የእለት ዜና

ኢትዮጵያ 5ተኛውን የአለም የቆዳ አምራቾች ምክክር ጎባኤ እና 36ኛውን አለም አቀፍ የቆዳ ቴክኖሎጂስትና ኬሚስቶች ማህበረሰብ ህብረት ጉባኤን ልታዘጋጅ ነው

ኢትዮጵያ በአፍሪካ ለመጀመሪያ ጊዜ የሚከናወኑትን 5ተኛውን የአለም የቆዳ አምራቾች ምክክር፣ እንዲሁም 36ኛውን አለም አቀፍ የቆዳ ቴክኖሎጂስትና ኬሚስትስ ማህበረሰብ ህብረት የምክክር መድረክ ልታዘጋጅ መሆኑ ተገለጿል።
መድረኮቹም ከጥቅምት 22 እስከ 26 2014 ዓ.ም ባሉት ቀናት ውስጥ በአዲስ አበባ የሚከናወኑ መሆናቸውን ባሳለፍነው ሀሙስ በስካይ ላይት ሆቴል በተሰጠ ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ተገልጿል።
በመግለጫው ላይ የተገኙት የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስተር ዲኤታ አቶ ተካ ገብረእየሱስ ኢትዮጵያ በቆዳ ዘርፍ ላይ ከፍተኛ አቅም ያላት ቢሆንም ይህንን አቅሟን በሚገባ እየተጠቀመች ባለመሆኑ እስከ አሁን ድረስ የቆዳ ምርቶችን ከውጪ እንደምታስገባ ተናግረዋል።
ሚኒስትሩ አክለውም የሚታዩ ችግሮችን ለማስተካከል በዘርፉ ሊሰሩ የሚችሉ ባለሀብትና ተቋማትን በማበረታታት፤ ምርታቸውን የሚያሳድጉበትና ሰፊ የገበያ ትስስርን የሚፈጥሩበትን ሁኔታዎች ለማመቻቸት መንግስት በመስራት ላይ እንደሚገኝ አስታውቀዋል።
የአፍሪካ ቆዳና የቆዳ ምርቶች ኢኒስቲትዩት ዳይሬክተር አማካሪ የሆኑት ፕሮፌሰር መኮንን ሀይለማርያም የአፍሪካን የቆዳ ገበያ በምሳሌ ሲያስረዱ የአፍሪካ የጫማ ኢንዱስትሪ በአመት ወደ 1 ቢሊየን የሚገመት ጥንድ እንደሚያመርት ገልፀው ይህም ከአፍሪካ ህዝብ አጠቃላይ ብዛት ያነሰ መሆኑን አስረድተዋል።
ከውጪ ወደ አፍሪካ የሚገባው የጫማ ምርት የሚቀንስ ከሆነ የአፍሪካ የጫማ ገበያ ከሌሎች ተያያዠ የስራ ፈጠራ እድሎች በተጨማሪ በሱቆች ደረጃ ብቻ ለ1 ነጥብ 6 ሚሊየን ሰዎች የስራ እድል መፍጠር ያስችላል ብለዎል።
በተያያዘም የ2021 የአፍሪካ ሶርሲንግ የፋሽን ሳምንት እና የቆዳ ምርቶች የንግድ ትርኢት ከህዳር 24 እስከ ህዳር 27 2014 ዓ.ም በኢትዮጵያ አስተናጋጅነት በአዲስ አበባ እንደሚካሄድም በመድረኩ ተገልጿል።
በፉሽን ሳምንቱም ከ25 ሀገራት የተውጣጡ 250 አለም አቀፍ አምራቾችና ሻጮች ምርታቸውን ከ5 ሺህ ለሚበልጡ የንግድ ባለሙያዎችና ሸማቹ ማህበረሰብ የሚያስተዋውቁበት እንደሚሆንም ተገልጿል።
ጉባዔዎቹና የፉሽን ሳምንቱ የቆዳ አምራቾችን፣ ገዢዎችን፣ ሻጮችንና ጥናት አድራጊዎችን የማስተሳሰር ትልቅ እድልን ይፈጥራሉ ተብሏል።


ቅጽ 3 ቁጥር 143 ሐምሌ 24 2013

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

error: Content is protected !!