኛው አገራዊ ምርጫ ደግሞ በዚህ የታዛቢነት ሥራ ላይ ሴቶች በብዛት ተሳትፈዋል።
መለስ ብለን መረጃዎችን እንቃኝ። ምርጫ ቦርድ ምርጫውን ለመታዘብ ፍላጎት ላላቸው የአገር ውስጥ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ፈቃድ ሊሰጥ መሆኑን ባስታወቀ ጊዜ አንድ መቶ ዐስራ አንድ ድርጅቶች ተመዝግበው ነበር። ከእነዚህም መካከል በተለያየ መስፈርትና አካሄድ 36 ድርጅቶች ምርጫውን እንዲታዘቡ ተመርጠዋል።

ከተመረጡ ታዛቢ ድርጅቶች መካከል ደግሞ 8ቱ በሴቶች ጉዳይ ላይ የሚሠሩ ሲቪክ ማኅበራት ናቸው። በዚህም መሠረት በጠቅላላው 134 ሺሕ 109 ታዛቢዎች ሲቀርቡ፣ ከዛም መካከል 61 ሺሕ 851 ማለትም 46 በመቶ ሴቶች ናቸው።
ይህ በቁጥርም ደረጃ ብቻ ቢሆን የታየ እንደሆነ ይበል የሚያሰኝ ደረጃ መሆኑ እሙን ነው። በተለይም ሴቶች እንዲህ ባለው መንገድ ወደ ፖለቲካ ተሳትፎ መቅረብና በሚቀጥሉት አገራዊ ምርጫ የሚኖራቸው ተሳትፎም እያደር እንደሚጨምር ማሳያ ሊሆን ይችላል። ምቹ በማይመስለውና ብዙ ምቹ ያልሆነ መልክ ባለው የኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ የመሳተፍ ተሳትፎ ሊዘራ ይችላል የሚል ዕይታም አለ።

በምርጫው ሂደትና ድኅረ ምርጫ የተለያዩ አስተያየቶች ይሰጡ የነበሩ የአገር ውስጥ እንዲሁም ዓለማቀፍ ተቋማትም ይህን የሴቶች ተሳትፎ ታዝበዋል። እንደ ማሳያ የምሥራቅ አፍሪካ ተጠባባቂ ኃይል ምርጫ ታዛቢ ልዑክ በምርቻ የነበረውን የጾታ ተዋጽኦ በመሚመለከት አስተያየት ሰጥቷል። በዛም መሠረት በድምጽ ሰጪዎች ዘንድ አጥጋቢ የሚባል የጾታ ተዋጽኦ ነበር ብሎ በመጥቀስ፣ ከምርጫ ጣቢያ አስፈጻሚዎች መካከል 34 በመቶ እንዲሁም ከአገር ውስጥ ታዛቢዎች 84 በመቶ ሴቶች መሆናቸውን አስታውቋል።

አስመረት ፈቃዱ ነዋሪነታቸው በአዲስ አበባ ቦሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 7 ነው። በ6ኛው አገራዊ ምርጫ በመራጭነትም በተሳተፉበት የምርጫ ጣቢያ በታዛቢነት ተሳትፎ ማድረጋቸውን ነግረውናል። በዛም ከነበሩ ታዛቢዎች መካከል በርከት ያሉት ሴቶች እንደነበሩ እንደሚያስታውሱ ጠቅሰዋል። ወጣቶች መኖራውንና እንደውም በእድሜ ገፋ ያሉት እናት እርሳቸው መሆናቸውን ጠቅሰዋል።

‹‹ከዚህ ቀደም በነበረውና በማስታውሰው ምርጫ በታዛቢነት መሳተፍ አይደለም ለመምረጥ እንኳ የመሄድ ፍላጎት አልነበረኝም።›› ሲሉ የሚያስታውሱት አስመረት፣ ዘንድሮ ግን በቅርበት የሚያውቋቸው ሰዎች ለታዛቢነት እንደሚሳተፉ ሲነግሯቸው ተነሳሽነትን እንዳገኙ ገልጸዋል።

ታድያ እንዴት ነበር ስንል ጠይቀናቸዋል። እርሳቸውም እንዲህ ሲሉ መለሱ፤ ‹‹ብዙ ሴት ይኖራል ብዬ አልጠበቅኩም። እኔም ስፈራ ስቸር ነው ፈቃደኛ የሆንኩት። የሆነውን ስመለከትና ብዙ ሴቶች ሳይ ግን፣ እድሜ ይስጠን እንጂ በቀጣዩ ምርጫም በታዛቢነትም ቢሆን መሳተፌ የሚቀር አይመስለኝም።›› በአስመረት ዕይታ መሠረት በዚህ አጋጣሚ ወጣት ሴቶች የበለጠ ተነሳሽነትን ሊያገኙ ይችላሉ።

በእርግጥ ይህ እውነት ሆኖ ወጤቱም በቀጣይ ምርጫዎች እውን ሆኖ ሊታይ ይችላል። በተጓዳኝ በምርጫው የሴቶች በብዛት በታዛቢነት መሳተፍ ለምርጫው ሰላማዊነት ያበረከተው አስተዋጽኦ ሊኖር እንደሚችል ብዙዎች ያምናሉ። በእርግጥ ጉዳዩ የተወሰነ ጥናት የሚያስፈልገው ቢሆንም፣ በድምሩ ግን የሴቶች ተሳትፎ መጨመሩ መልካም ውጤት እንደሆነ ግልጽ ነው።

ከምንም በላይ አስመረት እንዳሉት ምርጫው ሴቶች በበለጠ በፖለቲካው ለመሳተፍ ተነሳሽነትን ሊፈጥርባቸው የሚችል ነው። የግድ ምቹ የፖለቲካ ምህዳር መፈጠር ላይኖርበት ይችላል። እንደ ወንዶች ሁሉ ሴቶችም የፖለቲካ መረዳትና ብቃት መሠረት ባለው ኹኔታ ውስጥ ገብተው መታገል፣ አጋጣሚዎች ሲገኙም በመሳተፍ ለውጥን ማጽናት እንደሚችሉ አሳይቶ የሚያተጋቸው ነው።


ቅጽ 3 ቁጥር 142 ሐምሌ 17 2013

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com