የእለት ዜና

የዕርቀ ሠላም ጠቀሜታ በቡራዩ ወጣቶች አንደበት

የሠላምና ልማት ማዕከል ለትርፍ ያልተቋቋም፣ መንግሥታዊ ያልሆነ አገር በቀል ድርጅት ሲሆን፣ ከማንኛውም የፖለቲካም ሆነ የሌላ ወገንተኝነት የጸዳ፣ በአገሪቱ የሠላም ባህል እንዲስፋፋ፣ በውይይት እና በንግግር የሚያምን ማሕበረሰብን ለመፍጠር የሚሰራ ተቋም ነው።
ተቋሙ ከተመሰረተበት 1982 ዓ/ም አነስቶ በተለያዩ የሠላም ግንባታ ሥራዎች ላይ ተሰማርቶ በመንቀሳቀስ ላይ ይገኛል። በተለይም ደግሞ ግጭትን ለመፍታት እና የሠላም ባህልን ለመገንባት የሚያስችሉ አገር በቀል እውቀቶችን በማዳበር በተለያዩ አካባቢዎች የሚከሰቱ አለመግባባቶች በውይይት እንዲፈቱ ሲያደርግ ቆይቷል። በተለይም ደግሞ በቦታ እና በሁኔታ አለመመቸት ምክንያት ለብዙ ተቋማት ለመድረስ አመቺ አይደሉም የሚባሉ የአገራችን አካባቢዎች ጭምር ሳይቀር በመግባት ከታችኛው የማሕበረሰብ አደረጃጀቶች ጋር ሰፊ የሠላም ግንባታ ሥራዎችን በማከናወን ላይ ይገኛል። ተቋሙም በተሰማራበት የሥራ ዘርፍ ምንም እንኳ እንደአገር ያለብን ችግር ዘርፈ ብዙ እና ሰፊ ቢሆንም የአቅሙን በማበርከት ላይ ከመሆኑም በላይ አመርቂ የሚባሉ ውጤቶችን በማስመዝገብ ላይ ይገኛል። ተቋሙም አሁን ያሉ ፕሮጅክቶችን በማስፋት እና ወደተጨማሪ ቦታዎች በመንቀሳቀስ፣ እንዲሁም የተለያዩ ማሕረሰብ አቀፍ የሆኑ የሰላም ጥረቶችን በመደገፍ እንዲሁም አቅማቸውን ጭምር በመገንባት ለችግሮች ተመጣጣኝ የሆነ ምላሽ ለመስጠት የበኩሉን አስተዋፅኦ በማበርከት የሚቀጥል ይሆናል።
ሠላምና ልማት ማዕከል

በ 2010 ዓ.ም. በአገሪቱ የመጣውን የፖለቲካ ለውጥ ተከትሎ የቡራዩና የአዲስ አበባ ወጣቶች ጎራ ለይተው ባለመግባባት ውስጥ መቆየታቸው የሚታወቅ ነው። በተለይም ደግሞ አለመግባባቱ በቡራዩ እና ኮልፌ አካባቢ ባሉ ወጣቶች ዘንድ በአንጻራዊነት ጠንከር ያለ እንደሆነ በተለያዩ አጋጣሚዎች በተፈጠሩ ግጭቶች ታይቷል። አካባቢን መሰረት ያደረገው ቁርሾ እልባት ሳያገኝ በመቆየቱ በኹለቱ ተጎራባች አካባቢዎች የሚኖሩ ወጣቶች ለተለያ ጉዳቶች ተዳርገው ነበር። ጸቡ የበርካቶች ሕይወት እንዲጠፋ፣ ብዙዎች ለእስር እንዲዳረጉና ግምቱ ያልታወቀ ንብረት እንዲወድም፣ እንዲሁም ጥቂት የማይባሉም ከተደላደለ ኑሯቸው እንዲፈናቀሉ ምክንያት ሆኖ ነበር።

በኹለቱ ከተሞች የሚኖሩ ወጣቶች እንደባላንጣ መተያየታቸውን እንዲያቆሙ በመካከላቸውም እርቀ ሠላም እንዲወርድ ከጣሩትና ውጤታማ ሥራን ከሠሩት አካላት የሠላም እና ልማት ማዕከል ትልቁን ድርሻ እንደሚወስድ በሂደቱ የተጠቀሙ ወጣቶች ይናገራሉ። ማዕከሉ ባዘጋጃቸው በርካታ የውይይት መድረኮች ላይ ተካፍለው እርቀ ሠላሙ ውጤታማ እንዲሆን አስቀዋፅኦ ካደረጉ እና እራሳቸውም ተጠቃሚ ከሆኑ ወጣቶች መካከል ለዛሬ የቡራዩ ወጣቶች ስለሂደቱ ያካፈሉንን አስተያየት እናስቀድማለን።

የቡራዩ ወጣቶችን ወክለው ለቀናት ያለመታከት የኹለቱን አካባቢ ወጣቶች ለማቀራረብ ሲሰሩ ከነበሩ ወጣቶች መካከል አንዱ የሆነውን ወጣት ጃዋር ከድር የራሱን ልምድ አካፍሎናል። ጃዋር ወለጋ ሻምቦ አካባቢ ተወልዶ ትምህርቱን እንዳጠናቀቀ ወደ ቡራዩ ከቤተሰቦቹ ጋር በመምጣት ቤት ተከራይተው አንድላይ የሚኖሩ ሲሆን፣ ቤተሰቦቹን ለማገዝና ራሱን ለመቻል በግል ዘርፍ እየሠራ የሚገኝ ወጣት ነው።

በስደት የነበሩ የፖለቲካ ፓርቲ መሪዎች ወደ አገር ውስጥ በገቡበት ወቅት አቀባበሉን ለማድመቅ በሚል “ቀለም እንቀባለን! አትቀቡም!” በሚል በወጣቶች መካከል የተነሳውን ጸብና ያስከተለውን መዘዝ በደንብ ያስታውሰዋል። በጥቂቶች መካከል የተነሳው አለመግባባት እንዴት በአጭር ጊዜ ተስፋፍቶ በርካታ ጉዳት እንዳደረሰም ያውቃል። አሁን ላይ ሆኖ ሲያሥታውሰው ቁጭት የሚያድርበት ጃዋር በኹለቱም ወገን በተሠራው ሥራ በእጅጉ ይጸጸታል። ወጣትነት ከስሜታዊነት ጋር ተደምሮ መደረግ ያልነበረበት ተግባር መፈጸሙ ያሳዝነዋል።

አሁን ሲያስታወሰው የፖለቲካ ትኩስነት የነበረበትና ሠው ያልተረጋጋበት ወቅት ነበር። አሁን በቡራዩ ያለው ሠላም አስተማማኝ ነው የሚለው ጃዋር፣ ግጭቱ በተከሰተበት ወቅት እገሌ ነበረበት ብሎ ለመናገር እስኪያስቸግር ድረስ ሂደቱ የተወሳሰበ ነበር። ምንም የማያውቁ ሰዎች ላይ የበቀል እርምጃ የተወሰደበትና ድርጊቱ ወደነበርንበት ሠላም እንድንመለስ የተደረገውን ጥረት ከባድ ያደረገ ነበር ብሏል።

በወቅቱ በቦታው ስለነበረ፣ አለመስማማቱ በወጣቶች ተግባር እንዴት እንደተጋጋለና ፖለቲከኞችም እንዴት ሊጠቀሙባቸው እንደሞከሩ ትውስታውን የሚናገረው ጃዋር፣ የሠላምና ልማት ማዕከል ያዘጋጃቸው የዕርቀ ሠላም ሂደቶች የጥል ግድግዳውን ለማፍረስ እንደጠቀሙ ይናገራል። ማዕከሉ ባዘጋጃቸው ፕሮግራሞች አማካይነት ሠላማችንን በጋራ ለመጠበቅና የያኔው ክስተት እንዳይደገም በጋራ እንድንሰራ የሚያስችል አጋጣሚ ተፈጥሮልናል ሲል አስተያየቱን ይሰጣል።

ማዕከሉ፣ ወጣቶችን የሚያጋጫቸው ምንድን ነው? ብሎ የራሱ አጀንዳ ይዞ እኛን ስላቀራረበን፣ “እኛ ጋር ያለ ችግር እነሱ ጋር እንዳለ፣ እነሱ ጋር ያለም ችግር እኛ ጋር እንዳለ እንድናውቅ አደርጎናል” የሚለው ጃዋር፣ እኛ ብቻ ነን ተጎጂዎች የሚል ኹላችንም ጋር የነበረ አስተሳሰብ እንዲቀር በማዕከሉ የተሠራው ሥራ ጠቅሟል ይላል። ስሜታዊነት ቀርቶ ምክንያታዊ እንድንሆን የተዘጋጁት ውይይቶች ከማስተማራቸው ባሻገር፣ በማሕበረሰብ መካከል ልዩነት ስለማይጠፋ ግጭት የሚነሳ ከሆነ በውይይት መፍታትና መፍትሄ ማምጣት እንደምንችል ያወቅንበት ነበር ሲል የቡራዩ ወጣቶች አስተባባሪ ሆኖ ባየው ለውጥ ላይ አስተያየቱን ሰጥቷል።

በማዕከሉ የተዘጋጁት የውይይት መድረኮች አስተማሪ ከመሆናቸው በተጨማሪ ለወደፊቱም አብረውን እንደሚሰሩ በማወቃችን ትልቅ ጥቅም እናገኝበታለን የሚለው ይህ ወጣት፣ በውይይቱ ብቻ ሥራው እንዳይቆም ለማድረግ ከኮልፌ ወጣት ተወካዮች ጋር በመሆን የጋራ ኮሚቴ አቋቁመን በጋራ የበጎ አድራጎት ሥራዎችን ለመሥራት አቅደናል ብሏል። በሚያጋጩ ሳይሆን በሚያፋቅሩ የጋራ ነገሮች ላይ ለመሥራት መስማማታቸውን የሚናገረው ይህ የቡራዩ ወጣቶች አስተባባሪ፣ ቡራዩ ወደ ነበረችበት ሠላም እንድትመለስ ዕርቀ ሠላሙ ማገዙን ይመሰክራል። የከተማዋ ወጣቶች ተግባርም የሚደነቅ እንደሆነና ግጭቱ የፈጠረው ጸጸትና ቁጭት ስላገዘው በሌላው ቦታ ሆኖ እንዲያስብ ማድረጉን ይናገራል።

የሠላምና ልማት ማዕከል ያዘጋጃቸው ፕሮግራሞች አስፈላጊ ነበሩ የሚለው ጃዋር፣ እንደግለሰብ ብዙ የተማረበትና ከኹሉ ነገር የሰው ልጅና ሠላም መቅደም እንዳለበት ያወቀበት እንደሆነ ያስረዳል። ማዕከሉ የጀመረው ሥራ ተጠናክሮ መቀጠል አለበት የሚለው እሱ ብቻ ሳይሆን ተሳታፊዎች ጭምር እንደሆኑ በመናገር፣ የአሁኑ ትውልድ ከጥፋቱ የተማረው ቢኖርም ቀጣዩም ተመሳሳይ ችግር ውስጥ እንዳይወድቅ መቋረጥ የሌለበት እንደሆነ ይናገራል።

ማዕከሉ በጀመረው ሂደት አማካይነት የኹለቱ ከተማ ወጣቶች የጋራ ኮሚቴ አቋቁመው አብረው ለመሥራት ቢስማሙም፣ በአቅም ውስንነት ሳቢያ የፈለጉትን ያህል መንቀሳቀስ አለመቻላቸውን ጃዋር ይጠቁማል። በዘላቂነት አንዳችን ስለሌላችን ጥሩ አመለካከት እንዲኖረን የሚያስችለው የዕርቀ ሰላሙ ሂደት ለሌሎች እንዲዳረስ፣ እኛም ያወቅነውን ለሌሎቹ ማስተላለፍ እንድንችል የሚያግደን የአቅም ውሱንነት ተወግዶ የበለጠ መስራት እንደምንችል ተስማምተናል ይላል። ሳንተዋወቅ ስንጣላ የነበረውን አቁመን ተዋውቀን አንድ ቤተሰብ መሆናችንን ተገንዝበን እንድንረዳዳና ሌላውም ይህን ፈለግ ተከትሎ እንዲንቀሳቀስ የወጣቶቹ ፍላጎት መሆኑንም አስተባባሪው አሳውቋል።

ሌላዋ ስለስልጠናው ጠቃሚነት የምትናገረው የቡራዩ ወጣት ያብስራ ተስፋዬ ናት። የተወለደችው አዲስ አበባ ቢሆንም ያደገችው ቡራዩ ከተማ ነው። “ሰው የትም ይወለድ ያደገበትን አካባቢ ይመስላል” የምትለው ይህች ወጣት፣ ሠላም ለኹሉም ነገር መሠረት መሆኑን ትናገራለች።

ወጥቶ ለመግባትም ሆነ ሰርቶ ለመብላት ሠላም ከሌለ እንደማይቻል የምታምነው ያብስራ፣ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ሲወራ እየሰማች ያደገችው ነገር የሚያራርቅ እንደነበር ትናገራለች። በግጭቱ ወቅት የተፈጠረውን ያህል ጉዳት ያስከትላል ብለን ባንገምትም በኋላ የሆነውን ስናይ ስሜቱ ከባድ ነበር ትላለች። ብዙዎች ባለማወቅም ይሁን አውቀው፣ ወጣትነታቸውም ገፋፍቷቸው በሠሩት ሥራ ብዙ ነገር እንደታጣም የምታስታውሰውን ትጠቅሳለች። ቃላት እስኪያጥሩኝ ድረስ በወቅቱ የነበረውን ችግር መግለጽ ይከብደኛል የምትለው ያብስራ፣ አሁን ሳስበው የሚያስቆጭና የሚያሳዝን ከመሆኑ ባሻገር በሰቀቀንና በስጋት የኖርንበት ወቅት ነበር ብላለች። በክስተቱ ምክንያት አሁን ሠላም ወርዶም ቢሆን ቡራዩ ሠላም እንደሌለ አድርገው የሚያስቡ እንዳሉም ትሰማለች።

የሠላምና ልማት ማዕከል የኹለቱን ከተማ ወጣቶች ለማቀራረብና እርቀ ሠላም ለማውረድ እንቅስቃሴ ከጀመረ ወዲህ ብዙ ነገሮች መቀያየራቸውን አውቄያለሁ የምትለው ያብስራ፣ በግሏ ብቻ ሳይሆን በቤተሰቦቿና ጓደኞቿ ላይ ያመጣውን ለውጥ አስተውላለች። በማዕከሉ አማካይነት የተገኘው ስልጠና፣ በቅርበት ከማውቃቸው በተጨማሪ ለወደፊት የማውቃቸውንም እንድቀይር ያደርገኛል የምትለው ይህች ወጣት፣ ማዕከሉ ዓላማውን ተግባራዊ ለማድረግ እንቅስቃሴ ሲጀምር እንዲህ ውጤታማ ይሆናል ብላ አለመገመቷን ትጠቁማለች። አሁን ላይ ስትገመግመው ድሮ ያልነበረ ቅርርብ በኹለቱ ከተማ ወጣቶች መካከል ብቻ ሳይሆን የአንድ አካባቢ ነዋሪም እርስ በርሱ ይበልጥ እንዲተዋወቅ ማድረጉን ታምናለች። በማዕከሉ ስልጠና አማካይነት ይበልጥ ተቀራርበን እንደወንድምና እህት እየተያየን እንገኛለንም ብላለች።

ማዕከሉ ባዘጋጃቸው መድረኮች መገኘቴ በግል አመለካከቴን እንድቀይር አድርጎኛል የምትለው ያብስራ፣ ስለሰው ማንነት የነበረኝን የተዛባ አመለካከት እንዳስተካክል፣ የነበረኝም አተያይ ትክክል እንዳልነበረ እንዳውቅ አድርጎኛል የሚል እምነት አላት። ምን አይነት ሰው እንደነበርኩ፣ አሁን ደግሞ ምን አይነት አመለካከት እንዳለኝ አሳውቆኛል ስትልም ለውጡን እያነጻጸረች ትናገራለች። በአጠቃላይ ከምናየው ይልቅ ያለማስረጃ የምንሰማውን ብቻ ማመን እንደሌለብን አውቄያለሁ የምትለው ይህች የቡራዩ ወጣት፣ ሥልጠናው ለወደፊት ሌሎችንም እንዳሳውቅ ያግዘኛል ትላለች። እንደእሷ እምነት የማዕከሉ የእስካሁኑ ሥራና ብርታት ወጣቱ በራሱ እንዲጠነክር አድርጓል።

ዕድሉን ያላገኙ ወጣቶች በቀጣይ እንዲማሩ የበኩላችንን ማድረግ ይጠበቅብናል የምትለው ያብስራ፣ ይህን ለማሳካት እንዲችሉ ማዕከሉ ድጋፉን አጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቃለች። ማዕከሉ በፈጠረው መድረክ ተዋውቀን ኮሚቴ አቋቁመን የበለጠ በመግባባት ብንሠራም ሌላውም እንዲያውቅ መንቀሳቀስ እንፈልጋለን። ይህንንም ለማሳሳካት ድጋፍ ያስፈልገናል ስትል አስተያቷን ሰንዝራለች። ችግር ያለው በኹለቱ አካባቢዎች ብቻም ስላልሆነ ማዕከሉ አድማሱን አስፍቶ ቢንቀሳቀስ እንደኔ ብዙዎች አመለካከታቸውን እንዲቀይሩ ያደርጋል ስትል እማኝነቷን ሠጥታለች።


ቅጽ 3 ቁጥር 142 ሐምሌ 17 2013

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

error: Content is protected !!