የእለት ዜና

በጋምቤላ በደረሰው የጎርፍ አደጋ ክልሉ ከፌደራል መንግሥትን ምላሽ አለማግኘቱን ገለጸ

Views: 100

በላሬ ወረዳ በተከሰተ የጎርፍ አደጋ የተፈናቀሉ ሰዎችን ለማቋቋም የጋምቤላ ክልል ለፌደራል መንግስትን ጥሪ ቢያቀርብም መልስ አለማግኘቱን አስታውቋል።
የጋምቤላ ክልል አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር ጋትቤል ሙን እንደተናገሩት፣ በክልሉ ላሬ ወረዳ 4 ቀበሌዎች ላይ በደረሰ የጎርፍ አደጋ የተፈናቀሉ ሰዎች ቁጥር ከ 10 ሺሕ 600 በላይ መድረሱ ታውቋል።
ክልሉ ባለው አቅም በተወሰነ መልኩ የዘይትና የፉርኖ ዱቄት ድጋፍ አድርጓል ያሉት ጋትቤል፣ የተደረገው ድጋፍ ግን በቂ እንዳልሆነ ጠቁመዋል።
ለተፈናቃዮች ምንም አይነት መጠለያ እንዳልተሰራላቸው ያነሱት አቶ ጋትቤል፣ አሁን ላይ ተፈናቃዮች በደቡብ ሱዳን ድንበር አቅራቢያ መንገድ ዳር ላይ የሚገኙ ሲሆን፣ ዝናብ በሚዘንብበት ወቅት ከባድ ችግር እያጋጠማቸው መሆኑን ገልፀዋል።
ክልሉ ከአቅሙ በላይ በመሆኑ በኢትዮጵያ ውስጥ ከሚገኙ የተባበሩት መንግሥታት ተራድኦ ድርጅቶች ባሻገር ለፌደራል አደጋ ስጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን ቢያሳውቅም፣ አፋጣኝ ምላሽ ማግኘት እንዳልቻሉ ዳይሬክተሩ ተናግረዋል።


ቅጽ 3 ቁጥር 143 ሐምሌ 24 2013

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com