የእለት ዜና

ያልተዘመረላቸውን ስኬቶች ስለመሸለም

የሴቶች ስኬት አጀንዳ በሆነበት መድረክ የተለመዱ የሚመስሉና የሚጠበቁ፣ ወደ አእምሯችን የሚመጡ ምስሎች አሉ። የሴቶች ስኬት ማለት ከፍተኛ ወንበር ላይ ባለሥልጣን መሆን፣ ዲግሪን አንድ ኹለት ብሎ ቆጥሮ በብዛት መያዝና በእንግሊዘኛ ቋንቋ በብቃት መናገር፣ አመራር ላይ ያለ አንዳች እንከን ምርጥ ሥራዎችን መሥራት፣ በትልልቅ መድረኮች ላይ አንቱ እየተባሉ መጠራትና መሞገስ …ወዘተ። የሴቶች ስኬት ሲባል እነዚህን ነጥቦች የሚያስቡ ጥቂት አይደሉም።

ይህ ሲጠቀስ በልቦናችን ‹ኧረ! ይህን አይደለም ስኬት የምንለው!› ብለን ልንሞግት እንችላለን፣ በገሃድ በየመድረኩ የምናየው እውነት ግን ይኸው ነው። ሴቶችን በሚመለከት በሴቶች ጉዳይ በሚሠሩ ድርጅቶችና ተቋማት ባሰናዷቸው የእውቅናና የሽልማት ዝግጅቶች፣ ውዳሴዎችና ሙገሳዎች ለማን እንደተሰጡ መለስ ብሎ ማስታወስ በቂ ነው።

ይህ ማለት ሽልማትና እውቅና ላልተገባቸው ነው የተሰጠው ማለት አይደለም። ነገር ግን የሚገባቸውና በተባለው ደረጃ ያልተገኙ፣ ግን በአውዳቸው አረአያ ሊሆን የሚችልን ስኬት ያመጡ ብዙ ሴቶች አሉ፤ ያልታዩ፤ ያልተዘመረላቸው። በቄንጠኛ ልብስ ያልዘነጡ፣ ከተማሩት ጋር እኩል ‹ጽንሰ ሐሳብ› እያነሱ የማይሞግቱ፣ ከማኅበራዊ ድርሻቸው ሳይጎድሉ በመስኩም ሆነ በልጆቻቸው የነገ ሕይወት ውስጥ መልካም ዘርን የዘሩ ጥቂት አይደሉም፤ ግን ብዙዎቹ አልታዩም።

ኢትዮጵያ በዓለማችን ደሃ ከሚባሉ አገራት ተርታ ትገኛለች። ሴቶች ደግሞ በዚህ የከፋው ጉዳት ይደርስባቸዋል። እንዲህ ባለ ሁኔታ ውስጥ ሴቶች እንዲሁም በጠቅላላው ዜጎች ክፉ ቀንን ማሸነፊያ ብልሃት፣ አስቸጋሪ ጊዜን መወጫ መንገድ የሚፈልጉት ከቴሌቭዥን መስኮቶቻቸው አይደለም። ይልቁንም አጠገባቸው ካለች ብርቱ፣ ተስፋ ሳትቆርጥ የምትታገል መሳያቸው ነው። ታድያ እነዚህን ሴቶች ማጉላትና ማነሳሳት በእርግጥ ማኅበረሰብ ውስጥ የሚፈለገውን ለውጥ ለማምጣት አያስችልምን?

ይህን ነጥብ ያነሳነው በአንድ የሽልማት መሰናዶ በመገኘታችን ነው። ይህም የሴቶች ሰብአዊ መብት ተሟጋቾች ሽልማት ሲሆን አዘጋጁ ሲሃ ኔትወርክ ይባላል፤ ‹በአፍሪካ ቀንድ የሴቶች ስትራቴጂክ ኢኒሺዬቲቭ›።

ጥቂት ስለ ሲሃ ኔትወርክ
ሲሃ ኔትወርክ በአፍሪካ ቀንድ አገራት የሴቶች መብት ተሟጋች ድርጅት ነው። በዋናነትም የሴቶችን ሰብአዊ መብት ማስከበርን አልፎም የሴቶች ሰብአዊ መብት ተሟጋቾችን መደገፍን ሥራዬ ብሎታል። ሴቶች ይልቁንም ጥቃት የደረሰባቸው ነጻ የሕግ አገልግሎት እንዲያገኙ ማገዝ፣ በኢኮኖሚ ለተጎዱ ድጋፍ ማድረግ እንዲሁም ሴቶች በአገር ጉዳይና በሰላም ዙሪያ ንቁ ተሳትፎ እንዲያደርጉ ማበረታታት ተያያዥ ሥራው ነው።

ኔትወርኩ በአውሮፓውያን የዘመን አቆጣጠር በ1995 በጅቡቲ ነው የተመሠረተው። በኢትዮጵያ ሥራ ከጀመረ ዐስር ዓመት እንደተጠጋው የነገሩን የኔትወርኩ የመርሃ ግብር አስተባባሪ ዝምድና አበበ ናቸው። አክለውም ኔትወርኩ ላለፉት ኹለት ዓመታት ከሴቶች ሰብአዊ መብት ጋር በተያያዘ ሰፊ ፕሮጀክት ይዞ ሲሠራ መቆየቱን ጠቅሰዋል።

ይህን ተከትሎ ነው ኔትወርኩ ለመጀመሪያ ጊዜ የሴቶች ሰብአዊ መብት ተሟጋቾች ሽልማትን ያሰናዳው። በተለይም ከኮቪድ 19 ወረርሽኝ ጋር ተያይዞ በሴቶች ላይ የሚደርሱ ጫናዎችን በማጤን ድጋፍ ሲያደርጉና በአቅማቸው ሁሉ ሲያግዙ የነበሩት መመስገን፣ መታየትና መታወቅ አለባቸው በሚል እምነት ሽልማቱ ተግባራዊ ሆኗል።

አስቀድሞ ለሽልማት እጩዎችን የሰበሰበው ከሕዝብ ነው። በዛም ከቀረቡት መካከል በተለያዩ መስፈርቶች በመመዘን ሰባት ሴቶች በመጨረሻ ለውድድር ቀርበዋል። እጩዎቹን ለዛ ያበቃቸው ሰብአዊ መብት ማስከበርን በሚመለከት የተጓዙት መንገድ፣ ውጤታማነታቸው፣ ችግሮችን ተቋቁሞ የመዝለቅ አቅማቸውና በማኅበረሰቡ ዘንድ ያገኙት ተቀባይነት እንዲሁም የከፈሉት መስዋዕትነት ተቃኝቶ ነው።

አሸናፊዋ የ600 ዮሮ የገንዘብ ሽልማትን ጨምሮ ዋንጫ እንዲሁም በአገርም ሆነ በአፍሪካ ደረጃ ኔትወርኩ በሚንቀሳቀስባቸው በሚያዘጋጃቸው መድረኮች አብሮ በመሄድ ሥራዋን የማስተዋወቅ እድል ይሰጣታል። ለሽልማት በእጩነት የቀረቡት የሴቶች ሰብአዊ መብት ተሟጋች ዮርዳኖስ ነጋ፣ ሕሊና ኃይሉ፣ ሀና ለማ፣ በፀሎት ከፈለኝ፣ ጠይባ ያሲን፣ ማሪያ ሙኒር እና ለታይ ተስፋይ ናቸው።

ታድያ ምን አዲስ?
የሽልማቱ አሸናፊ ጠይባ ያሲን ናቸው። ጠይባ የኹለት ልጆች እናትና ከጥቂት ዓመታት በፊት ኑሮአቸውን በጉሊት ንግድ ሥራ ይመሩ የነበሩ ብርቱ ሴት ናቸው። ትንሽ በሚባል የፍራንክ ቁጠባ ነው ከጉሊት ሥራቸው ውጪ በቡድኖች መሳተፍ የጀመሩት። ያም ወደ ኅብረት አድጎ ቀጥሎ ወደ ጥምረት ተሻገረ፤ ‹ይታወቅ ጥምረት› ይባላል። በዛም ሰብሳቢ ሆነው አገልግለዋል።

አዲሱ ነገር ይህ ነው፤ ተሸላሚዋ ጠይባ በሴቶች ጉዳይ ሲሸለሙና እውቅና ሲሰጣቸው እንደምናያቸው ሴቶች አይደሉም፤ የመጡበት መንገድ ይለያል። ከጉሊት ንግድ ነው የተነሱት። ቀጥለው በቁጠባና ከመሳዮቻቸው ጋር በመደጋገፍ ራሳቸውን አሳድገው ስለሴቶች ልጆችና ወጣቶች፣ ስለእናቶችና ሚስቶች መብት መከበር የሚሟገቱ ሰው መሆን የቻሉ ናቸው።

ዝምድና ስለ ተሸላሚዋ ሲጠየቁ ይህን ነጥብ አንስተዋል። ‹‹ሁሌ ትኩረት የሚደረገው የተማሩና ሥልጡን ናቸው የሚባሉት [ሴቶች] ላይ ነው፤ ሽልማት ሲሰጥም ሆነ እንዲታዩ የሚደረገው እነሱ ናቸው። አንዲት ሴት ስላልተማረች ንቁ አይደለችም ማለት አይደለም። እንደውም ማኅበረሰብ ውስጥ ገብተው በትክክል ለውጥ ያመጡ ሰዎችን መሸለም ነው የሚገባው።››

ጠይባ ለሽልማቱ የታጩትም ሆነ አሸናፊ ሊሆኑ የቻሉበት ምክንያት ምን እንደሆነም ዝምድና ነግረውናል። በሴቶች ሰብአዊ መብት እንዲሁም ተያያዥ ጉዳዮች ላይ በሚካሄዱ መድረኮች በንቃት መሳተፋቸው፣ በቤተሰብ ያለባቸውን ድርሻና ጫና ሳያስታጉሉ ከማንኛውም ሰው እኩል ውጤታማ ሥራ መሥራት እንደሚቻል በተግባር በማሳየታቸው እንዲሁም ለሴቶች መብት መከበርና ለእኩልነት ያላቸው ተነሳሽነትና ፍላጎት ከብዙ በጥቂቱ ነው ብለዋል።

ጠይባ በየመድረኩ ወጥተው ሲሞግቱ፣ የሰብአዊ መብታቸው ተገፍፎ በየፍርድ ቤቱ ፍትህን ፍለጋ ከሚኳትኑ ሴቶች ጋር አብረው ለመታገል ሲቆሙ ከርመዋል። ‹‹ለዚህ ሽልማት ያበቃኝ በበጎ ፈቃደኛነት ሴቶችና ሕጻናት ዙሪያ ከሚሠሩ ጋር በጋራ እሠራለሁ። ሴቶች ሲነኩ አልወድም። ከትምህርት ቤት ጀምሮ ራስ አገዝ እስካሉ እናቶችና ሴቶች ድረስ ጥብቅና መቆም እወዳለሁ። ዛቻና ማስፈራሪያ ይደርስብኛል። ግን እሱን ጥዬ ነው የምሠራው። መንገድ ላይ ሳይቀር የሴቶችን ጥቃት ተመልክቼ አላልፍም።›› አሉ።

ሽልማት በማግኘታቸው ደስተኛ እንደሆኑም ገልጸዋል። ነገር ግን ሽልማቱ እንደውም ተጨማሪ የቤት ሥራ ነው ሲሉ ቀጥሎ ብዙ ሥራ እንደሚጠብቃቸው ጠቀስ አድርገዋል።
በበኩላቸው በማኅበረሰብ ውስጥ የሚገኙ ራስ አገዝ ቡድኖች፣ ማኅበራት እንዲሁም ጥምረቶች ለውጥ ለማምጣት የሚያስችሉ መሣሪያዎች ናቸው ባይ ናቸው። ‹‹ጥምረት ያመጣው ለውጥ ዝም ብሎ አይደለም። ከታች ጀምሮ ጓዳ ካለችውና ምንም ከማታውቀው፣ ገንዘብ ከሌላት የተጀመረ ሥራ ነው።›› ብለዋል።

ይህ የጥምረት ሥራ በአዲስ አበባ ብቻ ሳይሆን በሐሳዋ፣ በድሬዳዋ፣ በባህርዳር እንዲሁም በወሎ ከተሞችና በየክልሉ እንዳለ አውስተዋል። ጥምረቶች ባላቸው ዓመታዊ የጋራ መድረክም በየክልሉ ያሉ ችግሮችን በማንሳት ምን እናድርግ፣ ችግር ያለበት ጋር እንዴት ተደራሽ እንሁን በሚለው ዙሪያ ምክክር እንደሚደረግ አስታውቀዋል።

ጠይባ ቅሬታ አላቸው። መንግሥት ለእነዚህ አደረጃጀቶች ተገቢውን እውቅና አልሰጠም ይላሉ። ተገቢው እውቅና ቢሰጥ ግን እንዲህ ያሉ ለማኅበረሰቡ ቅርብ የሆኑ አደረጃጀቶች እንደ አገር ጠቃሚ ሊሆኑ እንደሚችሉ ያምናሉ።
ከጋዜጠኞች ‹የእናንተ ጥምረት ለውጥ አምጥቷል ትላላችሁ ወይ?› የሚል ጥያቄ ለጠይባ ቀርቦላቸዋል። መልሳቸው እንዲህ ነው፤ ‹‹እኛ ለውጥ አምጥተናል ብለን እናስባለን። መንግሥት እውቅና ስላልሰጠን እንጂ፣ ቢሰጠን የበለጠ ውጤታማ መሆን እንችል ነበር። ጥምረታችን በጋራ በመሆን ብዙ ሠርቷል፤ አሁንም ተግቶ እየሠራ ነው። ሰብአዊ መብት ላይ ከሲሃ ጋር በመሆን እየሠራን እንገኛለን። አልፈንም በአኅጉር ደረጃ ለመሥራት እያሰብን ነው።››

ጠይባ መሻታቸው መንግሥት ለአደረጃጀቱ እውቅና እንዲሰጥ ነው። ፍርድ ቤት ፍትህን ጥየቃ ሲሄዱ ‹ማን ናችሁ?› መባልን እንደጠሉ ጠቅሰዋል። ችግር ለገጠማት ሴት ፍትህን ፍለጋ ሲሄዱ አጥፊዎች በጎን በገንዘብ እንደሚለቀቁና፣ ጥምረቶች እውቅና ከተሰጣቸውና ከመንግሥት ጋር አብረው ከሠሩ ግን እነዚህን ችግሮች ቢያንስ ማቃለል እንደሚቻል እምነታቸው ነው።
‹‹ወደፊት ብዙ አስበናል።›› አሉ የሰብአዊ መብት ተሟጋቿና የሲሃ የሴቶች ሰብአዊ መብት ተሟጋቾች ሽልማት አሸናፊዋ ጠይባ፤ ‹‹አሁን ግን ሰላም ነው የምንፈልገው።››

ከነገራችን ጋር
የሲሃ ኔትወርክ የመርሃ ግብር አስተባባሪዋ ዝምድና አበበ በሽልማት መርሃ ግብሩ ከጋዜጠኞች ጋር ባደረጉት ቆይታ በሴቶች ላይ የሚደርሱ ጾታዊ ጥቃቶች ምክንያታቸው የኅብረተሰቡ የአመለካከት ችግር ነው አሉ። ይህን አሉታዊ አመለካከት በሴቶችም ሆነ በወንዶች በኩል መቀየር ካልተቻለ የሲቪል ማኅበራት ለብቻቸው ለውጥ ያመጣሉ ማለት ዘበት ነውም ሲሉ አክለዋል።

ብዙ ጊዜ ከመንግሥት በቂና ተገቢውን ምላሽ እያገኙ እንዳልሆነ በማንሳት፣ ከመንግሥት ጎን ቆመን ስንሠራ የሰብአዊ መብቶች እና ደኅንነት ጉዳዮች ላይ ስናግዝ ከመንግሥት በቂ ምላሽ ይሰጠን ሲሉ ጥሪ አቅርበዋል።


ቅጽ 3 ቁጥር 143 ሐምሌ 24 2013

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

error: Content is protected !!